1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት የሚያሻው የቆሻሻ አወጋገድ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2011

ኢትዮጵያ የአካባቢ ተፈጥሮ ደህንነትን የሚያስጠብቁ ደንቦች፤ ሕጎች እና መመሪያዎችን በዝርዝር ያወጣች ሀገር ብትሆንም የደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጉዳይ ዛሬም አነጋጋሪ ነው። በፋብሪካ አካባቢ የሚገኙ ወንዞች በፍሳሾች መበከላቸው፤ በየቦታው ፕላስቲክን ጨምሮ በአካባቢው ተፈጥሮ ላይ ከሚያደርሰው ብክለት በተጓዳኝ የጤና ጠንቅነቱም ይነገራል።

https://p.dw.com/p/3BCPt
Äthiopien Addis Abeba Müll
ምስል DW/Y. Geberegiabeher

ትኩረት የሚያሻው የቆሻሻ አወጋገድ

ከሁለት አስር ዓመታት በፊት ይፋ የሆነ አንድ ጥናት በዋና ከተማ አዲስ አበባ የፍሳሽ እና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስልቱ 200 ሺህ የሚሆን የከተማን ነዋሪ ግምት ውስጥ ያስገባ እንደነበር ያመለክታል። ሆኖም ግን ያኔም ቢሆን አገልግሎቱ ያካለለው 6000 ቤተሰቦችን ብቻ እንደሆነ ነው ጥናቱ የሚያሳየው። ይቀጥልና ሲዘረዝረውም በጎርጎርዮሳዊው 1996/97 ዓ,ም 1,386 ኪዩቢክ ሜትር ቆሻሻ በአንድ ቀን እንደሚሰበሰብ፤ ከዚህ መካከልም 750 ኪዩቢክ ሜትሩ በከተማዋ ማዘጋጃቤት የሚከናወን መሆኑንም ያስረዳል። ይህ ደግሞ የተጠቀሰውን ዓመት ጨምሮ ከዚያ ቀደም ለነበሩ 20 ዓመታት የሚሠራ ነው። እንደ ጥናቱም ደረቅ የቆሻሻ ክምችት አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ ችግር ነው። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቆሻሻን ከየቤቱ የመሰብሰብ ስልት መታየቱ አንድ ነገር ሆኖ የአወጋገዱ መጨረሻ ሂደት ማነጋገሩ አልቀረም። የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገዱም በከተማዋ የሚፈሱ ወንዞችን  ለጥቅም እንዳይውሉ እስከማድረግ መድረሱ በየጊዜው የሚነሳ ችግር ነው። በዋና ከተማዋ ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ እንከን አነሳን እንጂ በፍሳሽ አወጋገድ ሰበብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የውኃ አካላት ለጤና አደገኛ በሆነበት ደረጃ ለብክለት መዳረጋቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ ትኩረት ሰጥተው ዘግበውበታል። በአካባቢው የሚኖሩ ወገኖችም ጉዳታቸውን ሲናገሩ ይደመጣል።

Äthiopien Addis Abeba Müll
ምስል DW/Y. Geberegiabeher

ለዚህ ትኩረት የሰጠ የመወያያ መድረክ ከሳምንታት በፊት በአዳማ ከተማ መካሄዱን የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በፌስቡክ ገፁ ባሰራጫቸው ተከታታይ ዜናዎች አመልክቷል። በምክክር መድረኩ ላይም ምንም እንኳን ሀገሪቱ የአካባቢ ተፈጥሮን ደህንነት እንዲያስጠብቁ የተደነገጉ ሕጎች፤ ደንቦች እና መመሪያዎችን በየጊዜው ብታጸድቅም ተግባራዊ ባለመሆናቸው ምክንያት የአካባቢ ብክለት እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።

ብዙውን ጊዜ በወንዞች አካባቢ የሚገነቡ ፋብሪካዎች እና የተለያዩ አምራች ድርጅቶች ከማምረቻቸው የሚወጣውን ፍሳሽ የሚያስወግዱበት አሠራር አካባቢን ከመበከል አኳያ አነጋጋሪ እና አቤቱታ ሲቀርብበትም ይታያል። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ያካሄደው ውይይት እና ምክክር በዚህ ረገድ መፍትሄ አስገኝቶ ይሆን?

በጉዳዩ ላይ በአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ፤ የአካባቢ እና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቶሎሳ ያደሳ ማብራሪያ ሰጥተውናል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ