1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኤርትራ የድንበር ጥብቅ ቁጥጥሩ አንድምታ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 28 2011

በኤርትራም ኾነ በኢትዮጵያ በኩል በይፋ ሳይገለጥ፦ ተከፍተው የነበሩት የዛላምበሳ እና የራማ ድንበሮች ወደ ኤርትራ የሚወስዱት በቀላሉ ማለፍ የማይቻልባቸው መኾናቸው ተገልጧል። ወደ ኤርትራ ለማለፍ የኤርትራ ባለሥልጣናት ከፌዴራል መንግሥቱ የተሰጠ ሰነድ መጠየቅ እንደጀመሩም ተጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/3B3f6
Äthiopischer Ministerpräsident Abiy Ahmed beim Staatsbesuch in Eritrea
ምስል Twitter/@fitsumaregaa

በኤርትራ የድንበር ጥብቅ ቁጥጥሩ አንድምታ

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የሥልጣን መንበሩን ከተረከቡበት ካለፉት ስምንት ወራት አንስቶ ግንኙነታቸው ፈጣን በሚባል መልኩ ለውጥ አሳይቷል። በሁለቱ ሃገራት መካከል የተዘጉ ድንበሮች ተከፍተው የሁለቱም ሃገራት ዜጎች ለረዥም ጊዜያት ተራርቀው ከነበሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት በቅተዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ቀጥሎም በአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ ሲቀላጠፍም ተስተውሏል። ያም ኾኖ ግን ምክንያቱ በኤርትራም ኾነ በኢትዮጵያ በኩል በይፋ ሳይገለጥ ተከፍተው የነበሩት የዛላምበሳ እና የራማ ድንበሮች ወደ ኤርትራ የሚወስዱት በቀላሉ ማለፍ የማይቻልባቸው መኾኑ ተገልጧል።

ወደ ኤርትራ ለማለፍ የኤርትራ ባለሥልጣናት ከፌዴራል መንግሥቱ የተሰጠ ሰነድ መጠየቅ እንደጀመሩም ተጠቅሷል። ድንበሩ ተከፍቶ ተዘጋ እስከተባለበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያም ኾነ በኤርትራ በርካታ ኹነቶች ተስተውለዋል። ለአብነት ያኽል  ኤርትራ ውስጥ ጄኔራል ስብሓት ኤፍራም ላይ የመግደል ሙከራ መደረጉ፤ ከመስከረም አንድ ጀምሮ ከ27 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው፤ «ከኤርትራ በኩል የሥጋት ሁኔታ» ቀንሷል በሚል በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ሰፍሮ የነበረው  የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር ወደ ክልሎችና የድንበር አካባቢዎች እንዲንቀሳቀስ መደረግ ተጀምሯል መባሉ ይጠቀሳሉ። በእርግጥ እነዚህ ጉዳዮች ከድንበር መዘጋቱ ጋር ምን ግንኙነት አላቸው? በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ላይስ ያለቸው አንድምታ ምን ይመስላል? የውይይቱ ትኩረት ነው።


ማንተጋፍቶት ስለሺ