1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መጋቢት 2 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2011

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ቡድን ከሦስት ሳምንት በኋላ በአፍሪቃ የእጅ ኳስ ዋንጫ ውድድርር ኢትዮጵያን ወክሎ ለሁለተኛ ጊዜ ይፎካከራል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪነቱን ለማንቸስተር ሲቲ ያስረከበው ሊቨርፑል በጀርመን ቡድንደስ ሊጋ መሪነቱን ከተረከበው ባየር ሙይንሽን ጋር ለመጋጠም ወደ ባየርን ያቀናል።

https://p.dw.com/p/3EoXe
Fußball Champions League - Liverpool vs Bayern München
ምስል Reuters/P. Noble

ሣምንታዊየስፖርት ዘገባ

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ቡድን ከሦስት ሳምንት በኋላ በአፍሪቃ የእጅ ኳስ ዋንጫ ውድድርር ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ ይፎካከራል።  የቡድኑ አሰልጣኝ፦ የእጅ ኳስ በኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ የስፖርት አይነቶች ተገቢውን ትኩረት አላገኘም፤ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪነቱን ለማንቸስተር ሲቲ ያስረከበው ሊቨርፑል  በጀርመን ቡድንደስ ሊጋ መሪነቱን ከተረከበው ባየር ሙይንሽን ጋር ለመጋጠም ወደ ባየርን ያቀናል። መሪነቱን የተቆናጠጠው ማንቸስተር ሲቲ በቡንደስሊጋው ወራጅ ቃጣና ውስጥ ላለመግባት መከራውን የሚበላው ሻልከን በሜዳው ያስተናግዳል። ነገ እና ከነገ በስተያ በአጠቃላይ አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ።

ለአራት ጊዜያት የምሥራቅ አፍሪቃ ዋንጫዎችን አስገኝተዋል። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪቃ ደረጃ ለመወዳደር ከሦስት ሳምንት በኋላ ቡድናቸውን አስከትለው ወደ ሞሮኮ ያቀናሉ። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሙሉጌታ ግርማ። የእጅ ኳስ ስፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በተመልካቹም፤ በስፖርት ጋዜጠኞቹም ብሎም በመንግሥት ደረጃም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ። ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል።

የእጅ ኳስ ስፖርት እንደሌላው ስፖርት ትኩረት ከተሰጠው ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል፤ ሕዝቡም በየሳምንቱ መጨረሻ ትንሿ ስታዲየም እየመጣ ድጋፍ ቢሰጣቸው ሞራላቸው እንደሚነቃቃ ተናግረዋል። ከኅብረተሰቡ እና ከመንግሥት ትኩረት ባሻገር በተለይ ደግሞ ጋዜጠኞች በቂውን ሽፋን ቢሰጧቸው ከስህተታቸው እየተማሩ ለበለጠ ውጤት እንደሚበቁ አክለዋል።

Deutschland | Handball WM | Frankreich - Dänemark
የእጅ ኳስ ውድድር በምዕራቡ ዓለም ተወዳጅ ሲኾን በርካታ አድናቂ አለውምስል picture-alliance/dpa/M. Wolf

ሻምፒዮንስ ሊግ

ነገ እና ከነገ በስተያ አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአንድ ነጥብ ብልጫ ሊቨርፑልን ቀድሞ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ የጀርመኑ ሻልከ ቡድንን በሜዳው ነገ ያስተናግዳል። ሻልከ በቡንደስ ሊጋው ወራጅ ቃጣና 14ኛ ጠርዝ ላይ ተጠግቶ ፈጽሞ ላለመውረድ ይውተረተራል።  

ቀደም ሲል በሜዳው 2 ለ3 የተሸነፈው ሻልከ በማንቸስተር ሲቲ ሜዳ ተጋጥሞ ያሸንፋል ማለት ይከብዳል። በአሰልጣኝ ዶሜኒኮ ቴዴስኮ የሚመራው ሻልከ ለማሸነፍ የ3 ለ2 ሽንፈቱን በመልሱ ጨዋታ በቅድሚያ ማካካስ ይጠበቅበታል።

በእለቱ በተመሳሳይ ሰአት ምሽት ላይ በሚኖረው ሌላኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ፦ የጣልያኑ ባለድል ጁቬንቱስ ክሪስትያኖ ሮናልዶን ከፊት አሰልፎ የስፔኑ ኃያል አትሌቲኮ ማድሪድን ለመበቀል ተሰናድቷል። በመጀመሪያው ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ በሜዳው  ጁቬንቱስ ቱሪንን 2 ለ0 አሸንፎታል። ዋንዳ ሜትሮፖሊታን ስታዲየምን ያስቦረቊት አትሌቲኮ ማድሪዶች በአሊያንትስ ስታዲየም እጅ የሚሰጡ አይመስሉም። በእርግጥ በሪያል ማድሪድ የጨዋታ ዘመኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ላይ በ31 ግጥሚያዎች 22 ግቦችን ካስቆጠረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነገ ማታ እጅግ ብዙ ይጠበቃል።  የጁቬንቱሱ አለኝታ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለሪያል ማድሪድ ተሰልፎ አትሌቲኮ ማድሪድ ላይ ካስቆጠራቸው 22 ግቦች ሦስቱ ሔትትሪክ ናቸው።

München vor dem Champions League Finale 2012
የባየር ሙይንሽኑ አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ውጫዊ ገጽታምስል picture-alliance/dpa

በቡንደስ ሊጋው ቅዳሜ እለት ቮልፍስቡርግን 6 ለ0 አደባይቶ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በ57 ነጥቡ በቀዳሚነት ጉብ ያለው ባየር ሙይንሽን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫውን ለመጨበጥ ከሚሟሟተው ሊቨርፑል ጋር  ረቡዕ ማታ ይጋጠማል። ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ግጥሚያ ትናንት በርንሌይን 4 ለ2 ድል አድርጎ በ73 ነጥብ 2ኛ ደረጃ  ይዟል። በማንቸስተር ሲቲ በ1 ነጥብ ይበለጣል። በቡንደስሊጋው የሁለተኛ ደረጃ የያዘው ዶርትሙንድ የቀድሞ አሰልጣኝ የነበሩት ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ ተፋላሚያቸው ባየር ሙይንሽንን በቅርበት ማወቅ ብቻ ሳይኾን ፈተናውም ነበሩ። እናም በረቡዕ ግጥሚያ ለባየር ሙይንሽን ብርቱ እና አስቸጋሪ ተጋጣሚ ኾነው መቅረባቸው አይቀርም። 

በእለቱ በተመሳሳይ ሰአት ምሽት ላይ የስፔኑ ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ኦሎምፒክ ሊዮን ጋር ይጋጠማል።  የብራዚሉ አጥቂ ኔይማር ከባርሴሎና ወደ ፈረንሳዩ ፓሪ ሴንጄርሜን በከፍተኛ ክፍያ የተዘዋወረበት ሒደት ጥያቄ አስነስቷል። «ኤል ሞንዶ» የተሰኘው ዕለታዊ ጋዜጣ ዛሬ እንደዘገበው ከኾነ፦ ኔይማር ክብርወሰን በሰበረው ከፍተኛ የዝውውር ክፍያ ካገኘው ገንዘብ ግብር ለስፔን መንግሥት በተገቢው መንገድ ከፍሎ እንደኾን እየተጣራ ነው ብሏል።

በሌላ ዜና የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ኢካይ ጉይንዶዋን በእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ የመቆየት ኹኔታው አጠራጣሪ መሆንኑን ይፋ አድርጓል። ምንም እንኳን በቡድኑ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር እስከ 2020 ድረስ ለመቆየት ውል ቢፈራረምም ከአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር የወደፊት እጣውን ለመወሰን መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ