1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዕርቀ ሰላም ለማውረድ በአሜሪካ ድርድር

ረቡዕ፣ ሰኔ 27 2010

ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመነጋገር ከሶስት ሳምንት በኋላ ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመጀመሪያ ፕሮግራማቸው በአሜሪካ የሚገኙትን በውጭ ያለው ሲኖዶስ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ መርቆሪዮስ እና የሲኖዶስ አባላትን ማነጋገር እንደሆነ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእርቀሰላሙ መጨረሻ ተገኝተውም የመልካም ምኞታቸውን ያስተላልፋሉ ተብሏል

https://p.dw.com/p/30qYQ
Äthiopien Addis Abeba Pressekonferenz Premierminister Abiy Ahmed
ምስል privat

ዶክተር ዐብይ በአሜሪካን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭውን ሲኖዶስ አባላት ያነጋግራሉ

በሀገር ውስጥ እና በውጭ በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ በመጪው ሐምሌ 12 በአሜሪካ ድርድር ማድረግ እንደሚጀመር ዛሬ ይፋ ተደረገ።  በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል እርቅ ለማውረድ በአውሮፓ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ የኮሚቴው አባላት ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ጽህፈት ቤቱን ቤልጂየም ያደረገው 23 አባላት የሚገኙበት ኮሚቴ የአውሮጳውን ኮሚቴ የሚመሩት መላዕከ ህይወት ሀረገወይን ብርሃኑ የሚባሉ አባት እንደሆነ ተገልጿል። በአዲስ አበባ የሚገኘውና ሰባት አባላት ያሉበትን ኮሚቴ የሚመሩት ደግሞ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ናቸው ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ያለውን ኮሚቴ ጠርተው ለዕርቀ ሰላሙ ያላቸውን መልካም ምኞት መግለጻቸውን የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ብርሃኑ ተድላ ተናግረዋል። 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ማለት ሀገር ማለት ነው። ቤተክርስቲያኑ ሰላም ስትሆን ሀገር ሰላም ይሆናል። እናንተ የይቅርታው የሰላሙ ተምሳሌት መሆን አለባችሁ ብለው ለኮሚቴው ዕውቅና ሰጥተዋል” ሲሉ አቶ ብርሃኑ በዛሬው ጋዜጣ መግለጫ አስረድተዋል። እርቀ ሰላሙን የሚያካሄደው ኮሚቴ ሐምሌ 11 ከኢትዮጵያ እንደሚነሳ በመግለጫው ተጠቁሟል። ለዕርቀ ሰላሙ ድርድር ከኢትዮጵያው ሲኖዶስ በኩል ሶስት ብጹዓን አባቶች የተመደቡ ሲሆን የአሜሪካ አቻውም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ብጹዓን አባቶች እንደሚያሳትፍ ተነግሯል። ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመነጋገር ከሶስት ሳምንት በኋላ ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚያ እንደደረሱ የመጀመሪያ ፕሮግራማቸው በአሜሪካ የሚገኙትን በውጭ ያለው ሲኖዶስ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ መርቆሪዮስ እና የሲኖዶስ አባላትን ማነጋገር እንደሆነ ተገልጿል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእርቀሰላሙ መጨረሻ ተገኝተውም የመልካም ምኞታቸውን ያስተላልፋሉ 

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ 

አዜብ ታደሰ 

አርያም ተክሌ