1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታላላቅ የተፈጥሮ አደጋዎች በ2018

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2011

ትናንት እኩለ ሌሊት ሲሆን ተሰናብቶ ወር ተራውን ለ2019 ዓ.ም ያስረከበው ጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ.ም የተፈጥሮ አደጋዎች በአሳሳቢ ፍጥነት እና መጠን የተከሰቱበት ዓመት እንደነበር ተመዝግቦለታል። እንዲህ ያሉ መረጃዎች ያሰባሰቡ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት በየሳምንቱ በሚባል መጠን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሰውን ሕይወት ያጠፉ ውድመቶች ደርሰዋል።

https://p.dw.com/p/3Arpu
USA Waldbrände in Kalifornien
ምስል Imago/Xinhua/Zhao Hanrong

የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ሱናሚ፣ ሰደድ እሳት እና እሳተ ጎሞራ

የዩናይትድ ስቴትሷ ግዛት ደቡብ ካሊፎርኒያ የሰደድ እሳት ያቃጥላት የጀመረው ገና በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ማለቂያ ወር ታኅሣሥ አንስቶ ሲሆን፤ እሳቱ እስከ 2018 ጥር ወር ዘልቆ ከ281 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት አቃጥሏል። የሁለት ሰው ሕይወትም ጠፍቷል። ቆየት ብሎ በሐምሌ ወርም በ17 የተለያዩ ስፍራዎች የተነሳው እሳት ከሰሜን እስከ ደቡብ ካሊፎርኒያ በሚገኙ ስፍራዎች ላይ ጉዳት አድርሷል። ከ16 የሀገሪቱ ግዛቶች የተውጣጡ 12 ሺህ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ለማጥፋት የተረባረቡበት የሰደድ እሳት 103 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን አቃጥሏል። 657 ቤቶችን አውድሟል። ሰፊ አካባቢዎችን ባዳረሰው በዚህ የእሳት አደጋ የሞቱት ስምንት ሰዎች ናቸው።

በድጋሚም በኅዳር ወር መጀመሪያ ቀናት አንስቶ ለሳምንታት ሰሜን እና ደቡብ ካሊፎርኒያ ግዛቶችን ያዳረሰው የሰደድ እሳት ወደ 230 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። በተለያዩ ሦስት ቦታዎች ላይ የተነሳው እሳት መንስኤው አለመታወቁ ነው የተነገረው። በወቅቱ የከፋ የተባለው የሰደድ እሳት ፓራዳይዝ የምትባለውን ከተማን ሙሉ ለሙሉ ያወደመው እና 27 ሺህ ነዋሪዎችን ከቤታቸው ያባረረው ነው። 150ሺህ ሄክታር መሬትን ያካለለው እሳት የ88 ሰዎች ሕይወትም ቀጥፏል። በደቡብ ካሊፎርኒያ የሚኖሩት ወገኖችን ይበልጥ ለጉዳት የዳረገችው ሳንታ አና የሚል መጠራ የተሰጣት ነፋስ እሳቱን በማዛመት ተፅዕኖውን አክብዳዋለች። በተጠቀሱት አካባቢዎች በሰደድ እሳቱ ሰበብ በጥቅሉ 91 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ15 ሺህ የሚበልጡ ሕንፃዎችን እና መኖሪያ ቤቶችም ወድመዋል።

US-FIRES
ምስል AFP/Getty Images

በጥቅምት ወር በአስረኛው ቀን የተከሰተው ማይክል በሚል መጠሪያ የተሰየመው ማዕበል እና ውሽንፍር በፍሎሪዳ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ላይ ባስከተለው ጉዳት ቢያንስ ለስድስት ሰዎች ህልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል። በሰዓት 155 ሜትር የሚምዘገዘገው ነፋስ እና ጎርፍ የደቡብ አላባማ እና ጆርጂያ ነዋሪዎችንም ስጋት ላይ የጣሉ ነበሩ። በተለይ ፍሎሪዳ ላይ ሀኪም ቤቶች እና ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል፤ መጓጓዣዎችን አሰናክሏል፤ ከአንድ ሚሊየን የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶችን ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተጓጉሏል። በተለይ ሃኪም ቤቶች እና የአዛውንቶች መጦሪያ ስፍራዎች ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም።

«እየተነፈሰች አይደለም።»

ይህ እንግዲህ ለአሜሪካኑ የአስቸኳይ ርዳታ መጠየቂያ አድራሻ በስልክ ከደረሱ የድረሱልኝ ጥሪዎች አንዱ ነበር። በአዛውንቶች መከባከቢያ ስፍራ ላይ በደረሰው አደጋ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ በዚህ ኃይል የሚንቀሳቀሱ የህክምና መሣሪያዎች ሁሉ ቀጥ አሉ። በዚህ መዘዝም የ14 አዛውንቶች ሕይወት አለፈ።

Waldbrände in Kalifornien
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Locher

ከዩናይትድ ስቴትስ ሳንወጣ በመስከረም አጋማሽ በሀገሪቱ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ የተከሰተው የባሕር ላይ ሞገድ እና ውሽንፍር በ24 ሰዓታት ውስጥ የመሬት መናድን ማስከተሉ ተመዝግቧል። ሰሜን ካሮላይና ላይ ቤቶችን እና ጎዳናዎችን ያጥለቀለቀው ጠንካራ ማዕበል በተፈጥሮ ወቅቱን ጠብቆ በአካባቢው የሚከሰት የባሕር ማዕበል አካል ነው። ምንም እንኳን የነፋሱ ፍጥነት ከተገመተው መቀነሱ ቢነገርም 90 ሜትር በሰዓት የተወረወረው ወጀብ በአካባቢው ኃይለኛ ዝናብ አስከትሎ ሰሜን እና ደቡብ ካሮላንናን በጎርፍ አጥለቅልቆታል። በዚህ የተፈጥሮ አደጋ ሰበብ የኃይል ማመንጫዎች  ከሥራ ውጭ ሲሆኑ እንደ ሜርኩሪ፤ አርሰኒክ እና ሊድ የመሳሰሉ መርዛማ ኬሚካሎች ከተከማቹበት ስፍራ በጎርፉ ተጠርገው በአቅራቢያ የሚገኙ ወንዞችን እንዳይመርዙ ባለስልጣናት ስጋታቸውን ሲገልፁ ተሰምተዋል። ይህ አደጋም ከ42 ሰዎች በላይ ገድሏል።

በምዕራብ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው እና የዩናይትድ ስቴትስ መሆኗ የሚነገረው ጉዋም ደሴት በመስከረም መጀመሪያ ቀናት ያሰጋት ከፍተኛ ደረጃ የነበረው ማንግኩት የተሰኘው የባሕር ማዕበል፤ ፊሊፒንስ እና ደቡብ ቻይናን ሳይቀር ገርፏል። በዚህ የተፈጥሮ አደጋ ቢያንስ የ4 ሚሊየን ሰዎችን ኑሮ ያናጋ መዘዝ ነው የደረሰው። 69 ሰዎችም ሕይወታቸውን ማጣታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ሲነገር ሰንብቷል። በሰዓት 107 ሜትር ፍጥነት የነበረው ነፋስ በሚሊየን የሚቆጠሩትን ከመኖሪያቸው ከማፈናቀል ሌላ እጅግ በርካቶችም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳያገኙ አሰናክሏል። 

Indonesien Erdbeben & Tsunami | Zerstörung in Palu, Sulawesi
ምስል Reuters/A. Perawongmetha

ሌላዋ በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ,ም ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ ያስተናገደችው ሀገር ኢንዶኔዢያ ናት። በቅርቡ ደግሞ በታኅሣስ ወር ማለቂያ ቀናት የደሴት ግዛቶቿ በሆኑት ጃቫ እና ሱማትራ የደረሰው አደገኛው የባሕር ማዕበል ሱናሚ ከ200 ለሚበልጡ ሰዎች ህልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል። ሱናሚውን የቀሰቀሰው በሁለቱ ደሴቶች መካከል የሚገኘው አናክ ክራካታዑ በተሰኘው ተራራ ላይ የፈነዳው እሳተ ጎሞራ እንደሆነ ይገመታል። በዚህ ሰበብም 1,500 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ 22,000 የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። የኢንዶኔዢያ ፕሬዝደንት ጆኮ ዊዶዶ ሀገራቸው አሁን ባለችበት ደረጃ በአካባቢው ነቅተው የሚገኙ እምቅ የእሳተ ገሞራ ክምችቶች መቼ ሊፈነዱ እንደሚችሉ ግምት መስጠት የሚያስችል ቴክኒዎሎጂ እንደሌላት ተናግረዋል። ይህ ባለመኖሩም ነው እሳተ ጎሞራው በፈነዳበት አካባቢ የሚኖሩ ወገኖችም ሆኑ ሀገር ጎብኚዎች ከደረሰው የሱናሚ አደጋ አስቀድመው ማምለጥ ያልቻሉት።

መስከረም ማለቂያ ገደማ የኢንዶኒዢያዋ ደሴት ሱላዉሲ በተለይ ደግሞ ማዕከላዊ ክፍለ ሀገሯ ፓሉ በመሬት መንቀጥቀጥ እና እሱን በተከተለው ሱናሚ ተመትታለች። 7,5 የተመዘገበው የመሬት ነውጥ በመሬቱ ውስጣዊ  የአቀማመጥ ገጽታ ላይ ቦታ መለዋወጥን ማምጣቱ ሱናሚ እንዲከተል እንዳደረገ ነው የተነገረው። በአደጋው ከ844 የሚበልጡ ሰዎች ሞተዋል። ጣምራው የተፈጥሮ አደጋ በግምት የ2,4 ሚሊየን ሰዎችን ሕይወት አናግቷል። በወቅቱ የሕይወት አድን ሠራተኞች ዋና ፈተና የነበረው ሕይወታቸው እያለ በፍርስራሽ ሥር የተቀበሩ ሰዎችን የማትረፉ ጥረት ነበር። የመሬት መንቀጥቀጡ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ በማድረጉ መቶ ሜትር ያህል ከፍታ ኖሮት የመጣውን የሱናሚ ማዕበል ማስጠንቀቂያ ብዙዎች መስማት አልቻሉም። ይህም ለሟቾቹ ቁጥር መበርከት ዋና ምክንያት ሆኗል።

Indien Andamanen North Sentinel Island
ምስል picture-alliance/AP Photo/G. Singh

በዚሁ በጥር ወር ጀርመን፣ ፈረንሳይ፤ ቤልጂየም፤ ኔዘርላንድስ፣  እና ፖላንድ በከባድ አውሎ ነፋስ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አውሎ ነፋሱ ቤቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱ ሌላ፤ ዛፎችን ከሥራቸው እየመነገለ ባገኘው ስፍራ ሲጥል፤ መንገዶችን እና የባቡር ጉዞዎችን ሲበጠብጥ፤  ታይቷል። በጥቅሉ በዚህ ክስተት 13 ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቧል። በየካቲት ወር ፓፓዋ ኒው ጊኒ 7,5 በተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ስትመታ በሺህ የሚገመቱ ሰዎች መኖሪያቸው ወድሟል። 160 ሰዎችን የገደለው ይህ የተፈጥሮ አደጋ በሀገሪቱ ላይ የ61 ሚሊየን ዶላር የንብረት ውድመት ማድረሱ ተመዝግቧል። በዚሁ ወር ደቡባዊ ሜክሲኮ ላይ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ 13 ሰዎች ሲገደሉ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶች ወድመዋል። ታይዋንም በዚሁ ወር በሬሽተር መለኪያ 6,4 በተመዘገበ የመሬት ነውጥ 17 ሰዎች ሞተውባታል። የመሬት መንቀጥቀጡ ቤቶችን ከማፈራረሱ በተጨማሪ ከ40 ሺህ የሚበልጡትን የውኃ መስመራቸውን ሰባብሮ አቅርቦቱን አሳጥቷቸዋል። ባጠቃላይም ታይዋን ላይ የ21 ሚሊየን ዶላር ጉዳት አድርሷል።

Deutschland Sturmtief Friederike Nordrhein-Westfalen
ምስል picture-alliance/Photoshot/J. Bywaletz

መጋቢትም ያለ ተፈጥሮ አደጋ አላለፈም። በወሩ መጨረሻ ላይ ፊጂ ደሴት አውሎ ነፋስ ባስከተለባት አደጋ አራት ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፤ በርከት ያለ ንብረት ወድሟል፤ መንገዶች ተዘጋግተዋል፤ ሁለት ሺህ ገደማ ነዋሪዎችም አካባቢያቸውን ለቅቀው ለመፈናቀል ተዳርገዋል። በዚሁ ወር የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ማሻቹስቴትስ ጨምሮ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ በርከት ያሉ ቦታዎች በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል። በወቅቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ ከሁለት ሚሊየን የሚበልጡት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል። ቁጥሩ በውል ያልተገለጸ ሕፃና መኖሪያ ቤትም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

በግንቦት ወር ሃዋይ በእሳተ ጎሞራ ያበጠ አካባቢ ሲተነፍስ የእሳት ፍሳሽ ያስከተለ ሲሆን በተከታታይ የተፈጠሩት አነስተኛ ክፍተቶች የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳስከተለ፤ ያ ደግሞ ጠንከር ያለ የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ እንዳመጣ ተመዝግቧ። ሃዋይ ላይ የደረሰው በሬሽተር እስኬል 4,4 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው እሳተ ገሞራ ወደ ሰማይ 10 ሺህ ጫማ ድረስ መውጣቱም ተነግሯል። በ24 ሰዓት ውስጥ በዚሁ ስፍራ በሰኔ ወር ላይ 500 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ መድረሱ ተነግሯል። በዚህ ሰበብ 82 ሕንፃዎች እና 279 መኖሪያ ቤቶች ሲወድሙ፤ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከአካባቢው ተፈናቅለዋል።

Staubsturm in Indien
ምስል Reuters/A. Abidi

በዚሁ በግንቦት ወር ከተለመደው እጅግ ከፍተኛ ሙቀት በተመዘገበባት ሕንድ ኃይለኛ ነፋስ እና መብረቅ ቤቶችን አውድመዋል ከብቶችንም ገድለዋል። ዛፎችን ከሥራቸው የገነዳደሰው ይህ አዋራ የቀላቀለ ኃያል ነፋስ ከ125 በላይ ሰዎች መሞትም ምክንያት ሆኗል። ሰኔ ወር ላይ የጓቲማላዋ ላይ ያልተጠበቀ የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ ሁለት ሚሊየን ሰዎችን አፈናቅሏል። እሳተ ጎሞራው ያስከተለው አመድ እና አቧራ አካባቢውን ሞልቶት ሰንብቷል። መንገዶች እና ድልድዮች ተሰባብረዋል፤ የ33 ሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል።

ጃፓን ሐምሌ ወር ላይ ደቡብ ምዕራብ ግዛቷን የመታው ከባድ ዝናብ ጎርፍ እና የመሬት መናድን አስከትሎባታል። ከወትሮው የዝናብ መጠን በሦስት እጅ ይበልጣል የተባለው ይህ ዝናብ ለአንድ መቶ ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል። ቤቶችን አውድሞ አካባቢውን በጭቃ የሞላው የተፈጥሮ አደጋ በሺህዎች የሚገመቱ ነዋሪዎችን ካለ መጠለያ አስቀርቷል። ወደ ሁለት ሚሊየን የተገመቱ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው መሰደድ ግድ ሆኖባቸዋል።

Japan Überschwemmung Flut
ምስል Getty Images/AFP/Y. Tsuno

ሃዋይ ነሐሴ ውስጥ ያጋጠማት ሌን የተባለው ውሽንፍር እንደከባድ የባሕር ላይ ሞገድ ተጠናክሮ ቢጀምርም ከአምስት ቀናት በኋላ ኃይሉን እየቀነሰ በመሄዱ ያስከተለው ጉዳት ቢኖርም ከሌሎቹ ጋር ሲተያይ ቀነስ ብሏል። እንዲያም ሆኖ ደሴቲቱ አስቀድሞ የመታት ውሽንፍር የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል እንደሚችል በማስጋቱ ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወሩ አስገድዷል። መንገዶችን የጠራረገው ጎርፍ ቤቶችን ጎድቷል የሰደድ እሳትንም ቀስቅሷል። አድማጮች ጎርጎዮሳዊው 2018 እነዚህን አስተናገዶ ለተረኛው 2019 አስረክቧል። ተፈጥሮ ምን ደግሳለች? ከቆየን የምናየው ይሆናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ