1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪና ፋይናንስ እጦት ለጀርመን ኩባንያዎች ፈተና ሆነዋል

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2011

የኢትዮጵያን ገበያ ጠጋ ብለው የተመለከቱ የውጭ ባለሙያዎች እንደሚሉት ውስብስብ የሆነው አስተዳደራዊ ሥራ ለኩባንያዎች ፈተና ሆኗል። የውጭ ምንዛሪ እና የፋይናንስ እጦት የሚፈትናቸው እና በኢትዮጵያ የሚሰሩ የጀርመን ኩባንያዎች ተሰፋ የሚሰንቁበት ጉዳይ አላጡም።

https://p.dw.com/p/39yE6
Äthiopien Addis Abeba Megenagna
ምስል DW/E. Bekele Tekle

በገበያው መስፋፋትና የንግድ ሥራ ዕድሎች መጠናከር ተስፋ አድርገዋል

በኢትዮጵያ ገበያ በሥራ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች የፋይናንስ አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የቢዝነስ ከባቢው ፈተና ሆኖባቸዋል። ባለፈው ሳምንት የጀርመን የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት የምሥራቅ አፍሪቃ ልዑክ ይፋ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደሚጠቁመው የሰለጠነ የሰው ሐይል እጥረት፣ የንግድ መሰናክሎች እና መሠረተ-ልማት አሁንም በኢትዮጵያ ገበያ ለተሰማሩ የጀርመን ኩባንያዎች ጋሬጣ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። 

የዳሰሳ ጥናቱ አጠቃላይ ውጤት ግን ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ገበያ ባሏቸው ዕድሎች ባለተስፋ መሆናቸውን ይጠቁማል። የጀርመን የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት የምሥራቅ አፍሪቃ ቢሮ ካነጋገራቸው 39 ኩባንያዎች መካከል 69 በመቶው የኢትዮጵያ ሥራቸው በሚቀጥሉት አስራ ሁለት ወራት ውስጥ አሁን ካለውም በላይ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል። 54 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማሳደግ እቅድ አለን ብለዋል። 64 በመቶው በሥራቸው ደስተኛ ሲሆኑ 44 በመቶው ደግሞ ተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ለመቅጠር ሐሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል። 

Äthiopien Addis Abeba Tsehay Insurance & Nib Bank
ምስል DW/E. Bekele Tekle

ጥናቱ ለምን አስፈለገ?

የዳሰሳ ጥናቱን ያከናወነው የጀርመን የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት የምሥራቅ አፍሪቃ ልዑክ መቀመጫው በኬንያ ነው። ልዑኩ መሰል የዳሰሳ ጥናቶች ሲሰራ ይኸ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የተቋሙ ኃላፊ ማረን ዲያለ ሼልሽሚት ይናገራሉ። ሼልሽሚት እንደሚሉት በኢትዮጵያ ገበያ የጀርመን ኩባንያዎች እየተበራከቱ መምጣት እንደሌሎች አገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ ላይ ብቻ ያተኮረ የዳሰሳ ጥናት ለመስራት ምክንያት ከሆኗቸው ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል። 

"እንዲህ አይነቱ የዳሰሳ ጥናት በ90 አገራት በሚገኙ 140 ቢሮዎች በቋሚነት ለበርካታ አመታት ስንሰራው የቆየንው ነው። በዚህ ዓመት የሥራ እንቅስቃሴያችን እና በኢትዮጵያ ገበያ የተሰማሩ የጀርመን ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ልንሰራው ችለናል። በመላው ዓለም የዳሰሳ ጥናቱን ስንሰራ ሁልጊዜም ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንጠይቃለን። ከዚያ የእያንዳንዱን አገር ውጤት እንመለከታለን። ዋናው ቢሯችንም የዓለም አቀፍ ሁኔታውን ለመገምገም ውጤቶቹን ይመለከታል" 

ለዳሰሳ ጥናቱ የሚያገለግሉ ጥያቄዎችን በኢትዮጵያ ገበያ ለሚገኙ 39 ኩባንያዎች ልከው ባገኙት ከፍተኛ ምላሽ በአንታዊ መልኩ መገረማቸውን ማረን ዲያለ ሼልሽሚት ይናገራሉ። 

"ከ60 በላይ የሚሆኑት በኢትዮጵያ የሚገኙ ኩባንያዎቻቸው በተሰማሩበት ሥራ እና በመጪዎቹ ወራት በሚኖራቸው ዕድገት ባለ ተሥፋ ናቸው። የዳሰሳ ጥናቱ በምሥጢር የተከናወነ በመሆኑ የትኛው ኩባንያ ከጀርባ በትክክል ምን እንደሚያስብ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር የለም። ከከዳሰሳ ጥናቱ ውጤት እና በተጨማሪ ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ካደረግናቸው ውይይቶች እንደተረዳንው ባለተስፋ እንዲሆኑ ያደረጓቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው እያደገ ያለ ገበያ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እያደገ ሲሆን የንግድ ሥራ ዕድሎችም እየጨመሩ ነው"

Äthiopien Addis Abeba CMC
ምስል DW/E. Bekele Tekle

የጀርመኖቹን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገት፣ የገበያው መስፋፋት እና የንግድ ሥራ ዕድሎች መጠናከር ሼልሽሚት በቀዳሚነት የጠቀሱት ጉዳይ ነው። ሁለተኛው ግን በቀጥታ ከአገሪቱ የለውጥ ፍላጎት ጋር ይገናኛል። ሼልሽሚት በኢትዮጵያ እየታዩ ናቸው የሚሏቸው የማሻሻያ ዕርምጃዎች የጀርመን ኩባንያዎችን ባለተስፋ አድርጓቸዋል። በነገራችን ላይ ከጥቂት ወራት በፊት የጀርመኑ ፎልክስቫገን ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቆ ነበር። የፎክልስቫገን ደቡብ አፍሪቃ ሊቀ-መንበር እና ኩባንያው ከሰሐራ በረሐ በታች ለሚገኙ አገሮች ያቋቋመው ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ቶማስ ሼፈር ለDW እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ገበያ እና የሕዝብ ቁጥሩ ዕድገት ኩባንያው ለረዥም አመታት ችላ ያላትን አገር ለመመልከት ምክንያት እንደሆነ ገልጸው ነበር። 

"በጥሩ ሁኔታ ሊያድጉ ይችላሉ ፣ ወደፊት የመኪና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ምናልባት ያስፈልጋቸዋል ብለን የገመትናቸውን ገበያዎች ከሁለት አመታት በፊት አጠናን። በዚህ ረገድ በበርካታ ምክንያቶች ከለየናቸው አራት ቁልፍ ገበያዎች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች። አንደኛው አገሪቱ ከአፍሪቃ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የሕዝብ ቁጥር የሚገኝባት መሆኗ ነው። መንግሥቱም ቢሆን ወደ ፊት አርቆ የሚያስብ ነው። የባቡር አገልግሎት በመጀመሩ የማጓጓዣ ሥራ እየተቃለለ ይገኛል። ስለዚህ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ወደፊት እየመጡ ካሉት አገሮች መካከል ናት ብለን እንድናምን ያደረጉን በርካታ ምክንያቶች አግኝተናል"

ቶማስ ሼፈር ከጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከመከሩ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ፎልክቫገን በፍጥነት ሥራ እንዲጀምር ፍላጎት እንዳለው አስተውለዋል። ማረን ዲያለ ሼልሽሚት በበኩላቸው የኢትዮጵያ ገበያ ካለው ዕምቅ አቅም በተጨማሪ ባለፉት ስድስት ወራት አይተንዋል የሚሉት ለውጥ ለጀርመኖቹ ኩባንያ በኢትዮጵያ ገበያ የመተማመን መንፈሳቸውን እንዳሳደገላቸው ያስረዳሉ። 

Äthiopien Addis Abeba Luxusapartments by Tsehay Real Estate
ምስል DW/E. Bekele Tekle

"ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ወደፊት የሚኖረውን የቢዝነስ ዕድል በእርግጠኝነት አሳድገውታል። ከእኛ የዳሰሳ ጥናት ውጤት 65 በመቶ የሚሆኑት የጀርመን ኩባንያዎች አዎንታዊ ዕይታ እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት በመጪዎቹ አስራ ሁለት ወራት ከዚህ በላይ ይሻሻላል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። ይኸ ደግሞ እያደገ በሚሔደው ገበያ ብቻ ሳይሆን በአዲስ መንግሥት እና እየተወሰዱ ባሉ ማሻሻያዎች ኩባንያዎቹ የተመለከቷቸው አዎንታዊ ምልክቶች ሳቢያ ነው።" 

የኩንያዎቹ ሥጋቶች

በኢትዮጵያ ገበያ የተሰማሩት የጀርመን ኩባንያዎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸውንም ፈተና በዳሰሳ ጥናቱ ወቅት ዘርዝረዋል። 69 በመቶ ገደማ ኩባንያዎች ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የማግኘት ፈተና እንዳለባቸው አስታውቀዋል። 46.2 በመቶው እንደሚሉት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሁንም ፈተና ሆኖባቸዋል። ከዚያ ባሻገር የመንግሥታዊ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ ለውጭ ባለወረቶች መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ማረን ዲያለ ሼልሽሚት ያምናሉ።

"ለቢዝነስ ሥራ አስቸጋሪ በሆነው አስተዳደራዊ ውስብስብነት ረገድ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ። በርካታ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ አስተዳደራዊ መሰናክሎች ዛሬም አሉ። ትልቁ ፈተና የፋይናንስ እጦት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ ነው። ይኸ ምርታቸው መሸጥ ለሚፈልጉ ለሥራቸው የውጭ ምንዛሪ ለሚያሻቸው ዓለም አቀፍ ቢዝነሶች እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። በፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ረገድ ያለውን ችግር መፍታት የመንግሥት ኃላፊነት ብቻሊሆን አይገባም። ገደብ የሚያደርጉ ድንጋጌዎችን በማንሳት ግልፅ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ነገሮች አሁንም እጅግ ውስብስብ ናቸው። ስለዚህ አንድ ሥራ መጀመር እና መስራት ቀላል ሊሆን ይገባል"  

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት የጀርመን ኩባንዎችን ቀልብ ለመሳብ ተደጋጋሚ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በኢትዮጵያውያኑ እና በጀርመን አቻቸው መካከል የተደረጉ ውይይቶች ግን የሚገባውን ያክል ጥረት አላፈሩም። ሼልሽሚት እንደሚሉት የጀርመን ኩባንያዎች እንደ ኢትዮጵያ ባለ ገበያ ለመግባት ወግ አጥባቂ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ጥረትም ቢሆን በአንድ ጊዜ ፍሬ እንዲያፈራ መጠበቅ የዋህነት ነው። 

Äthiopien Addis Abeba Nib International Bank
ምስል DW/E. Bekele Tekle

"ባለፈው አመት መንግሥት የኢትዮጵያን ገበያ ለማስተዋወቅ ከጀርመን ኩባንያዎች ጋር ተደጋጋሚ ግንኙነት ሲያደርግ ነበር። እኛም በአብዛኞቹ መርሐ ግብሮች ላይ ተሳትፈናል። ትልቅ ፍላጎትም ተመልክተናል። ፍላጎት ብቻውን ግን የጀርመን ኩባንያዎችን ከወራት በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። በጀርመን ኩባንያዎች ረገድ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ረዥም ነው።  ስለዚህ የውይይቶቹን ውጤት የምናየው ምናልባት በመጪዎቹ አመታት ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ መዋዕለ-ንዋይ የንግድ እንቅስቃሴን ይከተላል። አብዛኞቹ ኩባንያዎች ወዲያውኑ ወደ ሥራ አይገቡም። መጀመሪያ የገበያውን ጠባይ ለመረዳት እና የስራ አጋር ለማግኘት ጠንካራ ጥናት ይሰራሉ። ከዚያ በቋሚነት ወደ ሥራ ሊገቡ ይችላሉ። አንዳንድ ከፍተኛ ቴክኒካዊ ሥራዎች ሊሰሩ የሚችሉት በጀርመን ብቻ በመሆኑ በኢትዮጵያ ሥራ የማይጀምሩም ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህ ጉዳዩ በስራ ዘርፎች ያለው ልዩነት መታየት አለበት። ከጀርመን ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር እና የመዋዕለ-ንዋይ ዕድሎችን በማስተዋወቅ ብቻ አፋጣኝ ውጤት ማግኘት አይቻልም። ጊዜ ይወስዳል"

ማረን ዲያለ ሼልሽሚት በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር ያለው ውስብስብ ሒደት ሊቃለል እንደሚገባ በተደጋጋሚ ጠቁመዋል። ኃላፊዋ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የምትከተለው አሰራር ኩባንያዎች የማሸሽ አቅም ጭምር አለው። 

እሸቴ በቀለ