1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ከ100 ሺህ በላይ ህፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተዳርገዋል

ዓርብ፣ ጥር 3 2016

በሰሜን ጎንደር ዞን በተለይም ጃንአሞራ ወረዳ የተከሰተው ድርቅ በእንስሳትና በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናገሩ። መንግስት በአፋጣኝና በተከታታይ እርዳታ ካላቀረበ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት እየፈጠረ ነዉ ባይ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4bATt
ድርቅ እና ረሃብ በኢትዮጵያ
ድርቅ እና ረሃብ በኢትዮጵያ ምስል Million Haileselassie Brhane/DW

በሰሜን ጎንደር ዞን የጃናሞራ ወረዳ የከፋ ረሃብ ተከስቷል

በሰሜን ጎንደር ዞን በተለይም ጃንአሞራ ወረዳ የተከሰተው ድርቅ በእንስሳትና በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናገሩ።  መንግስት በአፋጣኝና በተከታታይ እርዳታ ካላቀረበ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት እየፈጠረ ነዉ ባይ ነዉ። ባለፈው የክረምት ወራት የሚጠበቀው ዝናብ ባለመጣሉ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል፡፡በተለይ የከፋ ድርቅ ከተከሰተባቸው ወረዳዎች መካከል በሰሜን ጎንደር ዞን የጃናሞራ ወረዳ ቀዳሚው እንደሆነነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ አንድ የጃንአሞራ ወረዳ ነዋሪ ድርቁ በተማሪዎች፣ በነዋሪዎቻና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

“ብዙ ተማሪዎች እያቋረጡ ነው፣ በተለይ እድሜያቸው ዝቅ ያለምግብ ስለማገኙ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም፣ እንስሳት በውሀ ጥም ደክመዋል፣ 50 እና 60 የሚሆኑ ሰዎች አልጋ ላይ ነው ያሉ፣ በጣም ተጠቅተዋል፣ መልዕክታችን ለመንግስት አድርሱልን፣ በጣም ተስኖናል፣ ውሀ ጥም ሞተናል፣ ... ከሞት አድኑን... ድረሱልን” ሲሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡ በወረዳው የበዋሰን ቀበሌ ነዋሪም ድርቁ በጤና ላይም ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡ “ወደ ጤና ጣቢያ ብዙ ሰው ነው ለህክምና የሚሄደው፣ የምንጠጣው ውሀ ንጽህና የሌለው ነው” ብለዋል፡፡ 

የጃንአሞራ ወረዳ እንስሳት ሀብት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መዲና አዳነ በወረዳው ሰፊ የእንስሳት ሀብት ቢኖርም በድርቁ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት ሞተዋል፣ ሌሎች ደግሞ በከፍተኛ የመኖ እጥረት ውስጥ ናቸው ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊዋ በ20 ቀበሌዎች   223ሺህ 283 የእንስሳት ሀብት ቢኖርም በድርቁ ምክንያት 10ሺህ የሚጠጋ እንስሳት ሞቷል፣ ከ115 ሺህ በላይ እንስሳት አስቸኳይ የመኖና የመድኃኒት አቅርቦት የሚፈልጉ እንደሆነም ገልጠዋል፡፡ በመሆኑም የእንስሳት መኖና መድሃኒት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ወ/ሮ መዲና አመልክተዋል። 

የጃንአሞራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሸጋው ተሰማ ከፌደራልና ከአማራ ክልል የተወሰነ እርዳታ ቢመጣም በቂ ባለመሆኑከፍተኛ የምግብና የውሀ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል፣ የችግሩን ጥልቀት ለሚመለከተው እያቀረቡ ቢሆንም በቂ ምላሽ እንዳልተገኘ ነው ገለጡት፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል ስተዳዳሪና የዞኑ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢምረው ካሳ ተጠይቀው  ከአዲስ አበባና ከሌሎችም አካባቢዎች ለማገዝ የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩም ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈለገውን ያክል እርዳታ ማምጣት ባይቻልም ወደ ወረዳው የደረሰውን እርዳታ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ እየተደረገ አንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ 

ክልላችን ላይ ያለው የፀጥታ ችግር ሀብት በቀላሉ እንዳመጣ፣ ለተጎጂዎች እንዳደርስ፣ ትልቅ እንቅፋት የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው፣ ከአዲስ አበባም ጭምር ለመደገፍና ለማገዝ የሚፈልጉ ወገኖች የመንገዱና የፀትታው ችግር እርዳታው በተገቢው መንገድ ወደ ተረጂዎች እንዳይደርስ ትልቅ እንቅፋት ሆኖበታል፣ የፀጥታው ሁኔታ ወደ መሻሻል ሲመጣ እርዳታውን ወደ ተጠቃሚው የማድረስ ስራ ይሰራል፣ አሁንም ወደ ቦታይ የደረሰውን እርዳታ ለተጠቃሚዎች እያደረስን ነው፡፡” ከትምህርትቤቶችና ከተማሪዎች ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በተመለከተም አቶ ቢምረው የሚከተለውን ብለዋል።

ድርቅ እና ረሃብ በኢትዮጵያ
ድርቅ እና ረሃብ በኢትዮጵያ ምስል Dong Jianghui/Xinhua/picture alliance

“ከ150 በላይ ትምህርት ቤቶች በወረዳው ይገኛሉ፣ከ 57ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች አሉ፣ እያጋጠመ ያለው ችግር ተማሪዎቹ የሚመገቡት ሲያጡና የውሀ ችግርም ስላለ፣ ለሁለትና ለሶስት ቀን ትምህርት የማቋረጥና እንደገና ወደ ትምህርት ቤት የመምጣት ነገር ይታል፡፡ ይህን ችግር ለማሻሻል ከክልሉ መንግስተ ጋር በመተባበር በተለይ በጃናሞራ ወረዳ በ40 ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 7ሺህ ያህል ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ለማካሄድ ዝግጅቶች ተጠናቅቋዋል፡፡” 

በሰሜን ጎንደር ዞን 6 ወረዳዎችና 83 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ 452 ሺህ ሰዎች ለእለት እርዳታ የተዳረጉ ሲሆን 104 ሺህ የሚሆኑት ህፃናት፣ 14 ሺህ እናቶችና ነብሰጡሮች መሆናቸውን ወረዳው አስታውቋል፡፡ በዞኑ አጠቃላይ 140ሺህ እንስቱም ለከፍተኛ የመኖ እጥረት ተዳርገዋል። ከትምህርት ጋር የተያያዘውን በተመለከተ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ የእጅ ስልክ ላይ ደውየ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እንዳሳውቃቸው ከነገሩኝ በኋላ ያን ባደርግም መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ 

ዓለምነው መኮንን 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ