1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

በሰብዓዊ ካፒታል ምዘና ኢትዮጵያ 135ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 2011

በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ካፒታል ምዘና ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ውጤት ከተሰጣቸው አገሮች ተርታ ተመድባለች። ባለፈው ሳምንት የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት በጋራ ባካሔዱት ስብሰባ ላይ ይፋ በተደረገው መመዘኛ ኢትዮጵያ 135ኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም ለዘርፉ ትኩረት የሰጠች ተብላለች። 

https://p.dw.com/p/36iNE
Indonesien IWF stellt Weltwirtschaftsbericht auf Bali vor
ምስል picture-alliance/dpa/F. Lisnawat

የአፍሪቃ አገሮች ዝቅተኛውን ደረጃ ይዘዋል

የዓለም ባንክ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው የሰብዓዊ ካፒታል ምዘና ውጤት ኢትዮጵያ ከ157 አገሮች በ135ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በምዘናው በርካታ የአፍሪቃ አገሮች ዝቅተኛ ውጤት ተሰጥቷቸው የግርጌውን ቦታ ተቆጣጥረዋል። ቻድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኒጀር እና ማሊ እጅግ ዝቅተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ አገሮች ናቸው። ባለፈው ሐሙስ ይፋ የተደረገው ይኸው መመዘኛ አገሮች በጤና እና የትምህርት ዘርፎች የሰሩትን ሥራ እየመዘነ ደረጃ ይሰጣል። የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው ሰነድ የ157 አገሮች የጤና እና የትምህርት ሥርዓቶች ዜጎቻቸውን ለውጤታማነት አሊያም ስኬታማነት ያበቁ እንደሁ ብሎ መርምሯል። 

ሰነዱ ይፋ የተደረገው በኢንዶኔዥያዋ የባሊ ከተማ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጥምር ስብሰባ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ነበር። በስብሰባው የተለያዩ ሃገራት የፋይናንስ እና የኤኮኖሚ ምኒስትሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማትን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ታድመዋል። ጉባኤው በዋንኛነት በሰብዓዊ ልማት ሥራዎች ያተኮረ ሲሆን ስኬታማ የተባሉ አገራት ሹማምንት የውጤታማነታቸውን ምሥጢር ለተሳታፊዎች አጋርተዋል። ኢትዮጵያ በመመዘኛው ዝቅተኛ ከሚባሉት ጎራ ብትመደብም በመድረኩ በመንግሥት ቁርጠኛ ሥራዎች መሻሻል አሳይተዋል ተብለው ከተጠቀሱ መካከል ነበረች።

ባለፈው ሰኞ አዲስ በተዋቀረው የጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ ካቢኔ ምክንያት የቀድሞው የተባሉት የፋይናንስ እና ኤኮኖሚ ትብብር ምኒስትሩ አቶ አብርሐም ተከስተ (ዶ/ር) በመድረኩ የሰብዓዊ ካፒታል ልማት የመንግሥታቸው ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል። ምኒስትሩ "በሰዎች እና ሰብዓዊ ካፒታል ላይ መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው። የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል ይረዳል፤ ሰዎች በአገራቸው እና በማኅበረሰቦቻቸው ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸውም ያግዛል። የረዥም ጊዜ የልማት ዕቅድ ያላት ኢትዮጵያን ለመሠሉ አገሮች ደግሞ በሰዎች ላይ ጥሪትን ማፍሰስ እጅግ አስፈላጊ ነው። የረዥም ጊዜ ልማት ጤናማ፤ በአግባቡ የሰለጠነ እና የተማረ ዜጋ ይፈልጋል። ይኸ የልማት ሥልታችን ዋንኛ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል። ከመንግሥታችን በኩልም ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለ" ሲሉ ተናግረዋል። 

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ጂም ዮንግ ኪም የባሊው ስብሰባ ሲከፈት እንደተናገሩት አገሮች ለዜጎቻቸው በሚያቀርቧቸው ትምህርት እና ጤናን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች አቀራረብ፣ ጥራት እና ፍትኃዊነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል። መንግሥታት ዜጎች ወደ ፊት የሚኖራቸውን እውቀት፣ ክህሎት እና ጤና ሊፈትሹ ይገባል ያሉት ጂም የመጀመሪያው የሰብዓዊ ካፒታል መመዘኛ ሁነኛ መሳሪያ እንደሚሆናቸው አስረድተዋል።

Indonesien IWF Bali | Lagarde
ምስል Reuters/J. P. Christo

«ይኸ መመዘኛ ለፖሊሲ አውጪዎች በልጆች ጤና እና የትምህርት አቀባበል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እና የዜጎቻቸው ገቢ መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያስችል አስደናቂ መረጃ ይሰጣል። የአገሮቻቸውን  መፃኢ እጣ-ፈንታ ለማረቅም ያግዛል። የረዥም ጊዜ እና አካታች ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት ሰብዓዊ ካፒታል ለመገንባት የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ኹነኛ መንገድ ናቸው።»

የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው የሰብዓዊ ካፒታል መመዘኛ ሦስት መሠረታዊ መለኪያዎች አሉት። የመጀመሪያው የሕጻናት በሕይወት የመቆየት ዕድል ሲሆን በአንድ አገር ያለውን ዕድሜያቸው ከአምስት አመታት በታች የሆኑ ሕጻናት ሞት በማስላት ይመዘናል። ሁለተኛው ልጆች በትምህርት ቤቶች የሚኖራቸውን ቆይታ እና የሚያገኙትን የትምህርት ጥራት የተመለከተ ነው። ሦስተኛው የጎልማሶችን በሕይወት የመቆየት ዕድል እና ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕጻናትን መቀንጨር አጣምሮ የያዘ ነው።  

የዓለም ባንክ እንደሚለው መስፈርቶቹ የተመረጡት አምስቱ ጉዳዮች ከስኬታማነት ጋር ያላቸው ቀጥተኛ ግንኙነት በጥናት በመረጋገጡ ነው። 
ስሌቱ አንድ ሕፃን ዕድሜው ለትምሕርት እስኪደርስ በሕይወት ይቆያል? ያ ሕፃን ትምህርት ከጀመረ በትምህርት ቤት ለምን ያክል ጊዜ ይዘልቃል? በአግባቡ ማንበብ እና መፃፍን ይማራል? በሒሳብ እና በሳይንስ የትምህርት ዘርፎች እንዲሁም ለችግሮች መፍትሔ በመፈለግ ረገድ ብቁ ይሆናል? ለከፍተኛ የትምህርት ተቋምስ ይደርሳል? ለሚሉ ጥያቄዎች የሚሰጡ ምላሾችን ይተነትናል። 

በጤና ረገድ አንድ ሕጻን በጤናማ እና ደኅንነቱ በተረጋገጠ አካባቢ ያድጋል? በቂ ምግብ፣ ሕክምና እና ለስኬታማነት የሚያበቃ ቤተሰባዊ ድጋፍ ይኖረዋል? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት የአንድ ትውልድን መፃኢ እጣ-ፈንታ ያሰላል። በእነዚህ የመመዘኛ ነጥቦች መሠረት ኢትዮጵያ ከዝቅተኞቹ ጎራ ተመድባለች። አቶ አብርሐም እንዳሉት ግን መንግሥታቸው ለዜጎቹ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ለማድረስ ከመስራት አላመነታም። 

Deutsche Schule in Äthiophien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher


አቶ አብርሐም "እስከ 60 በመቶ በጀታችንን በትምህርት፣ በጤና፣ የዜጎችን ማኅበራዊ ደህንነት በሚያረጋግጡ አገልግሎቶች እና ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ለማዋል ችለናል። ላለፉት 15 አመታት ይኸንንው ያለማቋረጥ በማድረግ ላይ እንገኛለን። በዚህም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለማዳረስ የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ ግብ ለማሳካት ችለናል። የመጀመሪያ የጤና ክብካቤ አገልግሎትን ለማዳረስ ተቃርበናል። የሕፃናት እና የእናቶች ሞት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል። በ1996 ወደ 50 በመቶ ገደማ የነበረው ድሕነት በ2016 ወደ 24 በመቶ ዝቅ ብሏል" ሲሉ የኢትዮጵያ ስኬቶች ያሏቸውን በመድረኩ ባሰሙት ንግግር ጠቃቅሰዋል። 

ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሖንግ ኮንግን የመሳሰሉ አገራት በሰብዓዊ ካፒታል ምዘናው ከአናት ተቀምጠዋል። በውይይቱ የተሳተፉ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች፣ የአገራት ሹማምንት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበላይ ኃላፊዎች አገሮች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎች ለማፍራት የፖሊሲ አቅጣጫዎቻቸውን ቆም ብለው እንዲፈትሹ አሳስበዋል። አገራቱ በበኩላቸው በዘርፉ ስኬታማ ለመሆን ቁርጠኝነታቸውን ሻገር ሲልም የገንዘብ ችግሮቻቸውን አስረድተው ዓለም አቀፍ አጋርነት እንደሚያሻቸው ከመግለጽ አልቦዘኑም። ኢትዮጵያን ወክለው በመድረኩ ንግግር ያደረጉት አቶ አብርሐም ተከስተ ጤና እና ትምህርትን ለመሳሰሉ አገልግሎቶች የሚያስፈልገው ገንዘብ በዋንኛነት ከመንግሥታቸው ኪስ እንደሚወጣ ቢናገሩም የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያሻቸውም ገልጸዋል። 

"የሰብዓዊ ካፒታል ልማትን ከዝቅተኛ ደረጃ በመጀመራችን ምክንያት አሁንም ፈተናዎች አሉብን። በተለይ በአሁኑ ወቅት የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ጥራት በማሳደግ ላይ ትኩረት እያደረግን እንገኛለን ። ከዚህ በተጨማሪ ፍትኃዊነት ላይም የበለጠ ትኩረት እየሰጠን ነው። የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶች በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና አካባቢዎች በፍትኃዊነት መዳረሳቸውን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው። ኢትዮጵያ ጥራት እና ፍትኃዊነትን ለማሳደግ አሁንም ቁርጠኛ ነች" ያሉት አቶ አብርሐም አብዛኛው ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ጠቁመዋል።  "ይሁን እና አሁንም የአገር ውስጥ ጥሪታችን ብቻውን በቂ አይሆንም። ስለዚህ ከልማት አጋሮቻችን ብዙ እንጠብቃለን። የዓለም ባንክ የሰብዓዊ ካፒታል ልማት መርሐ-ግብሮቻችንን በመደገፍ ረገድ ቁልፍ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በእንደዚህ አይነት ድጋፍ በሰብዓዊ ካፒታል ሥራዎች ከዚህ ተጨማሪ ስኬቶች እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል። 
በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሔንሪኤታ ፎር በበኩላቸው «የነገን ሰብዓዊ ካፒታል ለመገንባት ኹነኛው መንገድ የትም ይኑሩ የት በዛሬ ልጆች እና ወጣቶች ላይ መስራት ነው። የዛሬ ወጣት ዓለም እጅግ የተሳሰረች መሆኗን ይመለከታል። እምቅ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ አድርገን ካሳደግናቸው በርካታ ዕድሎች አሉ። እነዚህ ልጆች መዋዕለ-ንዋያችንን ሁሉ በእነሱ ላይ እንድናውል ይጠብቃሉ። ይኸ መደረግ ያለበት ትክክለኛ ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን አዋጪ በመሆኑ ጭምር ነው። አገሮቻችን ያለ ጠንካራ የነገ ትውልድ ሊያድጉ እና የበለጸጉ ሊሆኑ አይቻላቸውም።» ሲሉ በመድረኩ ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ