1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የመፀዳጃ ቤት እጥረት በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 11 2011

በዓለም ላይ የሚገኙ ደሃ ሃገራት ባላቸዉ የመፀዳጃ ቤት እጥረት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ጤናቸዉና ሕይወታቸዉ ለአደጋ መጋለጡን ተመለከተ። ትናንት ዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ በዋለዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተመድ) የመፀዳጃ ቤት ቀን በኢትዮጵያም የመፀዳጃ ቤት እጥረት ከፍተኛ ነዉ ሲል በተከታታይ ዓመታት ባወጣዉ መግለቻ ገልፆአል።

https://p.dw.com/p/38c6h
Sanitäre Einrichtungen im Slum von Kiberia
ምስል DW/A. Kiti

በኢትዮጵያ 93 % ሕዝብ የመፀዳጃ ቤት ችግር አለበት

ዘንድሮ ይፋ በሆነዉ ጥናት መሰረት በቂ መፀዳጃ ቤት ከሌላቸዉ የዓለም ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ተቀዳሚዉን ስፍራ መያዝዋ ነዉ የተነገረዉ። በኢትዮጵያ የመፀዳጃ ቤት ችግር እጅግ ከፍተኛ ነዉ ሲሉ የጤና ተቋማት የግብረሰናይ ድርጅቶች ሲያሳስቡ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም።  ዶክተር እስጢፋኖስ ምህረት የጠቅላላ ሀኪም ናቸው ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ችግሩ የተባባሰ መሆኑን ያስረግጣሉ። በተለይም ከአንስት አመት በታች በህጻናት ላይ ከንጽህና ጋር በተያያዘ የሚመጡ የጤና መንስኤ እንደሆነ ይገልጻሉ። በእድገታቸው ላይም መስተጓጎል ያስከትላል ይላሉ። 

Sanitäre Einrichtungen im Slum von Kiberia
ምስል DW/A. Kiti

የመፀዳጃ ቤት እጥረት በተለይ በአፍሪቃ እና በእስያ ባሉ ሃገራት ጎልቶ እንደሚታይም ተመልክቶአል። «ዋተር ኤድ»የተሰኘዉ ግብረሰናይ ድርጅት ባወጣዉ ጥናት መሰረት በተለይ በሁለቱ አሕጉሮች በተለይ በርካታ ሕብረተሰብ በአንድ ቦታ ተከማችቶ በሚኖርባቸዉ አካባቢዎች ችግሩ ጎልቶ  እንደሚታይ የወጣዉ ዘገባ ያሳያል።  ጥናቱ በዓለም ዙርያ ከሚገኙ ከአምስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ት/ቤት እንዲሁም ከስምንት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች መካከል አንዱ መፀዳጃ ቤት የሌላቸዉ ናቸዉ። 344 ሚሊዮን ህጻናት ከአፍሪካ በታች ያሉ ህጻናት የመጸዳጃ ቤት ችግር እንዳለባቸው የ«ዋተር ኤድ» ሪፖርት ያመለክታል። የመንግሥታቱ ድርጅት 2015 ዓለም እስከ 2030 የጎርጎረሳዉያን ዓመት የልማት ግቦች ብሎ ካስቀመጠዉ መካከል እያንዳንዱ ሰዉ የተሟላ የመፀዳጃ ቤት ይኖረዋል ይላል።

የተመ የመፀዳጃ ቤት እለት ታስቦ በዋለበት እለት በኢትዮጵያ የሚኖረዉ ሕዝብ 93 % የመፀዳጃ ቤት ችግር አለበት የሚለዉን ጥናታዊ መረጃ ለዓለም መሰራጨቱን የተከታተሉ አንድ የ«DW» ተከታታይ ተከታዩን አስተያየት በዋትስ አፕ ልከዉልናል። 

በኢትዮጵያ የሚታየዉን የመፀዳጃ ቤት እጥረትን ተከትሎ በ«DW» የፊስ ቡክ ድረገጽ የደረሰን አንድ ሁለት አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል፤ ጆን አደም የተባለሉ የ«DW» ፌስቡክ ተከታታይ ባስቀመጡት አስተያየት« ይህ ችግር በጣም እየተበራከተ መቶአል። በከተሞቻችን መንገድ ዳር ብዙ ቆሻሻ የምናየው የሁል ግዜ ተግባር ሁኗል። ይህ ችግር እዲበራከት መንገድ ላይ የተከፍቱት ሆቴሎች አንዳና ምክንያት ናቸዉ። ሆቴሎቹ ካልተጠቀምህ ሽንት ቤት አያስጠቅሙም። ተጠቅመህም ሽንት ቤት ስጠይቅ ቁልፍ ነው ይሉሀል ይህን ችግር ለመቅረፍ ሆቴሎች ሽንት ቤታቸውን ለማንኛውም ክፍት እዲያደርጉ ሕግ ማስገደድ አለበት። እዲሁም መንግስት የህዝብ ሽንት ቤቶችን መስራት አለበት።»

Schild Sitzpinkler
ምስል Imago/teutopress

ነብዪ ግዮናዊ  የተባሉ ሌላዉ የ«DW አድማጭ ባስቀመጡት አስተያየት እውነት እንነጋገር ይህ በተማረው ማህበረሰብ ይብሳል እስኪ ዩኒቨርሲቲዎችን ተመልከቱ ግድግዳ ላይ ሚጠርግ ውጭ ሚፀዳዳ ተማሪ ነው ያለው። በዚህ ትውልድ ምንም ጥሩ ነገር አላየሁበትም።» 

Yonas Samuel የተባሉ በበኩላቸዉ «ይህ ችግር በ27 ዓመት ውስጥ ምንም አይነት ለውጥ አላመጣም ማለት ይቻላል።  መልካም አስተዳደር በሌለበት ሃገር አይደለም መፀዳጃ ቤት ሊለወጥ፤ የህብረተሰቡም የማህበራዊ ህይወት ምንም የተለወጠ ነገር የለም ። ትልቁ ቁም ነገር ማህበረሰብ የገቢው መጠን ከእጅ ወደ አፍ በሆነባት ሃገር ወደ 10 ሚልዮን ርሃብተኛ ባለባት ሃገር ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። እርግጠኛ ነኝ ማንም ሰው አቅም ካለው ንፁህ መጸዳጃ የማያስብ የለም ።ግን አቅሙ ከየት ይምጣ? መንግስትም በዚህ ላይ ትኩረት ሲያደርግ አይታይም።  ምናልባት አሁን ያለው የለውጥ መንግስት እናይ ይሆናል። ህብረተሰቡም ግን ባለው አቅሙ አካባቢውን ቢያፀዳ መልካምነው።» ብለዋል።

Symbolbild - Slum in Afrika
ምስል Getty Images/T. Karumba

 ዶክተር እስጢፋኖስ ምህረት በበኩላቸዉ በመፀዳጃ ላይ በመጠቀም እና በውኃ ላይ በመበከሉ ለከፋ ችግር እንደሚያስከትል ሳይጠቅሱ አላለፉም።ከመጸዳጃ ቤት ጋር ተያይዞ እጅን ካለመታጠብ የአንጀት ኢንፌክሽኖች ያስከትላል። እስከአገር የሚዘልቅ ብዙ ሰዎችን የሚያጠቃ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በኢኮኖሚም በማህበራዊው ተጽእኖ እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል። ንጽህናን ጉድለት ጋር በተያያዝ ወደ ጤና ተቋም የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ቀላል አይደለም ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ በዋለዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «የተመድ» የመፀዳጃ ቤት ቀን በጉዳዩ ላይ ዘመቻዎችን የሚያካሂዱ የሰብዓዊ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መንግሥታትና የንግዱ ኅብረተሰብ ለማኅበረሰብ ፅዳት መጠበቅ ቅድምያ እንዲሰጡ አሳስበዋል። 

ነጃት ኢብራሂም   

አዜብ ታደሰ