1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮች በርዳታ እጦት እየተሰቃዩ ነዉ

ማክሰኞ፣ መስከረም 15 2016

ከአፋር፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ እና ከደቡብ ክልሎች ቀያቸውን ጥለው ለመፈናቀል መገደዳቸውን የገለፁ ያነጋገርናቸው ዜጎች እርዳታ ማግኘት ካቆሙ ወራቶች ተቆጥረዋል። በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁስሳዊ ጉዳት አድርሷል ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስም አስከትሏል

https://p.dw.com/p/4WpnZ
ጃራ የሰፈሩ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ርዳታ ከተቋረጠባቸዉ ወራት መቆጠሩን ይናገራሉ
በአብዛኛዉ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለዉ ጃራ-አማራ ክልል ከሰፈሩ ተፈናቃዮች በከፊልምስል Alemnew Mekonnen/DW

 

ኢትዮጵያ ውስጥ በእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት፣ በኃይል እንዲሁም በድርቅ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የዕለት እርዳታ ጠባቂ የሆኑ ሰዎች እርዳታ ማግኘት ፈተና እየሆነባቸው መምጣቱን ለዶቼ ቬለ ገለፁ።ተፈናቃዮችና አዲስ ዓመት በመቐለ
ከአፋር፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ እና ከደቡብ ክልሎች ቀያቸውን ጥለው ለመፈናቀል መገደዳቸውን የገለፁ ያነጋገርናቸው ዜጎች እርዳታ ማግኘት ካቆሙ ወራቶች ተቆጥረዋል። 
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁስሳዊ ጉዳት አድርሷል ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስም አስከትሏል" ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ምብቶች ኮሚሽን "ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በቂ የምግብ ድጋፍ፣ የንፁሕ መጠጥ ውኃ ፣ የህክምና አገልግሎት ፣ እየቀረበ አለመሆኑን ባደረገው ክትትል መገንዘቡን መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ . ም ባወጣው የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፓርቱ ገልጿል።
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ከወራት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት መረጃ "ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው 22.1 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ውስጥ 9.9 ሚሊዮን ያህሉ በመንግሥት የአስቸኳይ ድጋፍ ይደረግለታል፣ ቀሪ 11 ሚሊዮን ገደማ ያህሉ ደግሞ ረጂ ድርጅቶች በሚሰጡት ድጋፍ የሚሸፈን ነው" ብለው ነበር።// 

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ተፈናቅለዉ መንዲ ከሰፈሩ ተፈናቃዮች በከፊል
ከምዕራብ ወለጋ ዞን የተፈናቃሉ ነዋሪዎች ምስል Negassa Dessalegen/DW

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ? 

በፌዴራል መንግሥቱ እና አጋሮቹ እንዲሁም በሕወሓት መካከል በነበረው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው ከተፈናቀሉት በርካታ ዜጎች መካከል ተምቤን አቢ አዲ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የተጠለሉት አቶ ብርሃነ አንደኛው ናቸው።
"እርዳታ የሚባል ወደ ዘጠኝ ወራችን ነው።እህል የሚባል አላገኘንም። ሰው በረሃብ ምክንያት እያለቀ ነው" 

አፋር ውስጥ በተለይ አብዓላ ጦርነቱ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ስፍራዎች ቀዳሚው ነው። በወቅቱ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ስለወደመች የአካባቢው ነዋሪዎች ኑሯቸው በድንገት ተማሳቅሎ ነበር። አቶ አብርሃም አንደኛው ናቸው።
"እርዳታ እስካሁን አምስት ወራችን ምንም የለም። እስካሁን እየጠበቅን ነው ያለነው"። 

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተፈናቃዮች መቸገራቸዉን አስታዉቋል
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መስሪያ ቤትምስል Solomon Muchie/DW

ጉጂ አካባቢ በነበረው ግጭት ከለመለመው መኖሪያቸው ተፈናቅለው ችጋር እየጠበሳቸው መሆኑን የገለፁ ስሜ ይቆይ ያሉ አስተያየት ሰጪ የምግብ ዋስትናቸው ቢናጋ በዚሁ ምክንያት ነው። 

ኢሰመኮ ይህንን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ 

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁስሳዊ ጉዳት አድርሷል፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስም አስከትሏል" ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአብዛኞቹ ክልሎች በድርቅ እና በግጭት ምክንያት በርካታ ሕዝብ እርዳታ ጠባቂ መሆኑን ገልጿል። "ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በቂ የምግብ ድጋፍ፣ የንፁሕ መጠጥ ውኃ ፣ የህክምና አገልግሎት፣ እየቀረበ አለመሆኑንም ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል መገንዘቡን መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ . ም ባወጣው የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፓርቱ ገልጿል። ከኦሮሚያ ክልል በተለይም ወለጋ ዞኖች በርካታ ሺህ ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ገብተዋል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ቤታቸው በሕገ ወጥ መንገድ የተሰራ ነው በሚል የፈረሰባቸውም እንዲሁ። ኑርዬ የተባሉ የወለጋ ተፈናቃይ አሁን ባሉበት ቦታ 
"በጣም ነው የተቸገርነው፣ የተሰቃየነው" ብለዋል። 

ተፈናቃዮቹ የባሕርዳር መታወቂያ ስለሌላቸዉ ርዳታ መከልከላቸዉን ተናግረዋል
ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለዉ ባሕርዳር የሰፈሩ ተፈናቃዮችምስል Alemenew Mekonnen/DW

የረድዔት ድርጅቶች ድጋፍ መቋረጥ እና የተረጂዎች ቁጥር 

የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ( USAID ) እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ( WFP ) በትግራይ ክልል እርዳታ ተዘርፎ ላልተገባ ዓላማ ውሏል በሚል የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቋረጣቸው ችግሩን አባብሶታል። ይህ ውሳኔ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ሀገራቸውን ሸሽተው ኢትዮጵያ ውስጥ ለተጠለሉ ስደተኞችም አደጋ ደቅኗል። ለስደተኞች ይቀርብ የነበረው ሰብዓዊ ድጋፍ ከጊዜ ጊዜ እየቀንሰ መጥቶ በአሁኑ ሰዓት የምግብ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ መቆሙን ከስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ማረጋገጥ ችለናል።
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የእርዳታ አቅርቦቱ ምን መሳይ ይሆን የሚለውን እንዲመልስ በተደጋጋሚ ጥረት ባደርግም ለጊዜው ኃላፊዎቹን ማግኘት አልቻልኩም። የተቋሙ ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ከወራት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው 22.1 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ውስጥ 9.9 ሚሊዮን ያህሉ በመንግሥት የአስቸኳይ ድጋፍ እንደሚደረግለት፣ ቀሪው 11 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ የተራድዖ ድርጅቶች በሚሰጡት ድጋፍ ጎርሶ የሚያድር መሆኑን ገልፀው ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር