1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ፣አልጄሪያና ሱዳን ሦስትና አንድነት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2011

ቃዛፊ እንደ ጦር ኃይሎች ጠቃላይ አዛዥ ያዋጉትን ጦርነት፣ አብዱል አዚዝ ቡተፈለቃ እንደ እዉቅ ዲፕሎማት ሲዘዉሩት ነበር።የአረቦችን ዉጊያ ዲፕሎማሲ ቃዛፊ ከትሪፖሊ-ካይሮ-ደማስቆ፣ ቡተፈሊቃ ከአልጀርስ፣ፓሪስ፣ኒዮርክ  ሲያሾሩት የ29ኝ ዓመቱ ወጣት የጦር መኮንን ሲና ግንባር ከእስራኤል ጦር ጋር ይፋለም ነበር።

https://p.dw.com/p/3GoMm
Sudan Proteste gegen Präsident Omar Al-Bashir in Khartoum
ምስል Reuters

የሦስቱ መሪዎች አንድነት እና ልዩነት

በ1973ቱ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዐረብ እስራኤል ጦርነት እስራኤል ጎን የተሰለፈችዉን ዩናይትድ ስቴትስን በመቃወም በዩናይትድ ስቴትስ ላይ የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ በመጣል የመጀመሪያዉ የዓረብ መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ነበሩ።ቃዛፊ እንደ ጦር ኃይሎች ጠቃላይ አዛዥ ያዋጉትን ጦርነት፣ አብዱል አዚዝ ቡተፈለቃ እንደ እዉቅ ዲፕሎማት ሲዘዉሩት ነበር።የአረቦችን ዉጊያ ዲፕሎማሲ ቃዛፊ ከትሪፖሊ-ካይሮ-ደማስቆ፣ ቡተፈሊቃ ከአልጀርስ፣ፓሪስ፣ኒዮርክ  ሲያሾሩት የ29ኝ ዓመቱ ወጣት የጦር መኮንን ሲና ግንባር ከእስራኤል ጦር ጋር ይፋለም ነበር።ሶስቱም ወታደሮች ነበሩ።ግን አይዋደዱም።ሶስቱም የየሐገራቸዉን ፖለቲካዊ ሥርዓት የለወጡ ነበሩ።እንደ ተጠላለፉ ኖሩ።ሶስቱም በሕዝብ አመፅ ከየመንበራቸዉ ተወገዱ።ቃዛፊ፣ቡተፈሊቃ፣ አል በሽር።የአልበሽር ትኩረታችን፣ የሁለቱ ማጣቀሻ፣ የየሐገራቱ ዕዉነት መድረሻችን ነዉ።

                                         

በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር የታገዙት የሊቢያ አማፂያን ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ገድለዉ የትሪፖሊ ቤተ-መንግሥትን እንደተቆጣጠሩ ለአጎራባቾቻቸዉ መንግስታት ካስተላለፏቸዉ መልዕክቶች አንዱ የቃዛፊን ሐብትና ቤተ-ሰቦችን ወደ ሊቢያ እንዲመልሱ ወይም ለቃዛፊ ቤተ-ሰቦችና ተከታዮች ድጋፍ እንዳይሰጡ የሚጠይቀዉ ቀዳሚዉ ነበር።ከምዕራባዉያን መንግሥታት ሙሉ ድጋፍና ትብብር ያልተለዉ ጥያቄ በጦርነቱ ወቅት ለአብዛኞቹ የቃዛፊ ቤተ-ሰቦች ጥገኝነት ለሰጠችዉ አልጀሪያ በጣሙን ለፕሬዝደንቷ ለአብዱል አዚዝ ቡተፈሊቃ ፈታኝ ጥያቄ ነበር።

Sudan Omar Al-Bashir
ምስል Reuters/M. N. Abdallah

ቡተፈሊቃ ከአዲሶቹ የትሪፖሊ ገዢዎች ይልቅ የምዕራባዉያንን ግፊትና ጫና በዘዴ ለማለፍ ጥርሳቸዉን በነቀሉበት ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ቃላት ሲቀምሩ የሱዳኑ ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽር ተንደርድረዉ ትሪፖሊ ገቡ።የሊቢያ አማፂያን የትሪፖሊ ቤተ-መንግስትን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሊቢያን በጎበኙት የሱዳኑን ፕሬዝደንት የቀደመ የአፍሪቃም የዐረብም መሪ አልነበረም።ጥር 2012።አሉም።

«እዚሕ የመጣነዉ የሊቢያ ሕዝብ ቃዛፊን ከስልጣን በማስወገድ ለሱዳን ሕዝብ ታላቅ ስጦታ በማቅረቡ ልናመሰግን ነዉ።ሱዳንን የከፋፈለዉ ኢፍትሐዊነት፣ወረራና አመፅ ናቸዉ።እነዚሕ በሙሉ  በቃዛፊ ቀጥተኛ ድጋፍ ነበራቸዉ።»

አልበሽር በርግጥ በሙዐመር ቃዛፊ መገደል የሚፈነዱቁበት ምክንያት ነበራቸዉ።ቃዛፊ በ1969  ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ  ከካርቱም መሪዎች ጋር ብዙም ተጣጥመዉ አያዉቁም።ቃዛፊን በስድስት ወር ግድም ቀድመዉ ኢስማኢል አል አዝሐሪ የሚመሩትን የሱዳንን ሲቢላዊ አስተዳደር አስወገድዉ ሥልጣን የያዙት ጄኔራል ጃዓፈር መሐመድ አል-ኒሜሪ ፖለቲካ የሳባቸዉ፣ ለመፈንቅለ መንግስት የገፋፋቸዉ፣ የአስተሳሰባቸዉም መሠረት የያኔዉ የግብፅ መሪ፣የዓረቡ ዓለም እዉቅ ብሔረተኛ የገማል አብድናስር አስተምሕሮ ነበር።

Algerien Algier Proteste gegen Regierung
ምስል picture-alliance/NurPhoto/B. Bensalem

ሻለቃ ቃዛፊም የንጉስ ኢድሪስን ዙፋን መነቃቅረዉ ሊቢያን የተቆጣጠሩት የናስር አስተምሮ ምርኮኛ፣ ታማኝ ደቀ-መዝሙር በመሆናቸዉ ነበር።ከ1280 ኪሎ ሜትር በላይ ድንበር የሚጋሩትን  ሱዳንና ሊቢያን የሚመሩት ሁለቱም የጦር መኮንኖች፤ ሁለቱም አረቦች፤ሁለቱም ብሔረተኞች፣ሁለቱም የአንድ ሰዉ፣ ደቀመዛሙርት ቢሆኑም ሊግባቡ ግን አልቻሉም።

በ1973 የአረብ እስራኤሎች ጦርነት ግብፅ ለምትመራዉ ጦር ኒሜሪ አል በሽርን የመሳሰሉ ወጣት የጦር መኮንኖችን፣ ቃዛፊ ከዶላር እስከ የጦር ጄት፤ ከወታደር እስከ ድንኳን  አዝምተዉ ለናስር ወራሽ ለአንዋር አ ሳዳት የነበራቸዉን ታማኝነት አስመስክረዋል።ይሁና ኑሜሪ ወደ ምዕራቦቹ በተለይም ወደ ዩትድ ስቴትስ ማዘንበላቸዉን የትሪፖሊዉ ቁጡ መሪ አልወደዱትም።ቃዛፊ ኒሜሪን ለመበቀል የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጪ ጦር (SPLA)ን ጨምሮ የኒሜሩን ተቃዋሚዎች ያስታጥቁ፣ ያደራጁ፣በዲፕሎማሲም ይረዱ ነበር/

ሳዲቅ አል መሕዲ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን ቃዛፊ የካርቱሞች  «ወዳጅ»  መሆናቸዉን ቢያስታዉቁም  የወዳጅነቱ መሠረት በቅጡ ሳይጣል በ1989 ኮሎኔል ዑመር ሐሰን አልበሽር የመሕዲን መንግስት አስወግደዉ ስልጣን ያዙ።እንደገና ጠብ።

ቃዛፊ የዳርፉር አማፂያንን በተለይም የፍትሕና እኩልነት ንቅናቄ (JEM) የተባለዉን አማፂ ቡድን እስካፍንጫዉ ማስታጠቃቸዉ፣ የንቅናቄዉ መሪ ለዶክተር ኻሊል ኢብራሒም መዉጪያ መግቢያ መፍቀዳቸዉ ለአል በሽር የብቀላ ሴራ ከበቂ በላይ ምክንያት ነዉ።

የቃዛፊ ተቃዋሚዎች ቤንጋዚ ላይ መደራጀት ሲጀምሩ ጦር መሳሪያ አቀባይ፣መረጃ አስተላላፊ፣ መንገድ መሪዎችም የአልበሽር ወታደሮች ወይም ሰላዮች ነበሩ።የቃዛፊ ተወዳጅ፣ ታማኝ  አልጋወራሽም ይሆናሉ ተብለዉ ይጠበቁ የነበሩትን ልጃቸዉን ሰይፍ አል-ኢስላምን ሕዳር 2011 የያዙት ዚንታን የተባሉት የሊቢያ ሚሊሺያዎች ናቸዉ።ሰይፍ አል ኢስላም ያሉበትን ሥፍራ፣የሸሸጓቸዉን ሰዎች ማንነት፣የታጠቁን መሳሪያ ሳይቀር የጠቆሙት ግን CIA አይደለም።ሞሳድ አይደለም፣ MI 16 ወይም MI15 አይደሉም።የሱዳን ብሔራዊ የመረጃ አገልግሎት NISS እንጂ።

Algerien Präsident Abdelaziz Bouteflika
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Djarboub

አል በሽር ከፖለቲከኛነትም፣ ከዲፕሎማትነትም ይልቅ እንደ ጦር ጄኔራልነታቸዉ ቃዛፊን የማጥፋታቸዉን ድል ሲያቅራሩ፣ቡተፈሊቃ ድምፃቸዉን አጥፍተዉ ሊቢያን ከሠላማዊ፣ ሐብታም ሐገርነት ወደ ወሮበሎች መፈንጫነት ያሽቀነጠረዉ ለዉጥ ድንበር እንዳይሻገር ይታትሩ ነበሩ።

አልበሽርም ሆኑ ቡተፈሊቃ ግን የያዙትን ሥልጣን እንድም እንደ ቃዛፊ ዘር-ማንዘራቸዉን አስገድለዉ፣ተገድለዉ ሁሉንም እንደሚያጡት፣ሁለትም እንደ ቤን ዓሊ ተሰደዉ፣ ሶስትም እንደ ሙባረክ ተዋርደዉ እንደሚቀሙ ያሰቡ አይመስሉም።የፖለቲካ ተንታኝ አበበ አይነቴ እንደሚሉት የአፍሪቃ መሪዎች ስልጣን የሚያራዝሙበትን እንጂ የሚለቁበትን አስበዉ አያዉቁም።

ቃዛፊ ሲሻቸዉ እንደ ንጉስ ሲያሰኛቸዉ እንደማይነካ አምባገነን፣ አልበሽር እንደ ጦር ጄኔራል፣ ቡተፈሊቃ እንደ ዲፕሎማት ያስቡ ይሆናል።ሶስቱም ግን ስለ ሥልጣናቸዉ ያሰቡት አንድ ነበር።መቆየት። እርግጥ ነዉ የሊቢያ ምስቅልቅል ካንድ ሁለት አደጋዎች በስተቀር አልጄሪያን እንዳያብጥ የቡተፈሊቃ ብልሐት ብዙ ጠቅሟል።

የአልጄሪያ የነፃነት ተፋላሚ፣ ወታደር፣ የረጅም ጊዜዉ ዲፕሎማት፣የ20 ዘመኑ ፕሬዝደንት ጤናቸዉም እድሜያቸዉም ከድቷቸዉ   በድናቸዉ ሐገር እንዲገዛ መሞከራቸዉ ግን በርግጥ  ጅልነት ነበር።ከ1962 ጀምረዉ የወጣት ሚንስትር፣ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር፣ አፈ ጉባኤ፣ ኋላም ፕሬዝደንት ሆነዉ 57 ዘመን እንደተከበሩ ኖሩ።በስተማብቂያዉ ግን ተጠልተዉ-ተዋርደዉ ተሰናበቱ።

Libyen Protest gegen Gaddafi 2011
ምስል picture-alliance/dpa/M. Messara

«የሪፐብሊኪቱ ፕሬዝደንት ሥልጣን መልቀቃቸዉን ለሕገ-መንግስታዊዉ ምክር ቤት ፕሬዝደንት በይፋ አስታዉቀዋል።»የቡተፈሊቃ ዉድቀት በርግጥ አሳዛኝ ነዉ።የአልጄሪያ ፖለቲካዊ ጉዞ የአልጄሪያዉያን  የወደፊት ዕጣ ፈንታ ግን በምንም መንገድ ግን የሊቢያን ያክል አስደንጋጭ፣ የሱዳንን ያክል አጠራሪ አይሆንም።ሊቢያ ዛሬ ሐገር ለመባል ከስም በስተቀር የተረፋት የለም።የመዓልት ወሌት ዜናዋ ግድያ፣አፈና፣ባርነት፣ዝርፊያ፣ዉጊያ ነዉ።

የዛሬ ሰባት ዓመት ትሪፖሊ ድረስ ተጉዘዉ ድል ገድላቸዉን የደሰኮሩት የሱዳኑ ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽር በርግጥ እንደ ቃዛፊ ግንባራቸዉን ፈርክሶ የጣላቸዉ የለም።ግን ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ ከዚያ ከሚያቅራሩበት ወንበር ተሽቀንጥረዋል።የቀድሞ ታማኝ ጄኔራላቸዉ እንዳሉት ታስረዋል።

«እኔ የመከላከያ ሚንስርና የጊዚያዊ የፀጥታ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሥርዓቱ መወገዱን ፤የሥርዓቱ መሪ መታሰራቸዉን  አስታዉቃለሁ።አስተማማኝ ሥፍራ በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን አስታዉቃለሁ።ከዚሕም በተጨማሪ የሚከተለዉን አስታዉቃለሁ።አንደኛ የሐገሪቱን አስተዳደር ለሁለት ዓመታት የሚይዝ  የሽግግር ወታደራዊ ምክር ቤት መቋቋሙን አስታዉቃለሁ።በ2005 የፀደቀዉ የሱዳን ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት መታገዱን አስታዉቃለሁ።»

ምክትል ፕሬዝደንትና መከላከያ ሚንስትር ጄኔራል አዋድ መሐመድ አሕመድ ኢብን አሁፍ።ሐሙስ።የአል በሽርን አገዛዝ በመቃወም ካለፈዉ ታሕሳስ ጀምሮ ባደባባይ ሲሰለፍ የከረመዉ የሱዳን ሕዝብ የሰላሳ ዘመን ገዢዉ ከስልጣን በመወገዳቸዉ መደሰት፣መርካት፣ተስፋ ማድረጉ አልቀረም።

ጦር ኃይሉ ከቀድሞዉ ገዢዉ የነጠቀዉን ሥልጣን ለሁለት ዓመት እንደተቆጣጠረ ለመቆየት መወሰኑ እንጂ የደስታ፣ፌስታ፣ ተስፋዉ  ቅጭት።በፊት ለተቃዉሞ፣ ሐሙስ ለደስታ አደባባይ የወጣዉ ህዝብ ፌስታዉን አዲሶቹን ጄኔራሎች መቃወሚያ አደረገዉ።የተቃዉሞዉ መቀጠል የሚያስከትለዉ ቀዉስ አስገምግሞ ሳያበቃ ወታደራዊ ምክር ቤቱን ይመራሉ የተባሉት ጄኔራሎች እርበርስ መሻኮታቸዉ ገሐድ ወጥቷል።

ሐሙስ የአል-በሽርን መዉረድ ያወጁት ጄኔራል አዋድ መሐመድ አሕመድ ኢብን አዉፍ ዐርብ ሥልጣናቸዉን ለቀዉ በምትካቸዉ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ተሾመዋል።የጄኔራሎቹ ሹም ሽር የሱዳን ጦር አዛዦች እርስበርስም፣ ከስለላዉ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋርም እየተሻኮቱ መሆኑን ጠቋሚ ነዉ።

Muammar al-Gaddafi
ምስል Getty Images/AFP/F. Monteforte

ሱዳን እንደ ሊቢያ ወይም እንደ አልጄሪያ ምዕራባዉያንን የሚያማልል ሐብት የላትም።ሥልታዊ አቀማመጥዋ፣ የፖለቲካ ማዕከልነቷ፣ ከሁሉም በላይ ስፋትና ትልቅነቷ  ነዳጅ ከታቀፉት የበለጠ በተለይ ለአፍሪቃ እጅግ ጠቃሚ ያደርጋታል።ግብፅ-ከሰሜን፣ ኢትዮጵያ ከደቡብ ምሥራቅ፣ ኤርትራ ከምሥራቅ፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ከደቡብ ምዕራብ፤ ደቡብ ሱዳን ከደቡብ፤ ሊቢያ ራስዋ ከሰሜን ምዕራብ ሁሉም ወደ ካርቱም እያዩ ነዉ።

የአባይ ግድብ፣ የደቡብ ሱዳን ሠላም፣ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ዉዝግብ መቀጠል አለመቀጠሉ ካርቱም ላይ የሚበየን ነዉ።የአዲሶቹ ወታደራዊ ገዢዎች ተወካዮች ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ሕብረት መሪዎችን አነጋግረዋል።የንግግራቸዉ ዉጤት ምንም ሆነ-ምን የሚወሰነዉ ግን እንደገና ካርቱም እንጂ አዲስ አበባ አይደለም።ሊቢያን ወይስ አልጀሪያን ትሆን ይሆን? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ