1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መጋቢት 18 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ መጋቢት 18 2009

በአሰልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ የሚመራው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን  አዘርባጃንን 4 ለ1 በማሸነፍ ለዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ተቃርቧል። ኢትዮጵያ በ2ኛነት ባጠናቀቀችበት የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ውድድር በአዋቂ ወንዶች እና ሴቶች እጅግ ደካማ ውጤት አስመዝግባለች።

https://p.dw.com/p/2a4Nc
Aserbaidschan - Deutschland, 26.03.2017
ምስል picture alliance/dpa/M. Guengoer

ስፖርት፤ መጋቢት 18 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ኢትዮጵያ በ2ኛነት ባጠናቀቀችበት የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ውድድር በአዋቂ ወንዶች እና ሴቶች እጅግ ደካማ ውጤት አስመዝግባለች። በታዳጊ ወንዶች በተለይ ደግሞ በሴቶች ውድድር እንደተለመደው ጥንካሬዋን አሳይታለች። የስፖርት ተንታኝ አነጋግረናል። በአሰልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ የሚመራው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን  አዘርባጃንን 4 ለ1 በማሸነፍ ለዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ተቃርቧል። በውድድሩ የጀርመን ቡድን ግቦቹን ሲያስቆጥር በልምምድ ወቅት ያለ እስኪመስል ያለብዙ ችግር ነበር። በሌላ በኩል በጀርመን ምድብ ውስጥ የምትገኘው ሰሜን አየርላንድ እንዲሁም እንግሊዝ እና  ስኮትላንድም አሸናፊ ኾነዋል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ዘንድሮም ፉክክሩ በብሪታንያ እና በጀርመን መካከል ኾኗል፤ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን እጅ ሰጥቷል። የመጨረሻ ዙር አጠቃላይ አሸናፊው ግን እኔ መኾኔ አይቀርም ብሏል። 

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከብዙ ዓመት አንስቶ በመፈራረቅ የበላይነታቸውን በሚያሳዩበት የዓለም አገር አቋራጭ ፉክክር የኢትዮጵያ አሌቲክስ ቡድን ተሳትፎ የ2ኛነት ደረጃ በማግኘት ትናንት አጠናቋል። ካምፓላ ኡጋንዳ ውስጥ በተከናወነው 42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር የኢትዮጵያ ቡድን በኬንያ በሁለት ሜዳሊያዎች ተበልጦ ነው ሁለተኛ የወጣው። 

Adidas Leichtathletik
ምስል picture alliance/dpa/B. Thissen

በታዳጊዎች እና በአዋቂዎች የግል እና የቡድን ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን 4 የወርቅ፤ 4 የብር እና 1 የነሀስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችሏል። የኢትዮጵያ ቡድን ዋነኛ ተፎካካሪ ኬንያ 4 የወርቅ፤ 5 የብር እና 3 የነሀስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአፍሪቃም ከዓለምም አንደኛ መውጣት ችላለች። የሁለቱ ሃገራት እየተፈራረቁ አሸናፊ መኾን የተለመደ መኾኑን የስፖርት አማካሪው ኤልሻዳይ ነጋሽ ይናገራል። 

ለኢትዮጵያ በታዳጊ ሴቶች የስድስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ለተሰንበት ግደይ 18 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ በመሮጥ ወርቅ ስታስገኝ፤ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሃዊ ፈይሳ ከ23 ሰከንድ በኋላ ተከትላት በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች። 

በ8 ኪሎ ሜትር የታዳጊ ወንዶች ውድድር ላይ ደግሞ አምደወርቅ ዋለልኝ 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አጥልቋል። ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ቦኔ ጩለቃ እና ወልዴ ቱፋ ተሳታፊ በሆኑበት ድብልቅ የዱላ ቅብብል ሽቅድምድም ኢትዮጵያ ኬንያን ተከትላ ሁለተኛ ወጥታለች። በአዋቂ ወንዶች የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ አባዲ ሀዲስ 3ኛ በውጣት ነሐስ አጥልቋል። በተመሳሳይ ርቀት የሴቶች ውድድር ኬንያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተከታትለው በመግባት ዓለምን አስደምመዋል። ኢትዮጵያውያቱ ከ8ና እስከ 26ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። 

አዘጋጇ ኡጋንዳ 1 ወርቅ፤ እና 2 የነሐስ ሜዳሌያዎችን በማግኘት ሦስተኛ ወጥታለች። የቱርክ፣ የባህሬን እና  የኤርትራ ቡድን በተመሳሳይ ባገኙት 1 የነሐስ ሜዳሊያ አራተኛ ደረጃ ይዘዋል።

ሩስያ ውስጥ ለሚኪያሄደው የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ የአውሮጳ ሃገራት የማጣሪያ ውድድር ጀርመን ሰፊ በሆነ ውጤት የአዘርባጃን ቡድንን አሸንፎ ግስጋሴውን ቀጥሏል። በትናንቱ የ4 ለ1 ድል በምድብ ሦስት ውስጥ የሚገኘው የጀርመን ቡድን የመጀመሪያ ግብ ተቆጥሮበታል። 

Aserbaidschan - Deutschland, 26.03.2017
ምስል picture alliance/dpa/M. Guengoer

ቡድኑ የአዘርባጃን ተጋጣሚውን ሳይንቅ ተገቢ ጨዋታ አከናውኗል ሲሉ የጀርመን መገናኛ አውታሮች የትናንቱ ጨዋታ አሰላለፍ እና እንቅስቃሴን አወድሰዋል። አሰልጣኙ እና ተጨዋቾቹ ግን እስካሁን አምስቱንም የማጣሪያ ጨዋታዎች ቢያሸንፉም በትናንቱ ጨዋታ ውጤት ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጠዋል። የቡድኑ ተሰላፊ ማትስ ሁመል ጀርመን አዘርባጃንን 4 ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ መመጻደቅ ታይቶበታል ሲል ተችቷል።

ቶማስ ሙይለር እና ተቀይሮ የወጣው ማሪዮጎሜዝ አንድ አንድ ግቦችን እንዲሁም አንድሬ ሹርለ ሁለት ግቦችን ለጀርመን አስቆጥረዋል። በተለይ አንድሬ ሹርለ ካስቆጠራቸው ግቦች ባሻገር ኳሶችን አመቻችቶ ለግብ በማቀበል ያደረገው አስተዋጽዖ ላቅ ያለ ነበር። አንድሬ ሹርለ በትናንቱ እንቅስቃሴው በአሰልጣኙም ሆነ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ተችሮታል። 

ሦስቱም ተጨዋቾች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ እምብዛም ደስታ አላሳዩም። በባኩ ስታዲየም የጀርመን ቡድንን ያስተናገደው ተጋጣሚው የአዘርባጃን ቡድን ወኔ በተቀላቀለበት መልኩ ውብ ጨዋታ ቢያሳይም፤ አጥቂዎቹም ሆኑ ተከላካዮቹ ፍጥነት እና ጥንካሬ ሲሳናቸው ተስተውለዋል። 

እንግሊዝ ሊዩታንያን 2 ለ1፤ ሰሜን አየርላንድ ኖርዌይን 2 ለ0፤ ስኮትላንድ ስሎቬኒያን 1 ለ0 አሸንፈዋል። በትናንትናው ዕለት በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ስሎቫኪያ ማልታን 3 ለ1,፤ ፖላንድ ሞንቴኔግሮን 2 ለ1አርሜንያ ካዛክስታንን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ዴንማርክ ከሩማንያ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ቼክ ሪፐብሊክ ሳንማሪኖን 6 ለ0 የግብ ጎተራ በማድረግ ልካታለች። በነገው ዕለት የደቡብ አሜሪካዎቹ ብራዚል እና አርጀንቲናን ጨምሮ፤ አውስትራሊያ፣ የመካከለኛው አሜሪካ እና እስያ ሃገራት 16  ግጥሚያዎች ይኖራሉ። 

Australien Formel 1 Grand Prix Vettel Jubel
ምስል Getty Images/R. Cianflone

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የአውስትራሊያ ሜልቦርን ግራን ፕሪ ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል አሸናፊ ኾኗል። ትናንትና በተጀመረው ውድድር የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተንን በ9 ሰከንዶች ልዩነት ያሸነፈው ሰባስቲያን በድሉ ቢደሰትም  ወደፊት ገና ብዙ ፉክክር እንደሚጠብቀው ገልጧል። ሌዊስ ሐሚልተን በበኩሉ ዘንድሮ የአጠቃላይ ውድድር ድሉ የኔ ነው ብሏል። 

58 ዙር ወይንም ለሁለት ሰአታት በሚደረገው ውድድር ሰባስቲያን ፌትል በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 1 ሰአት ከ24 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ ነው። ሌዊስ ሐሚልተን በ9.975  ሰከንድ ተበልጧል። በዚህም መሠረት አሸናፊው ሰባስቲያን ፌትል 25 ነጥብ ሲሰበስብ፤ ሌዊስ ሐሚልተን በ7 ይከተለዋል። 

በሦስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የመርሴዲስ አሽከርካሪው ቫልተሪስ ቦታስ ነው። የአምናው አጠቃላይ ውድድር አሸናፊ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ከፎርሙላ አንድ ራሱን ባሰናበተበት የዘንድሮ ውድድር ከዋነኛ ተፎካካሪዎች አንዱ ይኾናል ተብሎ የተጠበቀው ፈርናንዶ አሎንሶ ያለምንም ነጥብ ውድድሩን አቋርጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ