1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሌ ክልል 30,000 ገደማ ሰዎች እርዳታ ይሻሉ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 10 2010

በሶማሌ ክልል ሁለት ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች እርዳታ የሚያቀርበው የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር (WFP) በክልሉ ከተቀሰቀሰው ቀውስ በኋላ መደበኛ ሥራውን መጀመር እንደተሳነው አስታወቀ። በተለይ በጸጥታ መናጋት ሳቢያ በገጠራማ አካባቢዎች የምግብ እርዳታ ማድረስ እንዳልቻለ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ቃል አቀባይ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/33HYr
Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

WFP operation in Somali region halted due to unrest - MP3-Stereo

የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር በሶማሌ ክልል በተቀሰቀሰው ቀውስ ሳቢያ የተቋረጠ ሥራው አሁንም እንዳልተጀመረ አስታወቀ። "ቀውሱ በዓለም የምግብ መርኃ-ግብር ሥራ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል" የሚሉት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ቃል አቀባይ ፖል አንተም ድርጅታቸው በመደበኛ ሥራው በሶማሌ ክልል የምግብ ዋስትናቸው ላልተረጋገጠ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ ያቀርብ እንደነበር ገልጸዋል። "እንዲያውም በኢትዮጵያ ሥራችን የሶማሌ ክልል ዋናው ማዕከል ነው ማለት ይቻላል። በመንግሥት የምግብ ለሥራ መርኃ-ግብር በድርቅ ለተጎዱ 311, 000 ገደማ ሰዎች ምግብ እናቀርባለን። ይኸ መደበኛ ሥራችን ነው። መደበኛ ሥራችን ደግሞ በጸጥታው ሁኔታ ምክንያት ተቋርጧል። ምክንያቱም ልንደርስ የምንፈልገውን ማኅበረሰብ መድረስ አልቻልንም" ሲሉ አክለዋል። 

የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር መደበኛ ሥራው ቢቋረጥም ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ቀውስ ሳቢያ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለተጠለሉ ሰዎች እገዛ እያደረገ መሆኑን ፖል አንተም ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር በጅጅጋ ከተማ በአብያተ-ክርስቲያናት፣ መስጊዶች፣ የበጎ አድራጎት ተቋማት እና የተለያዩ ማዕከላት ለተጠለሉ ዜጎች ሩዝ እና ዘይትን ጨምሮ አስፈላጊ የምግብ ግብዓቶች ማከፋፈሉን ድርጅቱ ገልጿል። እስካሁን ድረስ ከ15,000 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች 131 ሜትሪክ ቶን ምግብ ተከፋፍሏል። እንደ ፓል አንተም ገለፃ ግን አሁንም ከ20,000 እስከ 30,000 የሚደርሱ ሰዎች እርዳታ ይሻሉ።

"አለመረጋጋቱ ነሐሴ 28 ቀን ከተቀሰቀሰ በኋላ የምግብ ዕደላ እንደገና የጀመርንው ነሐሴ 3 ቀን ነው። በወቅቱ ወደ 52, 000 ገደማ ሰዎች በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ ዙሪያ መጠለያ ይፈልጉ ነበር። ባለፉት ጥቂት ቀናት ባደረግንው አፋጣኝ ዳሰሳ ከ20,000 እስከ 30,000 ሰዎች የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ እና ልንደርስላቸው የሚገባ ሰዎች መኖራቸውን ተገንዝበናል"

የሶማሌ ክልል የጸጥታ ሁኔታ በአንፃራዊነት መረጋጋት ቢታይበትም ወደ ነበረበት ግን አልተመለሰም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው የጉዞ ገደብም እንዳለ ነው። ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልን ነው ያሉት ፖል አንተም የጸጥታ ሁኔታው ከተሻሻለ መደበኛ ሥራቸውን ለመመለስ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ የምግብ እርታ ፈላጊዎች መድረስ አለመቻላቸው ግን መሰረታዊ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።

"የምግብ እርዳታ ለሚፈልጉት በማድረሱ ረገድ ልንደርስ የምንፈልጋቸውን አብዛኞቹን የከተማ አካባቢዎች መድረስ ችለናል፤ ወይም በሚቀጥሉት ቀናት እንደርሳለን። ነገር ግን ገጠራማ አካባቢዎች ለመድረስ አስቸጋሪ ናቸው። ምክንያቱም የጸጥታ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው። ይኸ በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ ችግር እየፈጠረብን ነው። መደበኛ ሥራችንን የሚቻል ከሆነ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንጀምራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ነገር ግን እስካሁን ድረስ በገጠራማ አካባቢዎች የማከፋፈል ሥራችንን ለመጀመር የሚረዱን የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይሁኑ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ቢሮ ሰራተኞች የሉም። ስለዚህ ስራችንን ለመስራት ወደ ገጠራማ አካባቢዎች መድረስ አልቻልንም" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ