1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፈናቀል እና የጤና ችግር ስጋቶች

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2011

ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ድንገት በአስገዳጅ አጋጣሚዎች ሲፈናቀሉ ለጊዜው የሚታሰበው ምን ይመገባሉ? የት ይጠለላሉ? ወይም ደግሞ ምንስ ይለብሳሉ? የሚሉት ሦስቱ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ናቸው። እነዚህ ሁሉ ሲጓደሉ በዋናነት የሚጎዳው የሰዎች የጤና ይዞታ ነው።

https://p.dw.com/p/3HIZQ
Äthiopien Vertriebene
ምስል Tizalegn Tesfaye

የጌዲዮ ተፈናቃዮችን እንደማሳያ

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች መበራከታቸው ይፋ ከሆነ ሰነባብቷል። ከመኖሪያ ቀዬ በመፈናቀል ምክንያት ከሚጎድሉት መሠረታዊ ፍላጎቶች ጎን ለጎን የጤና ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሚሆን የረድኤት ድርጅቶች በየጊዜው የሚያነሱት ጉዳይ ነው። ከኦሮሚያ ምሥራቅ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ተፈናቅለው ለወራት ዲላ ውስጥ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ወገኖች የክረምት ወራት በተቃረበበት በዚህ ወቅት አፋጣኝ ርምጃ ካልተወሰደ ለከፋ የጤና ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ጎሳ ተኮር ግጭት ያፈናቀለው አንድ ሚሊየን ገደማ ሕዝብ በሚገኝበት በደቡብ ኢትዮጵያ ከባድ የምግብ እጥረት ችግር እንደሚስተዋል ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ ባለፉት ሳምንታት ከ200 የሚበልጡ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕጻናትን ማከሙንም ገልጿል። በአካባቢው የድርጅቱ አስተባባሪ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል እንደገለጹት አንዳንድ ወላጆች እንደውም ችግሩ ልጆቹ ላይ ያስከተለው ጉዳት ከተባባሰ በኋላ ዘግይተው ነው ወደ ሕክምና ጣቢያቸው የሚመጡት። በዚህ ምክንያትም አንዳንዶቹን ማትረፍ እንዳልተቻለም አመልክተዋል።

Äthiopien Vertriebene
ምስል Tizalegn Tesfaye

ጉዳዩ የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ የመንግሥትን ትኩረት ከሳበ ወዲህ በቅርቡ በተጠቀሰው አካባቢ ያለውን የተፈናቃዮች ይዞታ ለማየት ወደስፍራው የተጓዘ አንድ ቡድን አባላትም ተመሳሳይ ነገር መመልከታቸውን ይናገራሉ። ተፈናቃዮቹን በቅርቡ ሄደው ከተመለከቱት አንዷ ጋዜጠኛ ትዕግሥት ካሣ በተለይ ጎቲቲ በተባለው ስፍራ ያስተዋለችውን እንዲህ ትገልጻለች።

«ወደዚያ የሄድነው እንግዲህ ዋናው የተፈናቃዮቹ ቁጥር በብዛት አለበት የተባለው ገደብን ካየን በኋላ ነው። ገደብ ላይ ወደ 300 ሺህ ተፈናቃይ አለ። ግን ገደብ ለከተማው ቅርብ ነው ለዲላ ከተማ። የጌዲኦ ዋና ከተማ ዲላ ናት። ለዚያ በጣም ቅርብ ስለሆነ ሰዋዊው ርዳታ በተወሰነ መልኩ ይመጣልም። የሚጠይቃቸውም ሰው በብዛት ስላለ፣ ችግሩ ያለ ቢሆንም፣ ትኩረት ግን እያገኙ ስለሆነ ከእሱ አልፈን ትኩረት ያጡት ጋር ነበር ለማየት የሄድነው።»

Äthiopien Vertriebenen
ምስል Tizalegn Tesfaye

የሕግ ባለሙያው አቶ መሱድ ገበየሁ ከሁለት ሳምንት በፊት በተጠቀሰው ስፍራ ያሉትን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙበትን ሁኔታ ለመመልከት ጋዜጠኛ ትዕግሥት አብራው የተጓዘችውን ቡድን ያደረገውን ጉዞ ያስተባበሩ ናቸው። የጉዟቸው አላማም በአካባቢው ያለውን የመፈናቀል ሁኔታ ለማየት እና ምን ዓይነት ርዳታ ማድረግ እንደሚቻል እና እንዴትስ ማስተባበር እንደሚቻል ጥናት ለማድረግ እንደነበር ነግረውናል።

«ከ15 ቀናት በፊት ነው ወደ ጌዲኦ ሄደን የነበረው። ያገኘነው ማኅበረሰብ ትንሽ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። በተለይ ጌዲኦ ከዋናው ከተማ ከዲቻ ገደብ የሚባል አለ። አንድ ዘጠና እንደተሄደ ገደብ ላይ ከ300 ሺህ በላይ ተፈናቅሎ ነው ያለው። እዚያ ያለው አንፃራዊ በሆነ መልኩ መሠረታዊ ነገሮች የምግብ የመጠለያ እነዚህ እና መሰል ነገሮች እያገኙ ነው። ከገደብ አንድ 20 ኪሎ ሜትር ጎቴቲ የምትባል ጣቢያ አለች። በተለይ እዚያ ስፍራ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ነው። በጣም አስቸኳይ ርዳታ የሚያስፈልገው ብዙ መሠረታዊ ነገር የጎደለው።»

Äthiopien Vertriebene
ምስል Tizalegn Tesfaye

ቡድኑ የተመለከተውን  በአካባቢው  ለሚገኙ ለዞኑ አመራሮች፤ ለክልሉ እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መግለጻቸውንም ዘርዝረዋል። በእነሱ እይታም ከሚቀርበው የምግብ እና የአልባሳት ርዳታ በተጨማሪ አፋጣኝ የጤና አገልግሎት ርዳታ ለተፈናቃዮቹ ያስፈልጋል። እነሱ በቦታው ተገኝተው ተፈናቃዮቹ የሚገኙበትን ችግር ካስተዋሉ በኋላም እረፍት ነስቷቸው የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆኑ ሌላውም ወገን እንዲህ ያለውን እንግልት ትኩረት እንዲሰጠው ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸውልናል።

ተፈናቃዮቹን በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ እንደሚጎበኙ የተነገረን በዲላ ሃኪም ቤት የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ዶክተር ተስፋነው በቀለ በጎ ፈቃደኛ ሌሎች የሙያ አጋሮቻቸውን እና ዜጎችን በማስተባበር እነዚህን ወገኖች ለመርዳት እየሞከሩ ነው። እሳቸውም ተፈናቃዮቹን የጎበኘው ቡድኑ ያነሳውን የጤና ስጋት ያረጋግጣሉ።

Äthiopien Vertriebene
ምስል Tizalegn Tesfaye

ከመፈናቀል ጋር በተገናኘ የሚከተለው ማንኛውም ችግር ጤና ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ እንደማይቀር ያመለከቱት የደቡብ ክልል የጤና እና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ሥራ ሂደት ክፍል ተወካይ የሆኑት አቶ አባተ አዶሳ ለተፈናቃዮቹ በተቻለ አቅም መቅረብ የሚገባቸውን ነገሮች እያቀረብን ነው ይላሉ። ሆኖም በበጎ ፈቃደኝነት ተፈናቃዮቹን በተደጋጋሚ በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ዶክተር ተስፋነው የክረምቱ ወራት ሲጠናከር በተፈናቃዮቹ መንደር አሳሳቢ የጤና ችግር እንዳይከተል ስጋት አላቸው።

የጌዲኦ ዞን ተፈናቃዮች ቁጥር በተለያዩ አካላት በተለያየ መጠን እንደሚቀርብ የገለፁልን በደቡብ ክልል የቀይ መስቀል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ ድርጅታቸው ከሌሎች ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን የሚችለውን እያደረገ ቢሆንም አሁን ካለው የሰው ብዛት እና ፍላጎት አኳያ በቂ ርዳታ እየቀረበ ነው ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል። በነገራችን ላይ አድማጮች እነዚህ ተፈናቃይ ወገኖች የሚገኙበትን ሁኔታ ተመልክተው ያለውን የጤና ችግርም ቃኝተው መምጣታቸው ከተገለጸልን ጥቂት የማይባሉ የህክምና ባለሙያዎች ያስተዋሉትን እንዲያጋሩን ያደረግነው ጥረት ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት ይኖረዋል በሚል ስጋት ስለገባቸው እንዳልተሳካልን መግለፅ እንወዳለን። በደቡብ ክልል የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን በተመለከተ ያሳስባል የተባለው የጤና ችግር ላይ የየበኩላቸውን ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን እናመሰግናለን። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ