1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ታሪክ

ሻርለት ማቄኬ፤ ፋናወጊዋ ደቡብ አፍሪካዊት ታጋይ

ሐሙስ፣ ሰኔ 7 2010

ደቡብ አፍሪካውያን የሀገራቸውን ልጅ ሻርለት ማኒያ ማቄኬን “በገነት ያለ መልዐክ ያለውን ድምጽ አድሏቸዋል” ይሏቸዋል። ዘፈን ህይወታቸው የነበረው ማቄኬ ዓለምን የመዞር ዕድል ያጋጠመውን የዝማሬ ቡድን (ኳየር) ከተቀላቀሉ በኋላ ያልተጠበቀ ነገር ገጠማቸው። ያ አጋጣሚ “የጥቁሮች የነጻነት እናት” የሚል ስያሜ ወዳሰጣቸው ትግል ህይወታቸውን መርቶታል።

https://p.dw.com/p/2ySSK
Charlotte Maxeke
ምስል Comic Republic

ሻርለት ማቄኬ፤ ፋናወጊዋ ደቡብ አፍሪካዊት ታጋይ

ሻርለት ማኒያ ማቄኬ ሁሌም ቢሆን በጥልቅ ስሜት የምታቀነቅን ድምጻዊ ነበረች። በጎርጎሮሳዊው 1981 ዓ.ም. “የነባር አፍሪካዊ የዝማሬ ቡድን” ከተሰኘው ስብስብ ጋር ሙዚቃ ለማቅረብ ደቡብ አፍሪካን ለቅቃ ተጓዘች። የዝማሬ ቡድኑ መጀመሪያ በብሪታንያ፣ ለጥቆ በዩናይትድ ስቴትስ ባሉ ተመልካቾች ከፍተኛ ዝና አተረፈ። ሆኖም ለድምጽውያኑ ነገሮች እንዳማሩ አልቀጠሉም። አውሮፓዊው የቡድኑ መሪ በዝግጅቶቻቸው ያሰባሰቡትን ገቢ ይዞ እብስ በማለቱ ድምጻውያኑ በአሜሪካ መሄጃ አጥተው ለመቀመጥ ተገደዱ። 

አጋጣሚ ያመጣው የዕጣ ፈንታ ነገር ማቄኬን በአፍሪካ ወንጌላዊ ተልዕኮ ከነበረው ሰው ጋር ያገጣጥማታል። ወንጌላዊው ማቄኬን ዊልበርፎርስ በተሰኘው ዩኒቨርስቲ እንድትማር ይጋብዛታል። ዩኒቨርስቲው በአሜሪካ ውስጥ ቀደምት ከሚባሉ የጥቁር አሜሪካውያን ኮሌጆች አንዱ ነበር። በሀገሪቱ የተከበረ ስም ካላቸው አፍሪካዊ አሜሪካዊ ምሁራን መካከል የተወሰኑቱ የተማሩት በዚያ ኮሌጅ ነው።

Charlotte Maxeke
ምስል Comic Republic

በኮሌጁ ትምህርቷን ስትከታተል የቆየችው ማቄኬ በጎርጎሮሳዊው 1901 ዓ.ም. የዩኒቨርስቲ ዲግሪ በማግኘት የመጀሪያዋ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ እንስት ሆነች። ማቄኬ ወደ ሀገሯ ስትመለስ ከዲግሪዋ የላቀ ነገር ሰንቃ ነበር። በደቡብ አፍሪካ ያሉ ጥቁሮችን እና ሴቶችን ሁኔታ ለማሻሻል ታጥቃ ተነሳች። ለዚህ ውሳኔዋ መነሻ የሆኑት እውቅ አፍሪካዊ አሜሪካዊ ምሁር እና መምህሯ የነበሩት ደብሊው. ኢ. ቢ ዶቦይስ ናቸው። ደቡብ አፍሪካዊቷን ጋዜጠኛ ዙቤዳ ጃፋርን እኚያን ምሁር እንዲህ ይገልጿቸዋል።

“ደብልዩ. ኢ. ቢ ዶቦይስ  በ19ኛው ክፍለዘመን የነበሩ ሰው ናቸው። ፈላስፋ፣ ፖለቲካዊ አሰላሳይ እና በፓን-አፍሪካኒዝም ከፊት ለፊት የሚሰለፉ ነበሩ። ስለ እርሷ አወዳሽ ገለጻዎችን ተጠቅመው ጽፈዋል” ትላለች ጋዜጠኛዋ።    

ዙቤዳ እንደማቄኬ ያሉ በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ውስጥ የፋና ወጊነት ሚና የነበራቸውን ሴቶች የማስተዋወቅ ሚና ለራሷ ሰጥታለች። ሰዎች ስለ እነዚህ ሰዎች ትግል የሚያዉቁት በጣም ጥቂቱን ነው ትላለች ጋዜጠኛዋ። እነዚህ ሰዎች እኩል መብት እንዲኖር ከ1900ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ሲታገሉ የነበሩ ናቸው ስትል ታክላለች።     

“የዚያን ጊዜ ሴቶች በጥቅሉ ተገቢውን ቦታቸውን አላገኙም። እርሷን  በተለይ የተመለከተ ብቻ  ሳይሆን በአጠቃላይ ሴቶችን ሁሉ ነው። የትግል ታሪኮች የሚያጠነጥኑት በወንዶች ዙሪያ ነው። ከዚያ በኋላ በ1950ዎቹ ተሳትፎ የነበራቸውን ሴቶች አካትቶ ይነገር ነበር። የዚያ ምክንያቱ የሚመስለኝ ለትውስታችን ቅርብ መሆኑ ነው” ትላለች።      

Charlotte Maxeke
ምስል Comic Republic

ማቄኬ በውሁዳኑ ነጮች ወደምትመራው ሀገሯ ስትመለስ ጥቁሮችን በተገለለ ቦታ የማድረጉ አካሄድ እየጨመረ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1912 ዓ.ም. ሻርለት ማቄኬ “የደቡብ አፍሪካ ነባር ተወላጆች ድርጅት ምስረታ ላይ ተሳተፈች። ያ ድርጅት በስተኋላ “የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ” (ANC) ተብሏል። ሴቶች በድርጅቱ ውስጥ በአባልነት እንዲሳተፉ ስታግባባ የቆየችው ማቄኬ ጥረቷ ባለመሳካቱ በዚያው ዓመት “የባንቱ የሴቶች ሊግ” የተሰኘውን ድርጅት መሰረተች። ከሊጉ ዋና እንቅስቃሴዎች መካከል ጥቁር ሴቶች የማለፊያ ፍቃድ እንዲይዙ የሚያስገድደው ህግን መቃወም ነበር። 

በስራቸው አንቱታን ያተረፉት ማቄኬ በህይወታቸው በሙሉ አፍሪካውያን በተለይም ደግሞ ሴቶች በራሳቸው ጉዳዩች የማዘዝ መብት እንዲኖራቸው ታግለዋል። የትምህርትን ጠቀሜታ በተመለከተ ምን አይነት እምነት እንደነበራቸው በግለ-ታሪካቸው ላይ በግልጽ ተቀምጧል።

“የራሳችን ነገሮች ራሳችን መስራት አለብን የሚል የጠነከረ እምነት ነበራቸው። ታውቃለህ! የራሳችንን ትምህርት ቤቶች እንድናንጽ እና እንድሰራ ይፈልጉ ነበር። እናም ራሳቸው ትምህርት ቤት ገነቡ። በመንደር ውስጥ የነበሩ አዳጊ ወንድ እረኞችን ያስተምሩ ነበር። እነዚያን ነገሮች ሁሉ አድርገዋል። በጉአቴንግ ግዛት ኤቫቶን ውስጥ ትምህርት ቤት አለ።  በዚያ ጥቁር አስተማሪዎች ብቻ ነበር የሚያስተምሩት - አፍሪካውያን አሜሪካውያን እና ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች። አሁንም እንደዚያው ነው” ስትል ዙቤይዳ የማቄኬን አስተዋጽኦ ትዘክራለች። 

Charlotte Maxeke
ምስል Comic Republic

የማይናወጥ የሞራል ልዕልና፣ ድፍረት እና ጽናት ያልተለየው ህይወት የነበራቸው ሻርለት ማኒያ ማቄኬ ያረፉት በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 1939 ዓ.ም. በጆሃንስበርግ ነበር። ከእርሳቸው ህልፈት አስር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ የሀገሪቱ አብዛኛው ህዝብን በሚሸፍኑት ጥቁሮች ላይ የጭቆና እና የቀለም ልዩነትን የሚደነግገውን የአፓርታይድን ፖሊሲ አጸናች። በማቄኬ ፊት አውራሪነት ተጀምረው የነበሩ ጥረቶችም የጠፉ መሰሉ። ነገር ግን እርሳቸው በመዝራት የተሳተፉበት የአልበገር ባይነት ዘር ቀጣይ የደቡብ አፍሪካ ትውልዶችን የሚያነቃቃ ከመሆን አልተገታም።    

ጃኪ ዊልሰን/ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ          

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.