1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው ካንሰር በአፍሪቃ

ማክሰኞ፣ የካቲት 19 2011

የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ሲታሰብ ለወትሮው ወባ እና ኤች አይቪ ኤይድስ ነበሩ በርከት ያለውን ሕዝብ ጤና በማወክ አሳሳቢነታቸው የሚወሳው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ብዙም የማይወራለት ካንሰር የብዙዎቹን ሕይወት እየነጠቀ መምጣቱ ስጋት ፈጥሯል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቶቹ ጥቂት አይደሉም።

https://p.dw.com/p/3E8MJ
Melanoma - Hautkrebs - Illustration der Krebszellen
ምስል Imago/Science Photo Library/A. Pasieka

አሳሳቢው ካንሰር በአፍሪቃ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት በአሁኑ ወቅት ካንሰር እየተስፋፋ የመጣ የጤና ችግር መሆኑ እየተነገረ መሆኑን በመጠቆም በዋትስአፕ እና ፌስቡክ የሚከታተሉን አድማጮቻችንን በአካባቢያቸው ስለካንሰር እና ስለካንሰር ታማሚዎች ያስተዋሉትን እንዲያጋሩን ጠይቀን ነበር። አንዳንዶቹ በመገናኛ ብዙሃን ከሚሰሙት በዘለለ የካንሰር ታማሚ በአቅራቢያቸው እንደማያውቁ ቢናገሩም አብዛኞቹ ግን አሳሳቢነቱን በቅርብ ያዩዋቸውን ምሳሌዎች በማስደገፍ ሊገልፁልን ሞክረዋል። በዋትስአፕ ከደረሱን አስተያየቶች አንዱ፤ 

«ይህ በሽታ በጣም አደገኛ እየሆነ መጥቷል እኔ ባለሁበት ቦታ ማንም ለእሱ ትኩረት እየሰጠ አይደለም ነገር ግን በጤና ባለሙያዋችም  ቢሆን ትምህርት ሲሰጥ አላየሁም። እናም አሁን ሳያሰቡት ለሞት እየዳረጋቸው ነው። እንዳየሁት ከታማሚዎቹ ሴት ይበዛል።  አንድ እኔ የታዘብኩት ነገር ልንገራችሁ፤ አንዲት እናት በደህናዋ ሥራ እየሠራች ሳለ አንደ ቀን አመመኝ ብላ ሆስፒታል ተወሰደች፤ እዚያ ግን ምንም ማድረግ አንችልም ብለዋት ወደ አዲሰ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለከፍተኛ ሕክምና ሪፈር  ብለው ሰደዷት፤ እዛ ብትሄድም ታዲያ ቀጠሮ ተሰጥቷት ተመልሳ በጣም አሰቃይቷት ስትሞት አይቻለሁ። ስለዚህ እባካችሁ እንደሌላው በሽታ ለዚህም ትኩረት እንዲሰጠው ብላችሁ ለኅብረተሰቡ ትምህርት ቢሰጥ መልካም ነው፤ እናንም ለሚመለከተው አካል አቅርቡልን።» ይላል። እርግጥ ነው ካንሰር በአሁኑ ጊዜ የብዙዎችን ቤት እያንኳኳ የሚገኝ ብዙም ያልተወራለት በሽታ ሆኗል። በዋትስአፕ አድራሻችን አስተያየታቸውን የላኩልን ሌላኛው ተከታታያችንም «አዎን እውነት ነው፤ ብዙ ወንድሞች እና እህቶቻችን በበሽታው ተጠቅተዋል።» ብለውናል።

ከወራት በፊት ስለ የጡን ካንሰር ማብራሪያ የጠየቅናቸው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከፍተኛ የካንሰር ሃኪም የሆኑት ዶክተር ማቴዎስ አሰፋም በተለይ በዋና ከተማ አዲስ አበባ ለህክምና እና ምርመራ ከሚመጡ አብዛኞቹ የጡት ካንሰር ተጠቂዎች መሆናቸውን ገልፀውልናል።

ቀደም ሲል የበለፀገው እና በኤኮኖሚ ያደገው ዓለም በሽታ ተደርጎ ይታይ የነበረው ካንሰር አሁን ለምን ኤኮኖሚዋ ባልዳበረው አፍሪቃ የመስፋፋት አጋጣሚን አገኘ የብዙዎች ጥያቄ ነው። በዋናነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ታዲያ የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ፤ የሰዎች አመጋገብ መለወጥ፤ እና በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ በህክምና ባለሙያዎች ይነሳሉ። አስተያየታቸውን ካካፈሉን መካከል የህክምና ባለሙያ መሆናቸውን ጠቅሰው ከዚሁ ከጀርመን የአመጋገብ ነገር ዋናው ጉዳይ ነው የሚል አስተያየታቸውን ወደጻፉልን አብድዩ አድማሱ ደወልን፤ በህክምናው ዘርፍ የስነልቡና ባለሙያ እና በዚህ ዘርፍም ትምህርት ላይ መሆናቸውን በመግለፅ ሰዎች ተዘጋጅቶ ጣጣውን የጨረሰ እሽግ ምግብ እየገዙ መመገብ መምረጣቸው አንዱ መዘዝ ነው ያሉበትን ምክንያት አስረድተዋል።

Angola Laden mit Lebensmitteln in Cabinda
ምስል ISSOUF SANOGO/AFP/Getty Images

ሰው የሚመገበውን ይመስላል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ፤ አመጋገብ አንዱ አሳሳቢ የጤና እንከን ሊያስከትል የሚችል መሆኑን የሚጠቁም ነው የእሳቸው ማሳሰቢያ። የታሸጉ ምግቦችን እና ለረዥም ጊዜያት የሚቆዩ የተዘጋጁ ምግቦችን ከየገበያ አዳራሹ እየገዙ መመገብ አሳሳቢ ልማድ እየሆነ መምጣቱንም ነው የጠቆሙት። ሌላው በዚህኛው ዓለም ሰዎች የግድ ህመም ጠንቶባቸው አልጋ እስኪይዙ አይጠበቅም ወደ ሀኪም ሄዶ የጤናን ይዞታ ለማወቅ። አስቀድመው የሚደረጉ የምርመራ እና የህክምና ክትትሎች ህመሙ ስር ሳይሰድ እንዲደረስበት እንደሚረዱ ይታመናል። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ከፍተኛ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ማቴዎስ ኢትዮጵያ ውስጥ የከተማም ሆነ የገጠሩ ነዋሪ ቢሆን በአብዛኛው ህመሙ ከጠናበት በኋላ ወደ ህክምና እንደሚመጣ ነው የሚናገሩት።

ይህ ብቻም አይደለም በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግም ሌላው ካንሰርና መሰል በሽታዎችን እንደሚጋብዝ የህክምና ባለሙያዎች ደጋግመው ይናገራሉ። የመጓጓዣ ስልቶች እንደዛሬው ሳይስፋፉ ሰዎች ለረዥም ሰዓታት በእግር መንቀሳቀሳቸው ጤና እንደነበርም ያስታውሳሉ። እናም የአኗኗር ስልት መለወጥ ብዙዎችን እንዳሳነፈ እና ያ ደግሞ ጤናቸውን ላይ የበኩሉን አሉታዊ ጫና እንዳስከተለም ያሳስባሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እንቅስቃሴ ጤንነትን ለመጠበቅ ያለውን ፋይዳ የሚያስገነዝቡ የሩጫ እና የእግር ጉዞ መርሃግብሮች የመደረጋቸው ዜና ይነገራል። ይህ ሊዘወተር የሚገባ እና፤ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የሚለውን ነባር አባባል የሚያስታውስ ነው። እርስዎስ የራስዎን እና የቤተሰብዎን ጤና ለመጠበቅ ምን ያደርጋሉ? ተሞክሮውን በአድራሻዎቻን ሊያጋሩን ይችላሉ።

በየዓመቱ በመላው ዓለም ከሚከሰተው ከስድስት ሰዎች ሞት አንዱ ሕይወቱ የሚያልፈው በካንሰር ምክንያት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ድርጅቱ እንደሚለውም በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን  ካንሰር ለሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ከሆኑ በሽታዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። እንደ የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በካንሰር ሰበብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 9,6 ሚሊየን ይገመታል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ 70 በመቶ የሚሆኑት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ኗሪዎች ነበሩ።

 ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ