1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትራምፕ ዳግም ሊመረጡ መቻላቸው በአውሮጳ ያሳደረው ስጋት

ማክሰኞ፣ ጥር 21 2016

መጪውን ምርጫ ካሸነፉ ለአውሮጳ ሀገራት የኔቶ አባላት ወታደራዊ ድጋፍ ይሰጡ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ «እኛን በተገቢው መንገድ የሚይዙን ከሆነ ነው የምንደግፋቸው»ማለታቸው ተሰምቷል። ኔቶንና የኔቶ አባል የአውሮጳ ሀገራትን በሚመለከት ለተጠየቁትም «ኔቶ ሀገራችንን ተጠቅሞባታል።የአውሮጳ ሀገራትም ተጠቅመውባታል » ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4bqcr
Vorwahlen USA 2024 - New Hampshire Donald Trump
ምስል Matt Rourke/AP/picture alliance

ትራምፕ ዳግም ሊመረጡ መቻላቸው በአውሮጳ ያሳደረው ስጋት


የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ  በመጪው ህዳር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ለመፎካከር ባለፈው ሳምንት በኒው ሀምሻየር የተካሄደውን  ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ዳግም በፕሬዝዳንትነት መመረጣቸው አይቀርም የሚሉ ድምጾች እየጎሉ ነው። የህዝብ አስተያየቶችም ሆኑ የፖለቲካ ተንታኞች ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ የመመለስ እድላቸው የሰፋ በመሆኑ ይስማማሉ። ትራምፕ ዳግም ሊመረጡ መቻላቸው ለአብዛኛው አውሮጳ ፈታኝ ክስተት መሆኑ እንደማይቀርም ያምናሉ ። በዶቼቬለው የማትያስ ቮን ሀይም ዘገባ መሠረት ሊሳካ ይችላል ለተባለው ለሁለተኛው የዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ዘመን የአውሮጶ ሀገራት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ከአሁንና ከቀድሞ የአውሮጳ ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው።

የአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ፕሬዝዳንት ክርስቲን ላጋርድ ዶናልድ ሊመረጡ መቻላቸውን ለአውሮጳ «ግልጽ ስጋት» ብለውታል።አነጋጋሪው የትራምፕ አስተያየትና የአውሮጳ ሕብረት የቤልጅየሙ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ደ ክሩ ደግሞ «ትራምፕ በ2024 አሜሪካ ትቅደም የሚለውን አስተሳሰብ ይዘው ከመጡ ከመቼውም በላይ አውሮጳ ራስዋን መቻል አለባት ሲሉ አሳስበዋል።የቀድሞው የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ካርል ቢልድት ፣ትራምፕ ዳግም ከተመረጡ ሰፊ ዓለም አቀፍ መዘዞችን ሊያስከትል እንደሚችል ተንብየዋል። የብራሰልሱ የዶቼቬለ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ እንዳለው ሌሎችም በዚህ የሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ስጋቶቻቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ትራምፕ በ2018 ከቡድን ሰባት አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በካናዳ
ትራምፕ በ2018 ከቡድን ሰባት አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በካናዳ ምስል Jesco Denzel/Bundesregierung/dpa/picture alliance

ትራምፕ ቢመረጡ አውሮጳን የሚያሰጉት አሜሪካ ለዩክሬን ጦርነት የምትሰጠውን ድጋፍ ልትቀንስ መቻሏ እና ከዚህ ቀደም ከሀገራቸውን ከኔቶ አስወጣለሁ ሲሉ መዛታቸው በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

ሱድሀ ዴቪድ ዊልፕ በዩናይትድ ስቴትስ ፣በጀርመን መንግሥትና በአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን የሚደገፈው የጀርመን የማርሻል እርዳታ የበርሊን ቢሮ ሃላፊ ናቸው። ዶቼቬለ የትራምፕ ዳግም ወደ ዋይት ሀውስ መምጣት ለአውሮጳ ምን ያህል አስጊ እንደሆነ የጠየቃቸው ዴቪድ ዊልፕ ዋነኛው ስጋት የአውሮጳ ወታደራዊ ብቃት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።ዊልፕ  ለዚህ መፍትሄው አውሮጶች ወታደራዊ ሚናቸውንና ኤኮኖሚያቸውን በማጠናከር አጋሮቻቸውን በማስፋት ራሳቸውን ብቁ ማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
"አውሮጳ በወታደራዊ እንቅስቃሴ በተለመደው ሁኔታ ጠንካራ ተዋናይ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል። ይህ ከሆነ በጎረቤት ሀገራት የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ያስችለዋል። ይህም ከፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት የሚመጡ የውጭ ስጋቶችን መቀነስ ያስችለዋል። በበሁለተኛው የትራምፕ የስልጣን ዘመን ሊወሰዱ የሚችሉ ተከላካይ እርምጃዎችን ለመቋቋም ኤኮኖሚውን በማጠናከርም ከእስያ ሀገራት ጋር ጠንካራ አጋር መሆን ያስችለዋል።» 

ትራምፕ ባሸነፉበት በኒው ሀምሻየሩ ምርጫ ድምጽ የሰጡ የትራምፕ ደጋፊ
ትራምፕ ባሸነፉበት በኒው ሀምሻየሩ ምርጫ ድምጽ የሰጡ የትራምፕ ደጋፊ ምስል DW


ሌላው የአውሮጳ ሀገሮች ስጋት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባላቸው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የትራምፕ መመረጥ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ነው። ይህም ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በንግድ ልውውጡ ዘርፍ ተግባራዊ ያደረጓቸውን ጫናዎች መነሻ ያደረገ ነው። በስልጣን ዘመናቸው ሀገራቸው ከፓሪሱ የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ስምምነት  እንድትወጣ ያደረጉት ትራምፕ እንደገና ቢመረጡ ሌሎች የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶችንን ሊገፉ ይችላሉ የሚለውም የአውሮጳውያን ተጨማሪ ስጋት ነው። የአሜሪካን ምርጫ ጀርመንና የአውሮጳ ኅብረት  

እነዚህን የመሳሰሉ ፈተናዎች ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል የሚባሉት የአውሮጳ ሀገራት አስቀድመው ለነዚህ ስጋቶች አልተዘጋጁም የሚሉ ትችቶች ይቀርቡባቸዋል። በፌደራል ጀርመን ምክር ቤት የተቃዋሚዎቹ የወግ አጥባቂዎቹ የክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ዩርገን ሃርድት  ለሁለተኛው የትራምፕ የስልጣን ዘመን ጀርመን በቂ ዝግጅት አድርጋለች ብለው አያስቡም። 
« ባለፉት 3 ዓመታት ጆ ባይደን ከአውሮጳ ጋር የነበራቸው የትብብር ስልት ትራምፕ ከሚያራምዱት የጠብ አዝማሚያ ይልቅ በጣም ውጤታማ እንደሆነ እንዲያረጋግጡ ለመርዳት ብዙ ጥረት አላደረግንም። ከቻይና ጋር ሊኖረን የሚገባውን  ስልታዊ አሰራር ለማዳበር አልሞከርንም። ስለ መከላከያ ወጪ ባደረግናቸው ስምምነቶችም ወደፊት አልገፋንም። በዩክሬን ጦርነት ግፊት ምክንያት ብቻ ግን እንቅስቃሴ አለ።»

በ2019 ዓም ዋትፎርድ ብሪታንያ የተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ የኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች ከትራምፕ ጋር
በ2019 ዓም ዋትፎርድ ብሪታንያ የተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ የኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች ከትራምፕ ጋር ምስል Francisco Seco/AP Photo/picture alliance


ትራምፕ በኔቶ ላይ ያላቸው ጥርጥሬ በአውሮጳ ስጋት እየፈጠረ ነው። በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው የምዕራባውያን የመከላከያ ኅብረት ከሆነው ከኔቶ እንደሚወጡ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲያሳውቁ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 2020 ትራምፕ ለአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዝላ ፎን ዴር ላየን « አውሮጳ ጥቃት ከደረሰበት ልንረዳችሁም ሆነ ልንደግፋችሁ አንመጣም» ብለዋቸው ነበር ። መጪውን ምርጫ ካሸነፉ ለአውሮጳ ሀገራት የኔቶ አባላት ወታደራዊ ድጋፍ ይሰጡ እንደሆነ በጎርጎሮሳዊው ጥር 2024 አጋማሽ የተጠየቁት ትራምፕ እኛን በተገቢው መንገድ የሚይዙን ከሆነ ነው የምንደግፋቸው ማለታቸው ተሰምቷል። ኔቶንና የኔቶ አባል የአውሮጳ ሀገራትን በሚመለከት ለተጠየቁትም «ኔቶ ሀገራችንን ተጠቅሞባታል።የአውሮጳ ሀገራትም ተጠቅመውባታል » ሲሉ ነበር መልስ የሰጡት። የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ተሳትፎ በፍርድ ቤት ሊታይ ነው


ትራምፕ ለኔቶ የሚሰጡትን ድጋፍ የሚቀንሱ ከሆነ ደግሞ ገበያው እንደሚለው ከአንዳንድ የአውሮጳ ሀገራት በኩል ከዚህ ቀደም የመከላከያ ኃይላቸውን ለማጠናከር ይቀርብ የነበረውን ሀሳብ ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ አማራጭ ላይኖራቸው ይችላል ። አውሮጳውያን ትራምፕ ዳግም የዩናትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በሚያሰጉ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው ቀጥሏል። የወቅቱ የአውሮጳ ኅብረት ሊቀመንበር የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ግን የትራምፕ መልሶ መምጣት ሊያሰጋን አይገባም ብለዋል። ለዚህ መዘጋጀት እንደሚገባ ስጋቱም በራሳችን ለመቆም ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ለኅብረቱ ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ስጋቱ የበረታባቸውን ለማረጋጋት ሞክረዋል። 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ