1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግብፅ የአባይ ዉኃ እና ብክለቱ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 6 2010

የአባይ ወንዝ መበል ለግብፅ ትልቅ ችግር ነዉ። የኬሚካል ኩባንያዎች ፍሳሻቸዉን ወደዚሁ ወንዝ ነዉ የሚለቁት። የመጸዳጃ ቤት  ፍሳሽም በከፊል ወደዚሁ ወንዝ ይገባል። በዚያም ላይ ቆሻሻ አባይ ላይ ይንሳፈፋል። ይህን የደፈረሰ እና የሚሸት ዉያ ተጠቅመዉ በዴልታ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች ማሳቸዉን በመስኖ ያርሳሉ።

https://p.dw.com/p/2pSYR
Ägypten Kairo Nil-Fluss
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Ammar

አባይ ለግብፅ ሕይወቷ ነዉ፤

የዉኃ ጠበብት ከዴልታ አካባቢ የሚመጡ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች በከፍተኛ ደረጃ የተበከሉ መሆናቸዉን ይናገራሉ። የአባይ ዉኃን በቧምቧ አስተላልፎ ጥቅም ላይ ለማዋል በተለይ ደግሞ ጨዉን ለማስወገድ ሂደቱ እጅግ ዉስብስብ ነዉ ። የአባይ ዉኃ ምን ያህል ቆሻሻ ይሆን? ለማጽዳትስ ምን ማድረግ ይቻላል?

«ከአባይ ዉኃዬ አልጠጣህም ወይ? ይላል የግብጿ ኮከብ ከያኒ ሽሪን ታዋቂ ከሆኑት ዜማዎቿ አንዱ። ነገር ግን በቅርቡ በአንድ የሙዚቃ ድግሷ ላይ ይህን ዘፈን እንድትጫወት ስትጠየቅ የተሰማዉ ያለዉን ችግር አመላካች ነዉ። ይኸዉም «የአባይ ዉኃን ከምትጠጡ ባለጋዙን ዉኃ ጠጡ፤ አለበለዚያ ሲስቶሶማይስስ ይከተላችኋል» ስትል ተደምጣለች። 

ሽሪን በሙዚቃዋ እንደዋዛ ያቀረበችዉ ነገር ግብፅ ዉስጥ ባስከተለዉ መዘዝ ምክንያት ከዘፈን ሥራዋ እንድትታገድ አድርጓታል፤ መገናኛ ብዙሃንም የእሷን ሙዚቃ አያጫዉቱም፤ ጉዳይዋም በፍርድ ቤት እየታየ ነዉ። ጥፋቷ ደግሞ የግብፆች ብሔራዊ ኩራት የሆነዉን አባይን የበሽታ ምንጭ አድርጋ ማቅረቧ ነዉ። ሆኖም ያ እዉነተኛ ችግር ነዉ። የግብፅ የሕይወት ምሰሶ የሆነዉ አባይ መበከሉን ምሁራንም ይናገራሉ።

የማዳበሪያ ፋብሪካ የሆነዉ ኪማ የፋብሪካ ለዓመታት ፍሳሹን ወደአባይ ሲለቅቀዉ ኖሯል። የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽም ወደወንዙ ይገባል። ክርፋቱ ትንፋሽ ያሳጣል። ምንም እንኳን ኪማ አሁን ፍሳሹን ዳግም ወደሚያጣራዉ ተቋም ይላካል ቢልም እዉነታዉ ግን አባይ ግን ኬሚካል ኬሚካል መሽተቱ አለመቆሙ ነዉ።

Ägypten Pumpe mit Dieselbetrieb an einem Bewässerungskanal in der Naehe von Qena am Nil
ምስል Imago/photothek

«እስከ አስዋን ድረስ የሚወርደዉ የአባይ ዉኃ በንፅፅር ሲታይ ንፁሕ፤ የጠራ እና ሰማያዊነቱ ዉብ ነዉ። ነገር ግን ከአስዋን ጀምሮ ያለዉ የአባይ ዉኃ ከማዳበሪያ ፋብሪካዉ ኪማ በኋላ የሆነዉን መመልከት ነዉ።»

አህመድ ዛኪ አቡ ኬንዝ አባይን ለመጠበቅ የሚንቀሳቀስ የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ኃላፊ ናቸዉ።

«በዚያም ላይ ሌሎቹም ፋብሪካዎች ማለትም የስኳር ፋርብሪካ፤ የወረቀት ፋብሪካ፣ የፎስፌት ፋብሪካ፣ የዘይት ፋብሪካ እና ቆሻሻዎች ናቸዉ። ሁሉም የቆሻሻ ፍሳሾች ወደአባይ ነዉ የሚገቡት።በተጨማሪም የበርካታ መኖሪያ ቤቶች የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽም ወደዚያ ነዉ የሚፈሰዉ።ይህ ሁሉ ሰማያዊዉን የአባይ ዉኃ ወደቢጫማነት ለዉጦታ፤e ወደባህር ሲገባም ቡናማ ወይም ጥቁር ይሆናል።»

Ägypten Kairo Nil-Fluss
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Ammar

የግብፅ መንግሥት ይህን ወቀሳ አይቀበልም። ዮም ሳባ በዘገበዉ መሠረት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ኻሊድ ፋህሚ ለሀገሪቱ ምክር ቤት እና የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ኮሚቴ ባቀረቡት ዘገባ የአባይ ዉኃ ጥራት ደረጃ በሚፈቀደዉ መጠን መሆን እንደሚገባዉ አመልክተዋል። በዉኃ ዉስጥ በፋብሪካዎች ፍሳሽ ምክንያት ያለዉ የብክለት መጠንም በአግባቡ መቀነስ እንደሚኖርበት እና ያንንም የሚያደርግ ርምጃ መወሰድ እንደሚገባም ገልጸዋል። የማዳበሪያ ፋብሪያ ኪማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጋማል ኢስማኤል ግን ለብክለቱ ፋብሪካቸዉ ተጠያቂ አይደለም ባይ ናቸዉ።

«የእኛ ፋብሪካ ፅዳቱ የተጠበቀ ነዉ። የፋብሪካዉ ፍሳሽ በዉኃ ማከሚያ ስልት ዉስጥ ነዉ የሚያልፈዉ። ወደ አባይ ከሚወርድ የፋብሪካ ፍሳሽ ጉዳይ ጋር ግንኙነት የለንም። ኪማ ከዚህ ነፃ ነዉ። ሕዝብ እንዲረጋጋምወደ አባይ የሚወርደዉ ፍሳሽ ቆሻሻ እንዳልሆነ መግለጽ እንችላለን።»

የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቹ አህመድ ካዚ ግን ይህን አይቀበሉም። የአባይ ወንዝ ከ90 ሚሊየን ለሚበልጠዉ የግብፅ ሕዝብ ህይወት የሆነዉ ብቸኛ የዉኃ ምንጭ ነዉ። ሰዎች ዉኃዉን ቀድተዉ ሻይ ለማፍላትም ሆን ጥርሳቸዉን ለመታጠብ ከመጠቀማቸዉ በፊት ዉኃዉ አስቀድሞ ሊፀዳ እንደሚገባ የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር GIZ ባለሙያ ያስረዳሉ።

«የዉኃዉ ጥራት እየተበላሸ መሄድ በግብፅ ትልቅ ጉዳይ ሆኗል። ሕጎች ብዙዉን ጊዜ ተግባራዊ አይደረጉም። በርካታ ፋብሪካዎች አሁንም ያልተጣራ ፍሳሻቸዉን ወደወንዙ ይለቃሉ። በብዙ አካባቢዎች የአባይ ዉኃ ለመጠጥነት እንዲዉል ለማድረግ የሚወጣዉ ወጪ የባህር ዉኃ ጨዋማነቱን እንዲቀንስ ለማድረግ ከሚወጣዉ ጋር ተቀራራቢ ሆኗል በቆሻሻዉ ምክንያት።»

Ägypten Nil-Fluss
ምስል Imago/Zumapress

እናም አብዛኛዉ የአባይ ዉኃ ለቤት ዉስጥ ጥቅም የሚዉል አይነት አልሆነም። በዚህ ምክንያትም በተለይ የግብፅ የዳቦ ቅርጫት በሚባለዉ የዴልታ አካባቢ ለእርሻ የሚዉል ሆኗል። እንዲያም ሆኖ የዉኃዉ ፅዳት ጉዳይ አጠያያቂ እና እየወረደ ሄዷል።በዚያም ላይ የአባይ ዉኃ ግብፅ ዉስጥ ተደጋግሞ ጥቅምላይ የሚዉል መሆኑ ዉኃዉን በመጨረሻ ለሚጠቀምበት ችግር የሚያስከትል ሆኖ ተገኝቷል። በግbreና የሚተዳደረዉ መንሱር ቴምር እና ማንቶዎቹን በአሸዋማዉ ደለል ላይ ለማሳደግ ይሞክራል። ግን እየደረቁ ነዉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የወንዙዉኃ የተሸከማቸዉ ቆሻሻዎች እና ኬሚካሎች መሆናቸዉን ይናገራል። ለእርሻዉ የሚጠቅመዉን ዉኃ የሚያገኘዉበአንድ ወገን ከአሌክሳንደሪያ አቅራቢያ ከሚገኘዉ የአባይ ግድብ እና በሌላ ወገን ደግሞ ከሜዲትራኒያን ባህር በሚገባለት ዉኃ ከተፈጠረ ሐይቅ ነዉ። የሐይቁ ዉኃ የብክለት ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ያካሄደዉ ጥናት ያመለክታል። ዉኃዉ በዉስጡ የያዘዉ የናይትሬት ብክለት መጠን የዓለም የጤና ድርጅት ከደነገገዉ ከ20 እጅ እጥፍ ይበልጣል። ይህ ደግሞ የመጣዉ ከየፋብሪካዉ ወደአባይ ዉኃ ከገባዉ ፍሳሽ ነዉ። በዚህ ምክንያትም ዓሳዎች አልቀዋል። የአካቢዉ ነዋሪዎችም ለጉበት በሽታ መዳረጋቸዉ ነዉ የሚነገረዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ