1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ወለጋ 10 ባንኮች ተዘርፈዋል - የዞኑ አስተዳዳሪ

እሑድ፣ ጥር 5 2011

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን 10 ባንኮች በታጣቂዎች መዘረፋቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ለDW ተናገሩ። ታጣቂዎቹ በዞኑ የአራት ወረዳዎች የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ማቃጠላቸውን እና  በሌሎቹ ወረዳዎች ዝርፊያ መፈጸማቸውን ገልጸዋል። 

https://p.dw.com/p/3BUaK
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በምዕራብ ወለጋ 10 ባንኮች መዘረፋቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ገለጹ

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቺስ ተመስገን ለDW እንደተናገሩት በመንግስት እና የግል ባንኮች ላይ ዝርፊያው የተፈጸመው ትላንት 10 ሰዓት ገደማ ነው። አስተዳዳሪው የታጠቁ ባሏቸው ኃይሎች ተፈጸመ ያሉት ዝርፊያ የተከናወነው በተመሳሳይ ሰዓት መሆኑንም ገልጸዋል።  

“የታጠቀው ኃይል እዚህ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እና በደረሰን መረጃ መሰረት 10 የሚሆኑ የመንግስት እና የግል ባንኮች ተዘርፈዋል” ብለዋል የዞኑ አስተዳዳሪ። ከተዘረፉት ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ሕብረት ባንክ እንዲሁም የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ባንክ እንደሚገኙበት አስረድተዋል። በባንኮቹ ዝርፊያ የተወሰደው ገንዘብ መጠኑ ግን እስካሁን አለመታወቁን ጨምረው ገልጸዋል።  

የታጠቁት ኃይሎች በባንኮች ላይ ከፈጸሙት ዝርፊያ በተጨማሪ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አቶ ተመስገን አክለዋል። በተለይ በዞኑ አራት ወረዳዎች ላይ ያሉ የመንግስት ተቋማት ታጣቂዎች አቃጥለው ሙሉ በሙሉ ማውደማቸውን አብራርተዋል። በዞኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አራት ወረዳዎች ገንጂ፣ ባሎሳቢ፣ ዱግዶ እና አለታ ሲቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በምዕራብ ወለጋ ዞን የመከላከያ ሰራዊት ቢሰማራም የታጠቁት ኃይሎች በተመሳሳይ ሰዓት በየአካባቢው ጥቃት የሚያደርሱ በመሆናቸው ለመቆጣጠር ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል። 

ከምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቺስ ጋር የተደረገውን አጭር ቃለ ምልልስ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።  

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ