1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ግንቦት  26 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2011

ለ6 ተከታታይ ጊዜያት የድል ጫፍ ላይ ደርሰው በስተመጨረሻ ስለተሳካላቸው የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የአሰለጣጠን ፍልስፍና እና ሰብእና የእግር ኳስ አፍቃሪያን አድናቆት ችረዋል። ብራዚላዊው አጥቂ ኔይማር የአስገድዶ መድፈር ክስ ቀርቦበታል። የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንደርታ ቡድኖች ጨዋታ በፀጥታ ስጋት የተነሳ መከናወን አልቻለም። 

https://p.dw.com/p/3JlqL
Bildergalerie Sonntag in der Welt
ምስል picture-alliance/dpa/B. Coobs

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በበርካቶች ዘንድ እጅግ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሻምፒዮን ሊግ ፍጻሜ በጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በሚመራው ሊቨርፑል ድል መጠናቀቊ የስፖርት አፍቃሪዎች መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። ለስድስት ተከታታይ ጊዜያት የድል ጫፍ ላይ ደርሰው በስተመጨረሻው ስለተሳካላቸው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የአሰለጣጠን ፍልስፍና እና ሰብእና  በመላው ዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእግር  ኳስ አፍቃሪያን አድናቆት ችረዋል። ብራዚላዊው አጥቂ ኔይማር የአስገድዶ መድፈር ክስ ቀርቦበታል። የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንደርታ ቡድኖች ጨዋታ በፀጥታ ስጋት የተነሳ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ መከናወን አልቻለም። 

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ፍልሚያ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ዋንጫቸውን ያገኙት የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ «ታሪክ ሠሪ» ተሰኝተዋል። አንዳንድ የአውሮጳ ጋዜጦች «ንጉሥ ክሎፕ» የሚል ማዕረግ ሰጥተዋቸዋል። የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ዛሬ ከሰአት ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽ ሊግ ኮሚቴ ጨዋታው ናዝሬት ወይንም አዳማ ከተማ ውስጥ ይካሄድ ማለቱን የኢትዮጵያ ቡና አለመቀበሉን በጋዜጣዊ መግለጫው የታደመው የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ በስልክ ገልጦልናል። 

Äthiopien PK Coffee Club
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ቡድን መግለጫ በዋቢሸበሌ ሆቴልምስል DW/O. Tadele

ሊቨርፑል ማብቂያ የሌለው በሚመስል ፈንጠዝያ ተውጣለች። የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ለሻምፒዮንስ ሊግ ድል በመብቃታቸው ዓለም ውዳሴ እያቀረበላቸው ነው። ሊቨርፑል ኤኮ የተባለው ጋዜጣ፦ «ሊቨርፑል ዳግም የአውሮጳ ንጉሥ ኾኗል» ሲል አትቷል። አሰልጣኝ ዩርገን ክሎፕ አብረዋቸው የተጓዙትን እና በመላው ዓለም የሚገኙ የቡድኑ ደጋፊዎችን ህልም እውን አድርገዋል። በ4 ዓመታት ብቻ ሊቨርፑልን የአውሮጳ ተፈሪ ቡድን አድርገውታል» ሲል ዘግቧል።

ዴይሊ ሜይል በበኩሉ፦ «ሊቨርፑል የዘንድሮ የውድድር ዘመኑን በአጠቃላይ የ2018ቱን መከፋት ለማጥፋት ነበር ሲሠራ የከረመው። ክሎፕ ከእንግዲህ በፍጻሜው ኹለተኛ አጠናቃቂ ብቻ ተብለው ሊሰየም አይችልም» ሲል ጽፏል።

የስፔኑ ማርካ፦ «ስታዲየም ውስጥ ድንቅ ድባብ ግን አነስ ያለ እግር ኳስ ነበር» ሲል የጨዋታውን ሳቢ አለመኾን ገልጧል። «ቫን ጂክ እና አሊሰን ቤከር የከፋውን ባያስወግዱ ኖሮ ቶትንሀም ሆትስፐሮች የተሻለ በተገባቸው ነበር» ብሏል። «ክሎፕ አሁን ታሪክ ሠርቷል። ዩርገንዬ አንድ ጊዜ ስፔን ውስጥ አሰልጣኝ ኾነህ ማየቱ ቢፈቀድልን ምንኛ ደስ የሚል ነበር» ሲል ውዳሴ ያቀረበው ደግሞ ኤ ኤስ የተባለ ጋዜጣ ነው።  

UEFA Champions League Triumphfahrt FC Liverpool
ቢያሸንፉም ቢሸነፉም ፈገግታ ከፊታቸው የማይለየው የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕምስል picture-alliance/dpa/B. Coombs

የጣልያን ጋዜጦች በበኩላቸው አድናቆታቸውን ሰንዝረዋል። ጋዜታ ዴል ስፖርት ለአንዳች ፍንዳታ የሚውለውን «ቡም» የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በመውሰድ «ሊቨርቡም» ብሎታል ሊቨርፑልን። «በአውሮጳ ፍጻሜ ለሁለት ጊዜ ድል ከተነሳ በኋላ ክሎፕ አኹን የሚገባውን ድል እያጣጣመ ነው» ሲል ጽፏል። «ባለፉት ዓመታት የነበሩት የሽንፈት ቁስሎች ታክመዋል» ሲል አክሏል።

ኮሪዬሬ ዴል ስፖርት ቀጣዩን ጽፏል። «ንጉሥ ክሎፕ፤ ይኽን ቅጽበት ለረዥም ጊዜ ሲያልመው ነበር። ማሸነፍ ይገባዋል። ላለፉት ስድስት ጊዜያት በፍጻሜ ያጣቸውን ድሎች ላለመድገም ዘንድሮ ዕድል ከጎኑ ነበረች» ሲል የንግሥና ሞገስ አጎናጽፏቾዋል።

ቱቶስፖርት፦ «ሳላህ እና ኦሪጂ ስታዲየሙ ላይ ገነው ወጥተዋል። ጨዋታው በእርግጥ ለማየት የማይስብ ነበር። ተጋጣሚው በቀያዮቹ የመጀመሪያ ደቂቃ ግብ ተጽዕኖ ስር ወድቋል። የፖቼቲኖ ወታደሮች የሚቻላቸውን ተፋልመዋል ኾኖም ቫን ጂክ እና ጓዶቹ እያንዳንዷን የጨዋታ ስፍራ ዘግተውት ቆይተዋል። ግብ ጠባቂው አሊሰን ወሳኝ ሰው ነበር» በማለት ጽፏል።

የጀርመኑ ዙድ ዶየቸ ሳይቱንግ ጋዜጣ፦ «እጅግ ብዙ ገንዘብ ተገቢው ቦታ ላይ ፈሷል» በሚል ርእስ ባስነበበው ዘገባው፦ ከባርሴሎና 3 ለ0 ተሸንፎ በመልስ ጨዋታው አንፊልድ ላይ 4ለ 0 ድል ማድረግ ስኬቱ ከየት መጣ ሲል ይጠይቅና መልሱን ሲሰጥ በደንብ ማቀዳቸውና አሊሰን ቤከር እና ቪርጂል ቫን ጂክ ምርጥ ኾነው መገኝታቸው ነው ይላል።

ሊቨርፑል በ2018 አዲስ ዓመት ቪርጂል ቫን ጂክን ከሳውዝ ሀምፕተን ያመጣው በ84,5 ሚሊዮን ዩሮ ነው። እናም ድፍረት በተሞላበት ውሳኔ ይህን የዓለማችን ምርጥ ተከላካይ ተጨዋች አስመጥተው ባያሸንፉ ኖሮ በቅጽበት ጥርስ ውስጥ ይገቡ ነበር ሲል ተንትኗል አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፕን በተመለከተ።

UEFA Champions League Triumphfahrt FC Liverpool
ደማቅ አቀባበል፦ ሊቨርፑሎች የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ይዘው ወደከተማቸው ሲገቡ ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Coombs

ክሎፕ እንደ ፓሪስ ሳንጄርሜን አይነት ቡድኖች በአጥቂ ብቻ የሚተማመኑ አይደሉም። ባለፈው ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የዓለማችን ምርጥ ግብ ጠባቂ ስላልነበራቸው ለሽንፈት መዳረጋቸውን ጠንቅቀው ያውቁታል። ሲሞን ሚኞሌት ሎሪስ ካሪዮስን እየቀየረ ነበር የሚሰለፈው። ሊቨርፑል ተገቢው ቦታ ላይ ገንዘቡን አፍስሶ ለሌላ አላወጣም። ይልቁንስ እንደ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ያሉ ወጣት ተጨዋቾች ላይ እምነት ጥሏል። በአንጻሩ ቶትንሀም ሆትስፐር እያንዳንዷን ሳንቲም ተጨዋች ላይ ሳይሆን አዲስ ስታዲየም ግንባታ ላይ ነው ያዋለው።

ጨዋታ በተጀመረ አፍታም ሳይቆይ ማኔ ብልጠት በታከለበት መንገድ የሲሶኮ የተዘረጋ ክንድ ላይ ኳሷን ልኮ ፍጹም ቅጣት ምት አስገኘ። ዋንዳ ሜትሮፖሊታን በሊቨርፑል ደጋፊዎች ፌሽታ ተናጠ። ስፐርስ ፈጣን ምላሽ ለመሰጠት ቢጥርም የሊቨርፑል የተከላካይ አጥርን መደርመስ አልተሳካለትም። ሊቨርፑል መልሶ በማጥቃት በ17ኛው ደቂቃ አሌክሳንደር አርኖልድ በግቡ አግዳሚ በኩል የላካት ኳስ ትጠቃሽ ናት።

ከረፍት መልስ ቶትንሀም አይሎ ነበር የገባው። ዴሌ አሊ 54ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ቅጣት ክልል ውስጥ ከሽፎበታል። ኹኔታው ዬርገን ክሎፕ በ58 እና 62 ደቂቃ ላይ ተቀያሪ ተጨዋቾችን ለማስገባት አስገድዶታል። በፊርሚኖና ዊጅናልዱም ምትክ ኦሪጂና ሚልነርን ማሰለፋቸው ጠቅሟቸዋል።

UEFA Champions League Triumphfahrt FC Liverpool
የሊቨርፑል ተጨዋቾች የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ይዘው በከተማው ሲዘዋወሩምስል Reuters/P. Noble

በ66ኛው ደቂቃ ላይ ቶትንሀሞች የእስራኤሉ አጥቂ ሉቃስ ሙራን ሲያሰልፉ ሊቨርፑሎች ጭራሽ ወደ መከላከሉ ለማዘንበል ተገደዋል። 69 ደቂቃ ላይ ሚልነር በአግዳሚው በስተቀኝ የላካት አደገኝ ኳስ ለጥቂት ነበር ግብ ከመኾን ያመለጠችው። ከዐሥር ደቂቃ ግድም በኋላ ቲትንሀም ርቱ ሙከራዎችን በማድረግ ሊቨርፑሎችን አስጨንቀዋል። ሶን እና ሉቃስ በ79 እና 80 ደቂቃ ላይ በተከታታይ ግብ ክልል ውስጥ አስጨናቂ ሙከራ አድርገዋል። 86ኛው ላይ ሉቃስ ከርቀት ግቧን የሳተች ሙከራ አድርጓል። 87ኛው ደቂቃ ላይ ግን የቀድሞ የቮልፍስቡርግ አጥቂ ኦሪጂ የሊቨርፑልን ድል የደመደምች ግብ አስቆጥሯል። በዚህም ድል ቀያዮቹ አሁን በሻምፒዮንስ ሊግ ከሪያል ማድሪድ እና ኤሲ ሚላን ቀጥለው በ6 ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል። ሪያል ማድሪድ 13፤ ኤሲ ሚላን 7 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የፍሥጻሜ ጨዋታዎችን አሸንፈዋል።

የቀድሞ የማይንትስ እና የዶርትሙንድ አሰልጣኝ ክሎፕ በዓለም አቀፍ ውድድር የመጀመሪያ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ 6 ጊዜ ለፍጻሜ ደርሰው መሸነፋቸውም እንዲያከትም አድርገዋል። ኪከር የተሰኘው የጀርመን ድረገጽ ጋዜጣ ሪያል ማድሪድ በ2016 እና 2018 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ወስዷል፤ እናስ ሊቨርፑል ይህን ድሉን ወደፊት ማስጠበቅ ይችል ይኾን በሚል ላቀረበው ጥያቄ ግማሽ በግማሽ መላሾች አዎ ወይንም አይደለም ብለዋል።

Neymar Brasilien Karneval
የፈረንሳዩ ፓሪ ሴንጀርሜን ኮከብ ብራዚላዊው ኔይማርምስል Getty Images/M. Pimentel

የሻምፒዎንስ ሊግ ፍጻሜ በሚከናወንበት ወቅት አንድ አሳዛኝ ዜናም ተሰምቷል። የቀድሞው የሪያል ማድሪድ እና የአርሰናል አጥቂ ጆዜ አንቶኒዮ ሬይስ በመኪና አደጋ ሕይወቱ መጥፋቱ ተዘግቧል። በፍጻሜ ጨዋታ ምሽቱ የኅሊና ጸሎት ተደርጓል። 

የፈረንሳዩ ፓሪ ሴንጀርሜን ኮከብ ብራዚላዊው ኔይማር ላይ የአስገድዶ መድፈር ክስ ተከፍቶበታል። የኔይማር አባት ኾን ተብሎ የተደረገ ወጥመድ ነው ብለዋል። አስገድዶ መድፈር እንደተፈጸመባት የተናገረችው ሴት ድርጊቱ ሆቴል ክፍል ውስጥ ግንቦት 7 ቀን መፈጸሙን ተናግራለች። በወቅቱ ኔይማር «ሰክሮ » እንደነበር ድርጊቱም ሆቴል ውስጥ ከደረሰ ከ20 ደቂቃ በኋላ መፈጸሙን ገልጣለች። ብራዚል ሳኦ ፖሎ ከተማ ውስጥ ፖሊስ ለሮይተርስ የዜና ምንጭ እንደተናገረው የአስገድዶ መድፈር ድርጊቱ ተፈጸመ የተባለው ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ውስጥ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ