1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት እና ብሪታንያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 18 2011

27ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎችብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት የምትወጣበትን ረቂቅ የብሬግዚት ውል ባለፈው እሁድ ባካሄዱት ልዩ ጉባኤ ቢያጸድቁም ማዘናቸው አልቀረም። ለብሪታንያ መንግሥት የብሬግዚት ድርድር በስምምነት ማብቃቱ እፎይታ ቢሆንም ስምምነቱ ከሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት የገጠመው ተቃውሞ ግን ስጋት ውስጥ ጥሎታል።

https://p.dw.com/p/390zA
EU-Sondergipfel zum Brexit in Brüssel - May und Tusk
ምስል picture alliance/AP/O. Hoslet

ብሬግዚት ፣የአውሮጳ ህብረት እና ብሪታንያ

የብሪታንያ እና የአውሮጳ ህብረት ፍቺ (ብሬግዚት)፣ ረቂቅ ውል ባለፈው እሁድ በ27 ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጸድቋል። ብሪታንያ ከህብረቱ መውጣት የሚያስችላትን ውል ማጽደቁም ያለ ውጣ ውረድ በአንድ ሰዓት ውስጥ ነበር የተጠናቀቀው። ይህም ውሉ ይጸድቃል አይጸድቅም ሲል ልቡ ተንጠልጥሎ ለቆየው ወገን እፎይታን አስገኝቷል። ይሁን እና በፈቃደኝነትም ይባል በእምቢተኝነት ብሪታንያ ህብረቱን ለቅቃ የመውጣትዋ እውነታ የህብረቱን መሪዎቹ ልብ መስበሩ ፣ማሳዘኑ አልቀረም። ብዙውን ጊዜ የአባል ሀገራት መሪዎች ሲገኛኙ የቤተሰብ ዓይነት የህብረት ፎቶ መነሳት እና ሞቅ ያሉ መግለጫዎችን መስጠት የተለመደ ነበር። ይህ ግን ከእሁዱ ጉባኤ በኋላ አልታየም። በአብዛኛዎቹ አመለካከትም ዕለቱ የሀዘን እንጂ የደስታ አልነበረም፤ ።የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር ጉባኤው ካበቃ በኋላ በሰጡት መግለጫ ውሉ የጸደቀበትን እለት አሳዛኝ ብለውታል። ሀዘኑም እርሳቸውን ጨምሮ የብዙዎች እንደሆነ ነው የተናገሩት።

« አንድ ሀገር የአውሮጳ ህብረትን ለቆ ሲወጣ የሻምፓኝ ብርጭቆ ማንሳትም ሆነ ማጨብጨብ አያሰኘኝም ።አሳዛኝ ቀን ነው። ዛሬ ያነጋገርኳቸው ሁሉ ይህን ሀዘናቸውን ነው የገለጹልኝ። ሁሉም በህብረት የተጋራው ነበር።  የሚያስደስት አይደለም  የሚያሳዝን እንጂ። «ጥሩ ውል ነው፣ ግን አሳዛኝ ፣ውሉ አይደለም በጣም አስቸጋሪው። ሆኖም ብሬግዚት ለአውሮጳ ህብረትም ለብሪታንያም አሳዛኝ ወቅት ነው።»

EU-Sondergipfel zum Brexit in Brüssel
ምስል Reuters/Y. Herman

ዩንከር ያሉትን ከደገሙት ውስጥ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ይገኙበታል፤ ያም ሆኖ ሜርክል ብሪታንያ መነጠሏ ቢያሳዝንም መለያየቱ ግን በፖለቲካ ስምምነት ማብቃቱ የሚወደስ መሆኑን ሳያነሱ አላለፉም።

«ብሪታንያ ከ25 ዓመታት በኋላ ከአውሮጳ ህብረት መውጣትዋ አሳዛኝ ነው። እርግጥ ነው ውሳኔውን፣ የብሪታንያ ህዝብ የሰጠውን ድምጽ ማክበር አለብን። ይህን ስንቃወም የነበርነው ለወደፊቱ የአውሮጳ ህብረት እና የብሪታንያ ግንኙነት እንዲሁም ብሪታንያ ከህብረቱ ለምትወጣበት ውል ዛሬ ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ  ላይ መድረሳችን መልካም ነው።ከ27ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት እይታ አንጻር ስርዓቱን ለጠበቀ መለያየት እና ስለ ወደፊቱም ግንኙነት ለመደራደር መሠረት አለ ብለን እናምናለን። »  

EU-Sondergipfel zum Brexit in Brüssel
ምስል AFP/Getty Images/E. Dunand

ጭንቀታቸው የረቂቅ ውሉ መጽደቅ ሆኖ ለከረመው ለብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ የውሉ መጽደቅ እፎይታ አስገኝቶላቸዋል። በወቅቱ የአውሮጳ መሪዎችን ሀዘን ይጋራሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ እንኳን እንዲያውም ነበር ያሉት። ይሁንና ሆዳቸው የባባ ለመሰለው የቀድሞ ማህበረተኞቻቸው አይዟችሁ ተጽናኑ ዓይነት መልዕክት ነው ያስተላለፉት።

«በዚህ ወቅት ላይ አንዳንድ የአውሮጳ መሪዎች ማዘናቸውን ተገንዝቤያለሁ። በዚሁ ወቅት ላይ ብሪታንያ ውስጥም የሚያዝኑ አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ።ሆኖም እኔ ይህን የምመለከተው አሁን ወደ ሚቀጥለው ደረጃ የምንሸጋገርበት ወደፊት የምንጓዝበት ወቅት ነው። እኔ ስለ ብሪታንያ የወደፊት እጣ ሙሉ ተስፋ አለኝ። ከአውሮጳ ህብረትም ጋር በዚህ ጥሩ ውል እንቀጥላለን።ወዳጆች እና ጎረቤቶች ሆነን እንዘልቃለን። ብዙጊዜ ብዬዋለሁ። የአውሮጳ ህብረትን ለቀን እንወጣለን። ከአውሮጳ ግን አንወጣም። ከአውሮፓ ፣ ሰፋ ባለ መልኩ ደግሞ ከአውሮጳ ህብረት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እና ግንኙነታችን እንቀጥላለን»

ሜይ እንዳሉት በብራሰልሱ ጉባኤ ውሉ በስምምነት መጽደቁ የአንድ ምዕራፍ ፍጻሜ ነው። በሌል በኩል ደግሞ ለብሪታንያ መጻኤ እድል ወሳኝ የሚባለው የሀገር ውስጥ ክርክር የሚጀመርበት ወቅት ነው።

ለሜይ አሁን አሳሳቢው ጉዳይ ከዚህ በኋላ በብሪታንያ ሊከተል የሚችለው እርምጃ ነው። ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የፈጀው የብሬግዚት ድርድር ከሳምንት በፊት በረቂቅ ውል ሲጠናቀቅ የሂደቱ ማብቃያ የመቃረቡ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባው ነበር። ከዚያ ይልቅ በብሪታንያ በውሉ ያልተስማሙ የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ሌላ ችግር ሊያመጣ የመቻሉ ስጋት ያነጋግር ይዟል። ብሬግዚት ተግባራዊ እንዲሆን  የብሪታንያ ምክር ቤት ውሉን ማጽደቅ ይኖርበታል። ይህ ይሳካ አይሳካ ከወዲሁ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። ሆኖም ጉዳዩ ከወዲሁ ያሳሳበው የአውሮጳ ህብረት ለብሪታንያ ፖለቲከኞች መልዕክት አስተላልፏል። የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር ለብሪታንያ ፓርላማ ባስተላለፉት ጥሪ ብሪታንያ ም ሆነች የአውሮጳ ህብረት ከዚህ የተሻለ ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደማይችሉ ነበር ያስረዱት።

EU-Sondergipfel zum Brexit in Brüssel
ምስል Reuters/O. Hoslet

«በብሪታንያ የህግ መምሪያ ምክር ቤት ውሉን የሚያጸድቁ ይህ ከግናዛቤ እንዲስገቡ እጠይቃለሁ። ውሉ ለብሪታንያ ባለው ሁኔታ ሊደረስበት የሚችል በጣም አግባቢ ውል ነው። ለአውሮጳ ህብረትም እንዲሁ ይህ ብቸኛው ሊደረስበት የሚችል አግባቢ ውል ነው። »

የብሪታንያ ፓርላማ አባላት በብሬክዚት ላይ የያዙት አቋም የተለያየ ነው። ብሬግዚትን ከሚደግፉት ከአውሮጳ ህብረትም ጋር ትስስሩ ይቋረጥ ከሚሉት አንስቶ፣ አግባቢ መፍትሄ እንዲፈለግ የሚወተውቱት የአውሮጳ ህብረት ደጋፊዎችም ይገኛሉ። ሁለቱም ወገኖች ውሉን ይጠሉታል። በተለይ ብሪታንያ በመጋቢት 2019 በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ህብረቱን ከተሰናበተች በኋላ እስከ 2020 መጨረሻ ድረስ በተያዘው የሽግግር ጊዜ ለህብረቱ ህጎች እና ደንቦች የምትገዛ ሆና ግን በማናቸውን ጉዳዮች ላይ ድምጽ እንዳትሰጥ መከልከልዋ ነው ዋናው ተቃውሞአቸው። የአውሮጳ ህብረት የብሬግዚት ዋነኛ ተደራዳሪ ሚሼል ባርንየ ግን ውሉ ብሪታንያን ፈጽሞ የሚጎዳ እንዳይደለ ነበር እሁድ እለት በጥቅሉ ያስረዱት።

«ዛሬ በርግጥ ከብሪታንያ ጋር ያማያዳላ እና ሚዛናዊ ስምምነት ላይ ነው የደረስነው። ባለው ሁኔታ ሊደረስበት የሚችል በጣም አግባቢ ውል ነው። ውስብስብ ልዩ እና አስቸጋሪ በነበሩት ድርድሮች ከብሪታንያ ጋር ገንቢ ሥራዎች ነው ያከናወነው። በፍጹም ፀረ ብሪታንያ ሥራ አልተሰራም፤ በፍጹም።ብሪታንያም ከኛ ጋር ያከናወነችው ሥራ ገንቢ ነበር።ለብሪታንያ ቡድን ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ስምምነቱ አሁን መጽደቅ አለበት ሁሉም ሃላፊነቱን የሚወስድበት ጊዜ አሁን ነው። የዛሬው ስምምነት የወደፊቱን ጥብቅ እና ወዴት እንደሚወስደን የማይታወቅ ግንኙነታችን በሚመለከት ለምናካሂደው ድርድር መተማመኛ እንዲኖረን  የሚረዳ እና የሚያስፈልገን ነው። ብዙ ጊዜ እንደተናገርኩት ከብሪታንያ ጋር አጋር እና ወዳጅ ሆነን እንዘልቃለን።»

UK Großbritannien - Premierministerin Theresa May verteidigt Brexit-Vertrag im Unterhaus
ምስል picture-alliance/dpa/PA Wire

የብሪታንያ ህግ መምሪያ ምክር ቤት 650 መቀመጫዎች አሉት። አንድ ሃሳብ እንዲጸድቅ ቢያንስ 318 ድምጽ ያስፈልጋል። የሜይ ወግ አጥባቂ ፓርቲ 315 የምክር ቤት መቀመጫ ነው የያዘው። ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ ውሉን እንቃወማለን ብለዋል። ከዚህ ሌላ የሜይ አጋር የሰሜን አየርላንድ ዴሞክራቲክ ዩንየኒስት የተባለው ፓርቲ ውሉን ይቃወማል። ዋነኛው ተቃዋሚ ሌበር ፓርቲም እንዲሁም ረቂቅ ውሉን አይቀበልም። ከሁለት ሳምንት በኋላ የብሪታንያ ምክር ቤት የሚያሳልፈው ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችልም ለመገመት አሁን አስቸጋሪ ቢሆንም በተነሳበት ተቃውሞ ማለፉ ያጠራጥራል። ይሁን እና ሜይ በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ ለማካሄድ አቅደዋል። በርሳቸው አስተያየት ውሉን አለመቀበል ወደ ባሰ ክፍፍል እና አለመተማመን የሚወስድ ነው የሚሆነው። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ህዝቡን ፓርላማቸውን ለማሰመን የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

«የብሪታንያ ህዝብ በብሬግዚት ጉዳይ ላይ በመከራከር ጊዜውን ማጥፋት አይፈልግም የሚፈልገው። እንደ ሀገር አንድ የሚያደርገንን ጥሩ ውል ነው።  ይህን ውል ደግሞ ወd ህግ መምሪያ ምክር ቤት እወስደዋለሁ፤፤አስተማማኝ እና ከሁሉም የተሻለ ውል እንዳገኝን በሙሉ ተስፋ አቀርባለሁ። በፓርላምውም ሆነ ከዚያም ባሻገር በሙሉ ልብ የውሉን ምንነት እና አስፈላጊነት አስረዳለሁ። ዘመቻውን በናፍቆት ነው የምጠብቀው ።»

ሜይ ብሬግዚትን በተጀመረው ሂደት ለማሳካት የራሳቸውን ጥረት ቀጥለዋል። አሁንም ግን ጥያቄው ይሳካላቸዋል ወይ የሚል ነው። ይህ ካልሆነላቸው ነገሮች መወሳሰባቸው እንደማይቀር ነው የሚነገረው። ያለቀለት ወደ ኋላ የማይመለስ የተባለው የብሬግዚት ውል በብሪታንያ ፓርላማ ተቀባይነት ካላገኘ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው የማይቀር ነው የሚሉ አሉ። አዲስ ህዝበ ውሳኔ እንዲጠራም ሊጠይቅ እንደሚችልም ይገመታል። በመካከሉ ደግሞ ብሪታንያ ለመፍትሄ ፍለጋ ጊዜ ለመግዛት ከአውሮጳ ህብረት የምትወጣበት ጊዜ እንዲራዘም ልትጠይቅ ትችላለች የሚልም መላ ምት አለ። ሁሉንም የዛሬ ሁለት ሳምንት እና ከዚያ በኃላ ባሉት ጊዜያት የምናየው ይሆናል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ