1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምሥራቅ ጀርመን

ማክሰኞ፣ ጥር 29 2010

ጀርመንን ለሁለት ከፍሎ የቆየው የበርሊን ግንብ እድሜ እና ግንቡ ከፈረሰ በኋላ የተቆጠረው ጊዜ  ትናንት በጎርጎሮሳዊው የካቲት 5፣2018 እኩል ሆኗል። የጀርመን ኤኮኖሚ ከውህደቱ በኋላ እያደገ ከአውሮጳ የበላይነቱን ቢይዝም በቀድሞው የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች ግን አሁንም ልዩ ልዩ ማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ አላገኙም።

https://p.dw.com/p/2sD4Y
Deutschland Brandenburger-Tor 1990
ምስል imago/F. Berger

ምሥራቅ ጀርመን ከበርሊን ግንብ መፍረስ በኋላ

ጀርመንን ከፍሎ የነበረው ግንብ መሰራት የጀመረው በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 1961 ዓም ነበር ። የፈረሰው ደግሞ ህዳር 9 1989 ነው። ግንቡ መፍረስ የጀመረው በተሰራ በ28 ዓመት ከ2 ወር  ከ26 ቀናት በኋላ ነው። ግንቡ ከፈረሰ እስከ ትናንት ያለው ጊዜ ሲሰላ ደግሞ ከግንቡ እድሜ ጋር የሚስተካከል ሆኗል። የግንቡ እድሜ እና ከፈረሰ በኋላ የተቆጠረው ዘመን እኩል መሆን እዚህ ጀርመን ትናንት ትውስታን እያጫረ ብዙ አነጋግሯል።  ለጀርመን ብቻ ሳይሆን ለዓለም በትልቅ ተምሳሌትነቱ የሚጠቀሰውን ሰላማዊውን የጀርመን ውህደት ያፈጠነው ሳይጠበቅ እና ሳይታሰብ የበርሊን ግንብ መፍረሱ ነበር። ያኔ በስፍራው የሆነውን የመከታተል እድል ከነበራቸው መካከል የኔ ምዕራብ በርሊን ውስጥ ተማሪ የነበሩት አቶ በላይነህ ተሾመ አንዱ ናቸው።

Deutschland Berliner Mauer
ምስል Getty Images/AFP/G. Malie

አቶ በላይነህ ጀርመን ሲኖሩ ከ35 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ግንቡ ከመፍረሱ በፊት በሁለቱ ጀርመኖች መካከል የነበረውን ልዩነትም በቅጡ ያውቃሉ። ተማሪ ሳሉ ምሥራቅ ጀርመን በሄዱባቸው አጋጣሚዎች ልዩነቶቹ በግልጽ የሚታዩ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

ዶክተር አየለ ጉግሳም የበርሊን ግንብ ሲፈርስ ተማሪ ነበሩ። እርሳቸው ደግሞ ምሥራቅ በርሊን ውስጥ ነበር የሚኖሩት። ምዕራብ ጀርመንን በጎበኙባቸው አጋጣሚዎች ጎልቶ የሚታይ ልዩነት እንደነበረ ነው የሚናገሩት። ልዩነቱንም የገለጹት የሰማይና የምድር ያህል ነበር ሲሉ ነው።

የጀርመን ውህደት ለጀርመን ኤኮኖሚ መመንደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ልዩ ልዩ መብቶቻቸው ላይ ገደብ ተጥሎባቸው የነበሩ ዜጎች ነጻነት አኝኝተዋል። ውህደቱ እነዚህን እና ሌሎችንም  በርካታ ጥቅሞችን ማስገኘቱ ቢታወቅም ቀድሞ በኮምኒስት አስተዳደር ስር ለነበረው ምሥራቅ ጀርመን ግን ተስፋ የተደረገበትን እና የተጠበቀውን ያህል ውጤት አለማስገኘቱ አንዱ ችግር ነው እንደ ዶክተር አየለ ።አቶ በላይነህ እንደሚሉት በዚህ የተነሳ አንዳንድ የምሥራቅ ጀርመን አካባቢዎች አሁንም ድረስ ወደ ኃላ እንደቀሩ ነው።

Ausstellung 28 Achtundzwanzig Jahre Berlin mit und ohne Mauer
ምስል Stiftung Berliner Mauer/W. Rupprecht

ይህ ባስከተለው ቅሬታ ምሥራቅ ጀርመኖች መብታቸው እንዳልተጠበቀ በመቁጠር የቀኝ ጽንፈኛ እና የዘረኛ እንቅስቃሴዎች መነኻሪያ ሆነዋልም ይላሉ አቶ በላይነህ ። ቀኝ ጽንፈኞች በምሥራቅ ጀርመን ምክር ቤቶች ውስጥ የሚይዟቸው መቀመጫዎች ቁጥር እያደገ የመምጣቱ ፣ባለፈው መስከረም በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫም «አማራጭ ለጀርመን»የተባለው መጤ ጠል ፓርቲ ብዙ ድምጽ አግኝቶ የጀርመን ምክር ቤት ውስጥ መግባት የመቻሉ ምክንያት በምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ላይ ያደረው የተረስተናል ስሜት ነው እንደ አቶ በላይነህ።

ዶክተር አየለ ደግሞ የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ መጠናከር የጀርመን ችግር ብቻ አይደለም ይላሉ። ያም ሆኖ ከጀርመኖች ውህደት ሌላው ዓለም ብዙ ትምሕርት ሊቀስም ይችላል ይላሉ አቶ በላይነህ ።

ኂሩት መለሰ

ተስፋለም ወልደየስ