1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመጦመር ህይወትን መምራት ይቻላልን?

ዓርብ፣ ሐምሌ 13 2010

በወጣትነት ከሚዘወተሩ ልምዶች አንዱ የዕለት ውሎዎችን እየተከታተሉ የሚመዘግቡበት ደብተር ማዘጋጀት ይጠቀሳል። የተወሰኑ ወጣት ኬንያውያን ከትራስ ስር የሚሸሽጓቸውን የዕለት ውሎ መመዝገቢያዎችን ትተው ስሜቶቻቸውን እና ሀሳቦቻቸውን ከዓለም ጋር ወደሚካፈሉበት የጡመራ ዓለም ፊታቸውን አዙረዋል።

https://p.dw.com/p/31msg
Kenia Afrika Fashion Blogger Silvia Njoki
ምስል privat

ኬንያውያን ወጣቶች ጡመራን እንደ ስራ ይዘውታል

ጠዋት አንድ ሰዓት ነው። የኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ነዋሪዎች በስራ ገበታቸው ላይ በጊዜ ለመገኘት እየተጣደፉ ነው። ጨፍጋጋ የሆነው ከተማይቱ የአየር ጸባይ ግን ለስራ የሚጋብዝ አልሆነም። ለወር ያህል እንደሆነው ሁሉ ዛሬም እየዘነበ ነው። 

በናይሮቢ ዝናብ ጠብ ሲል ሁሉም ነገር ባለበት ቀጥ ይላል። የመጓጓዣ ዋጋዎች ያሻቅባሉ። በሚጨናነቀው ትራፊክ መላወሻ ማግኘት የማይታሰብ ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ከስራ የሚደረሰው አንድም አርፍዶ አሊያም በዝናብ ርሶ ነው። በርካቶች እኒህን በመሰሉ ቀናት ወደስራ ከመሄድ ይልቅ በቤታቸው ሆነው መስራትን ይሻሉ። የዲጂታል ቴክኖሎጂ ወዳድ ጥቂት ኬንያውያን ያለከልካይ ይህን ለማድረግ የኬንታደሉ ሆነዋል። ሲልቪያ ንጆኪ ከጥቂቶቹ መካከል አንዷ ናት። የፋሽን ጉዳዮችን የምትከትብበት በስሟ የሚጠራ ጦማርን ከቤቷ ሆና ታንቀሳቅሳለች። 

ሲልቪያ ዩኒቨርስቲ ገብታ ያጠናችው የምግብ ሳይንስን ነው። በሙያዋ መስራት ጀምራ የነበረ ቢሆንም ከአንድ ዓመት በላይ መዝለቅ አልቻለችም። በስራዋ ደስተኛ አለመሆኗን ስትረዳ ስራዋን ለቅቃ ፋሽን ለማጥናት ተነሳች። “ቀኑን ሙሉ በቤተሙከራ የሚደረግ ጋዋን መልበስ ነበረበኝ። ሜክአፕ ተቀብቼ መምጣትም ሆነ የጆሮ ጌጥ ማድረግ አልችልም ነበር። የምግብ ጥራት እና ደረጃ ደንብ ስለሚያስገድድ ጸጉሬንም መሸፈን ነበረብኝ። ምንም ደስተኛ አልነበርኩም። ለራሴ ህይወት እኮ አጭር ነች፤ ደስተኛ መሆን አለብኝ አልኩ” ትላለች ሲልቪያ።   

Kenia Afrika Fashion Blogger Silvia Njoki
ምስል privat

የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ሲልቪያ የፋሽን ትምህርትን ለመማር እስከዚያን ጊዜ ድረስ ያጠራቀመችውን ገንዘብ ሁሉ ሰብስባ ወደ ብሪታንያ አቀናች። በለንደን ባለ የበጋ ፋሽን ትምህርት ቤት የነበራትን ቆይታ ስታጠናቅቅ ወደ ኬንያ ተመለሰች። ያኔ ሁሉም ነገር ትክክለኛ ቦታውን ያዘ።  ወጣቷ ኢንተርኔትን እንደ ገቢ ማግኛ መጠቀሟ እንድታድግ እንደረዳት ትናገራለች። በፍቅር የምትሰራውን ለዓለም የማጋራቷን እውነታም ትወደዋለች።

ፎቶዎች ማንሳት ላይ ውዬ ፣ በድካም ዝዬ በቀጣዩ ቀን ስነቃ ምንም ቢደክመኝ ውስጤ ብዙ ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ከልብ የምትወደውን ስራ የምትሰራ ከሆነ አንድም ቀን የሰራህ አይመስልህም ይባላል።  የምወደውን ነገር በየዕለቱ እየሰራሁ ገንዘብ አገኛለሁ፣ ዓለምን እዞራለሁ። ከዚህ የበለጠ ደስታ ያለም አይመስለኝ። 

ካሉሂ አዳጋላም እንደ ሲልቪያ ሁሉ ስራዋን ትታ ወደ ጡመራው የገባች ናት። የፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪነት ስራዋን የዛሬ አምስት ከለቀቀች በኋላ “የካሉሂ ማድቤት” የተሰኘ ጦማር ከፍታ ከምግብ ጋር የተያያዙ ሀሳቦቿን መጻፍ ጀመረች። የዕለት ተዕለት የማድቤት ውሎዋን ማጋራቷ  ሀሳቧ ኬንያውያን ጋር ብቻ ሳይሆን ኢንተርኔት የሚጠቀም ሁሉ ጋር እንዲደርስ አስችሏታል። ከዚያም ተሻግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ካተረፉ ዕውቅ ምግብ አብሳዮች (ሼፎች)ጋር ግንኙነት መፍጠር እንድትችል አድርጓታል። በእጃቸው የከሸኑትን ምግብም ከኩሽናቸው ተገኝታ ለማጣጣምም ዕድሉን ከፍቶላታል። ይህን ዕድልም የኬንያን ምግቦች ለማስተዋወቅ ተጠቅማበታለች።

“መጦመር ስጀምር ይህ የሙሉ ስራ ጊዜዬ እንዲሆን አስቤ አልነበረም። የምግብ አዘጋጃጀት ዝርዝሬን ለጓደኞቼ ለማጋራት በማሰብ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን በራሱ ስም ያለው ሆነ”  ትላለች ካሉሂ።

ካሉሂም ሆነች ሲልቪያ መጠሪያ ስማቸው ዝነኛ እንደሆኑ የምርት መለያዎችታዋቂ ሆኗል። ሆኖም በኬንያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች አሁንም ቢሆን ቁም ነገር የሚሰሩ አይመስላቸውም። የራሳቸውን የአኗኗር ዘይቤ መሸጥ ላይ ያተኮሩ አድርገው ይወስዷቸዋል። ጦማሮቻቸውን የተመለከተ ግን የጥረቶቻቸውን ልክ በስራዎቻቸው ውስጥ ያስተውላል። ሁለቱም በማህበራዊ ድረገጾች በርካታ ተከታዮች አሏቸው። 

ለመሆኑ በኬንያ ምን ያህ ጦማሪያን ያሉ ይመስላችኋል? ከኬንያ የጦማሪያን ማህበር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ሀገሪቱ 24 ሺህ ጦማሮች አሏት። ይህ ቁጥር በየጊዜው የሚታደሱትንም ሆነ ጭርሱኑ አዲስ መረጃ ማውጣት ያቆሙትን ጭምር ያካተተ ነው። የጦማርያን ማህበሩ ሊቀመንበር ኬኔዲ ካችዋንያ ባሉበት የቆሙ ጦማሮች ከጦማሪያኑ ቁርጠኝነት ማጣት የመጣ እንደሆነ ይናገራል። ጦማሪያኑ ሊያስተዋውቁ በተነሱለት ጉዳይ ላይ ያሉ ሁነቶችን ወይም መረጃዎችን ለተከታታዮቻቸው በየጊዜው የማቅረብ ድክመት ሲስተዋልባቸው የሚመጣ እንደሆነም ያስረዳል። “አንዳንድ ሰዎች አሉ መጦመር ይጀምሩና በወራት ውስጥ ቀላል ነገር አለመሆኑን ይገዘባሉ። ከዚያ መጦመር ያቆማሉ። በየጊዜው የሚጦምሩትን እና እንቅስቃሴ ያለባቸው ጦማሮችን በተመለከተ እኛ ጋር ያለው ቁጥር የሚያሳየው 3,800 ገደማ  ነው። ይህ እንግዲህ በቪዲዮ የሚጦምሩትን ሁሉ ይጨምራል” ሲል ያብራራል ካችዋንያ።

Symbolbild Blog Blogging Internet
ምስል Fotolia/Claudia Paulussen

በቪዲዮ ጡመራን እንግሊዘኛ ተናጋሪዎቹ ቪሎግ ይሉታል። ጡመራን የሚገልጸው የእንግሊዘኛውን blogging የተሰኘውን ቃል እና ቪዲዮን በማጣመር የተገኘ ነው። በቪዲዮ መጦመር በሌላው ዓለም ጥሩ ተቀባይነት ቢያገኝም በኬንያ ግን አሁንም በጥርጣሬ ነው የሚታየው። በዩቲዩብ ቪዲዮዎችን የሚያወጡ ጦማሪያን ተቀናቃኞቻቸውን አሊያም የድርጅቶችን ምስል የሚያጠለሹ አዋኪ ወይም በጥባጭ ተደርገው ይወሰዳሉ። 

አሁን ነገሮች ቀስ እያሉም ቢሆን እየተለወጡ ይመስላል። በቪዲዮ የሚጦምሩቱ (ቭሎገርስ ይሏቸዋል) ጥሩ ተደርጎ ከተሰራ ይህም የሙሉ ጊዜ ስራ መሆን እንደሚችል እያሳዩ ይገኛሉ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው ሚስ ማንዲ በሚል የቁልምጫ ስም የምትጠራው ማንዲ ሳሮ ነች። ማንዲ ከሁለት ዓመት በፊት በከፈተችው የዩቲዩብ ቻናሏ በምግብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ ያጠነጠኑ ቪዲዮዎች ለተከታታዮዎቿ ታቀርባለች። 

ማንዲ በየጊዜው ለዕይታ የምታበቃቸውን ቪዲዮዎች በዩቲዩብ ቻናሏ በቋሚነት የሚከታተሉ 27 ሺህ ገደማ ደንበኞችን  አፍርታለች። “ተልዕኮዬ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ስለ ምግብ ማስተማር ነው” ትላለች ወጣቷ ጦማሪ።  “በምግብ ታሪኮችን እናገራለሁ” የምትለው ማንዲ ስራዎቿን ደረጃውን በጠበቀ እና ቁምነገርን ባደባለቀ መልኩ ታቀርባለች። ጦማሪያን እንዲህ ራሳቸውን ለማስመስከር ቢታትሩም የሚሰሩትን በቁምነገር ያለመውሰድ ችግር ከገዛ ቤተሰቦቻቸው ጭምር ይገጥማቸዋል። ሲልቪያ በእንዲህ አይነት ችግር እንዳለፈች ትናገራለች። 

“ከስድስት አመት በፊት አሁን የምሰራውን ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ገንዘብ አያገኙበትም ነበር።  ይህ አዲስ የስራ መስክ ነው። እናቴ እኔን በቴሌቭዥን እና በመፅሔት መመልከት ስትጀምር ነው ይህ ነገር ቁምነገር ያለበት ሳይሆን አይቀርም ያለችው።  ምክንያቱም እርሷ እኔ ምን እንደምሰራ ግንዛቤ አልነበራትም። ቀጭን ረዥም ተረከዝ ያላቸው ጫማዎች አድርጌ ቀኑን ሙሉ ስሮጥ እና ወደ ፓርቲዎች ለመሄድ ሜካፕ ስቀባባ ነው የምታየኝ። እና ለእናቴ ራስሽን ማስተማር፣ መማር አለብሽ ብዬ ነው የነገርኳት” ትላለች ሲልቪያ።  

Kenia Afrika Fashion Blogger Kaluhi Adagala
ምስል privat

ለካሉሂ ግን ሰዎች ስለስራዋ ላላቸው አመለካከት ቦታ አትሰጥም። “ለእኔ ይህ አሳሳቢ አይደለም። በወሩ መጨረሻ አስቤዛዬን መሸመት እና ገንዘብ ማግኘት ከቻልኩ ሌላው ሰው ስለስራዬ የሚያስበው አይረብሸኝም” ባይ ነች።  

የኬንያ ጦማርያን ማህበር ሊቀመንበር ካችዋንያ አሁንም በዘርፉ የበለጠ መሻሻል ለማምጣት እንደሚቻል ይናገራል። በኬንያ ያለው የኢንተርኔት ሽፋን 88 በመቶ ቢደርስም የሀገሪቱ ዜጎች በዲጂታሉ ዓለም ያሉ እንደ ፖድካስት እና ዩቱዩብ አይነት አገልግሎቶችን ሙሉ ለሙሉ መጠቀም እንዳልቻሉ ሊቀመንበሩ ይገልጻል። በኬንያ ያሉ አብዛኞቹ ጦማሪያን በምግብ እና የአኗኗር ዘይቤ ላይ በማተኮራቸው እንደ ግብርና፣ ትምህርት እና አካባቢ መሰል ጉዳዩች ገሸሽ መደረጋቸውም እንደ ድክመት ይነሳል።

“ወጣት ከሆንክ ተጠቃሚ ልትሆን የሚገባህ ቦታ ይህ ነው። ምክንያቱም ስራ ለመጀመር መሰናክል የሚሆንብህ ነገር አናሳ ነው። ወደዚያ እንዳትገባ የሚከለክሉ ቡድኖችም የሉም። አንዴ ወደዚያ ከገባህ ከኢኮኖሚው ዘርፍ ባለቀ ምን ያህል ዲሞክራሲያዊ እንደሆነ ታየዋለህ” ሲል ካችዋንያ ወጣቶችን ወደ ስራው እንዲገቡ ያደፋፍራል። 

“መጽሐፉን በሽፋኑ አትመዝነው” የሚል የቆየ አባባል አለ። ለሌላው ሰው ይህ አባባል የማይሰራ ሊመስል ይችላል በኬንያ ስራን አስመልክቶ ያለውን ተረክ እየቀየሩ ላሉ ለእነዚህ ጦማሪያን ግን ብዙ ትርጉም አለው። ስራ ፍለጋ ሲወጣ በጥልቅ ስሜት የሚሰራውን እንጂ በየቀኑ ድብርት ውስጥ የሚከተውን አይነት መሆን እንደሌለበት ህይወታቸው አስተማሪ ነው። 

ሮህዳ ኦዲሃምቦ/ ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ