1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የሐዋሳ ሐይቅ ሕልውና

ማክሰኞ፣ ኅዳር 4 2011

የሐዋሳ ሐይቅ በውስጡ በያዘው የብዝሀ ሕይወት ስብጥር ብቻ ሳይሆን ለከተማዋ ውበት በመሆኑም ጭምር ይታወቃል። ሐይቁ ወትሮ የነበረው ይዞታ ከጊዜ ወዲጊዜ እየተበላሸ እና እየተለወጠ መምጣቱ ግን አሁንም የወደፊት ሕልውናው ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ እንዳደረገው በቅርብ የሚከታተሉት ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/38APS
Süd Äthiopien, Hawassa See
ምስል DW/S. Wegayehu

የደን መራቆት ያስከተለው የአፈር ደለል

ቀደምሲል በሀዋሳ ሐይቅ ዙሪያው የሚገኙ ደኖች መመናመናቸውን ተከትሎ ፤ ወደ ሐይቁ የሚገባው ደለል ኑሯቸውን በሐይቁ ላይ ለመሠረቱ ሁሉ ሥጋት መሆኑ አልቀረም። ወጣት ዳዊት አብረሃም በሀዋሳ ሐይቅ ላይ በዓሳ ማስገር ሥራ የተሠማሩ ወጣቶች ያቋቋሙት የሀዋሳ ዓሳ አስጋሪዎች ማሕበር መሥራችና ሊቀመንበር ነው።

ወጣት ዳዊት እንደሚለው በደለልና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ፤ ከሐይቁ የሚገኘው የዓሳ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ የሐይቁን ስነምህዳር ለመጠበቅ ፤ በአንድወቅት ተጀምረው የተቋረጡ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ይጠቁማል፡፡

Lake Hawassa
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የሀዋሳ ሐይቅን ሕልውና ከአደጋ ለመጠበቅ ወደ ውኃው አካል እየገባ የሚገኘውን ደለል ማስቆም ይገባል በሚለው የዓሳ አስጋሪዎች ማሕበር ሀሳብ የሚስማሙት ፤ የአካባቢ ተቆርቋሪው አቶ ተድላ ወ/ሚካኤል ይህ ግን ብቸኛ መፍትሄ አይደለም ይላሉ።

ይልቁንም ከደለል መከላከልና ከደን ልማት ሥራዎች በተጨማሪ ፤ ከተማዋን እንደቀለበት ከከበቧት ፋብሪካዎች የሚወጡ ፈሳሾች በሀይቁ ላይ ያላቸው ተጽኖ መፈተሸ እንደሚኖርበት ይመክራሉ።

Lake Hawassa
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ሰነፍ እረኛ ከቅርብ ትቶ ከሩቅ ይመልሳል እንደሚባለው ፤ የሀዋሳ ሐይቅም አሁን የተጋረጡበት ችግሮች ከወዲሁ ካልተቀረፉ ፤ ነገ አንደ ሀሮማያ ሐይቅ የመድረቅ እና መጥፋት አደጋ  እንዳይገጥመው ስጋታቸውን የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው ፡፡

በዙሪያው ያሉትን የተለያዩ አሳሳቢ መንስኤዎች ቢያስተውሉም የአካባቢ ተቆርቋሪው አቶ ተድላ ግን የሀዋሳ ሐይቅ ዳግማዊ ሀሮማያ ሊሆን አይችልም ይላሉ።  ዛሬ ላይ ሐይቁን ከአደጋ ለመታደግ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተሰሩ መሆናቸውን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። የሐዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ለዕለቱ የጤና እና አካባቢ መሰናዶ ይህን ይቃኛል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው  ያድምጡ።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ