1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አናን ለኢትዮጵያ ፤ ኢትዮጵያ ለአናን

ሰኞ፣ ነሐሴ 14 2010

ኮፊ አናን።በ1962 ዤኔቭ የሚገኘዉ የተባበሩት መንግስታት የጤና ድርጅት የአስተዳደር እና የበጀት ክፍል ባለሙያ ሆነዉ ተቀጠሩ።ብዙም አልቆዩ አዲስ አበባ ወደሚገኘዉ የድርጅቱ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን መስሪያ ቤት ተዘዋሩ።አዲስ አበባ ኖሩ።ኢትዮጵያን አወቁ።ኢትዮጵያዉያንን ወደዱ።

https://p.dw.com/p/33RPt
UN Kofi Annan
ምስል Reuters/D. Sinyakov

አናን ለኢትዮጵያ ፤ ኢትዮጵያ ለአናን

የክዋሚ ንኩሩማሕ አፍሪቃን አንድ የማድረግ ሕልም-ትልማቸዉ ብሪታንያ ሲማሩ አለያም ጋናን ሲመሩ ተፀንሶ ሊሆን ይችላል።የተወለደዉ ግን አዲስ አበባ ላይ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት ነዉ።ኔልሰን ማንዴላ ጥቁር ወገኖቻቸዉን ከነጭ ዘረኞች አገዛዝ ነፃ የማዉጣት፤ ዓላማ ትግላቸዉን ደቡብ አፍሪቃ ላይ መጀመራቸዉ አያከራክርም።የትጥቅ ትግላቸዉ ክሒል፤ ብልሐት እና ሥልት አንድ ሁለት ያለዉ ግን አዲስ አበባ ነበር።ኮፊ አናን ኩማሲ፤ ጋና ተወለዱ፣የዓለም ትልቅ ማሕበርን ትልቅ ስልጣን ኒዮርክ ላይ ሲይዙ በዓለም ታወቁ።ከትንሺቱ ኩማሲ ትልቋ ኒዮርክ ያደረሳቸዉ ረጅም ርቀትን የተጓዙት ኢትዮጵያ ተለማምደዉ በአዲስ አበባ አቋርጠዉ ነበር።ቅዳሜ አረፉ።80 ዓመታቸዉ ነበር።አዲስ አበባ ታስታዉሳቸዉ ይሆን? እኛ እንዘክራቸዉ።

በ1994 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሩዋንዳ ለዘር ዛሯ እብደት ጭዳ ያደረገች ዜጋዋን የአስከሬን ደም እድፍ-ጉድፍ በቅጡ ሳታፀዳ ኪጋሊን ከጎበኙት የሐገራት መሪዎች፤ የያኔዉ የኢትዮጵያ የሽግግር ፕሬዝደንት መለስ ዜናዊ አንዱ ምናልባትም ቀዳሚዉ ነበሩ።

ፕሬዝደንቱን ተከትለን ኪጋሊ የተጓዝን ጋዜጠኞች ከአዉሮፕላን ማረፊያ እስከ እስከ ሆቴላችን የተጓዝንባት የአንድ የርዳታ ድርጅት መኪናንን የሚያሽከረክሩት ሾፌር ኢትዮጵያዊ ነበሩ።ሆቴላችን ስንደርስ የዓለም ቀይ መስቀል ማሕበር ተወካይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ አየን።መግለጫ ሰጪዉ ኃላፊ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ።

ማምሻዉን አንድ አጭር፤ ቀጭን፤ ጠይም፤ ሸበቶ ሰዉዬዉ በብዙ ሰዎች ታጅበዉ የኢትዮጵያዉን ፕሬዝደንት ሊያነጋግሩ ሆቴላችን ደረሱ።ፕሬዝደንቱ ክፍል ሲገቡ «ጤና ይስጥልኝ» አሉ ።ኢትዮጵያዊ አይመስሉም ግን በአማርኛ ሰላምታ ሰጡ።ወዲያዉ አወቅናቸዉ ኮፊ አናን ናቸዉ።የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ዘመቻ ጉዳይ ረዳት ዋና ፀሐፊ።

Kofi Annan UN Generalsekretär in Ruanda
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

እንደ እሳቸዉ ሁሉ ያኔ ያላወቅናቸዉ ወይም ያላየናቸዉ ቢያንስ ሁለት ኢትዮጵያዉያን  ሩዋንዳ እና ለሩዋንዳ ሊሰሩ እዚያዉ ነበሩ።አንዱ ጋዜጠኛ፤ ዲፕሎማት፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሠራተኛ ናቸዉ።አምባሳደር ተፈራ ሻዉል።

ኮፊ አናን።በ1962 ዤኔቭ የሚገኘዉ የተባበሩት መንግስታት የጤና ድርጅት የአስተዳደር እና የበጀት ክፍል ባለሙያ ሆነዉ ተቀጠሩ።ብዙም አልቆዩ አዲስ አበባ ወደሚገኘዉ የድርጅቱ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን መስሪያ ቤት ተዘዋሩ።አዲስ አበባ ኖሩ።ኢትዮጵያን አወቁ።ኢትዮጵያዉያንን ወደዱ።

የያኔዉ የብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ወጣት ጋዘጠኛ ተፈራ ሻዉል ከአናን ጋር የተዋወቀዉም ያኔ ነበር።እርግጥ ነዉ አናን ጋናዊ ናቸዉ።የተማሩት ዩናይትድ ስቴትስ ሥራ የተቀጠሩት ሲዊስዘርላንድ ነዉ።በወጣትነታቸዉ ኢትዮጵያ ከሰሩ በኋላ የተቀየሩት ወደ ኢስማኢሊያ ግብፅ ነዉ።ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዉያን የነበራቸዉ ክብር እና ፍቅር ግን አምባሳደር ተፈራ እንደሚሉት ለየት ያለ ነበር።ልዩ ፀሐፊያቸዉ ኢትዮጵያዊት ነበሩ።ማስታወሺያ ያዢያቸዉ፤ሐኪማቸዉ፤ ፎቶ ግራፍ አንሺያቸዉ ኢትዮጵያዉያን ነበሩ።

  በ1994 ሩዋንዳ እና ሩዋንዳ አካባቢ ለሩዋንዳ ይሰሩ ከነበሩ  ኢትዮጵያዉን ሁለተኛዉ ዶክተር ያቆብ ኃይለማርያም ናቸዉ።ዶክተር ያቆብ ያኔ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩዋንዳን ጭፍጨፋ እንዲመረምር የሰየመዉ ልዩ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አቃቤ ሕግ ነበሩ።የሩዋንዳዉ ጭፍጨፋ የኮፊ አናንን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ሥራ፤እዉቀት ሥም እና ዝና የሚበክል መጥፎ አጋጣሚ ነዉ።ያኔ የተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪ ዘመቻ ጉዳይ ረዳት ዋና ፀሐፊ የነበሩት አናን ሩዋንዳ ሠፍሮ የነበረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራዊት በጨፍጫፊዎቹ ላይ እርምጃ እንዳይወስድ አዘዉ ነበር።

                               

አናንም እራሳቸዉ በኋለኛ ዘመናቸዉ የሩዋንዳዉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ መሆን ያልነበረበት ግን የሆነ፤ መደገም የሌለበት ብለዉታል።«የሩዋንዳዉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ፍፁም መሆን አልነበረበትም።ግን ሆነ።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሩዋንዳን ከጥፋት አላዳነም።ይሕ እዉነት ሁሌም ከመራር ፀፀት እና ጠንካራ ሐዘን ጋር እንድንኖር ያደርገናል።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፈጣን እርምጃ ወስዶ ቢሆን ኖሮ አብዛኛዉን ግድያ ማስቀረት ይችል ነበር።»

Gaza - Palästinensischer Präsident Arafat trifft Un Generalsekrektär Kofi Annan
ምስል Reuters/A. Jadallah

በ1997 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሆነዉ ሲመረጡ በድርጅቱ ዉስጥ ከተራ ባለሙያነት እስከ ረዳት ዋና ፀሐፊነት ለ35 ዓመታት አገልግለዉ ነበር።የዋና ፀሐፊነቱን ሥልጣን ከያዙ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጋዜጠኞች ሲጠይቋቸዉ ግን «ልክ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ስገባ የመጀመሪያዉ ቀን የነበረኝ ዓይነት ስሜት ነዉ ያለኝ» ብለዉ መለሱ።ሁሌም እንደተማሩ ነዉ።

ከሩዋንዳዉ ጭፍጨፋ በመማራቸዉ የይጎዝላቪያዉ እልቂት ከፈጀዉ ሕዝብ በላይ እንዳይጨርስ ጣሩ።የድርጅታቸዉን የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ጡንቻ የሶማሊያ፤የላይቤሪያ፤ የሴራሊዮን እና የሌሎችንም ሐገራት ግጭት ጦርነት ለማስቆም ተጠቀሙበት።የዓለም  ሐብት የድሆችን ኑሮ ለመቀየር፤ ትምሕርት እና ጤናን ለማዳረስ እንዲዉል የዓመአቱ ግብ (ሚሊኒየም ጎል) የተባለዉን ዕቅድ አስነደፉ።

አናን እና ድርጅታቸዉ ለሠላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ በ2001 ታላቁን የሠላም ሽልማት ኖቤል የሸለማቸዉ ድርጅት ተጠሪ ጉነር ቤርገ እንዳሉት አናን በድርጅቱ ታሪክ በጣም ዉጤታማ ዋና ፀሐፊ ናቸዉ።

                      

«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም እና እርቅን ለማስፈን፤ በሰዉ ልጅ ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለመከላከል ሁነኛ መሳሪያ ነዉ።ኮፊ አናን ደግሞ የተዋጣላቸዉየተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ፤ ምናልባትም በድርጅቱ ታሪክ በጣም የተሳካላቸዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ናቸዉ።»

በ2003 የዋሽግተን እና የለንደን መሪዎች ኢራቅን ሲወርሩ ተቃወሙ።ወረራዉን በመቃወማቸዉ ከዋሽግተን ገዢዎች የተቃጣባቸዉ ብቀላ ቀላል ነበረም።አንዱ እሳቸዉን ከነ ልጃቸዉ በሙስና መወንጀል ነበር።ሰዉዬዉ በአሜሪካ መርማሪ፤ በአሜሪካ አጣሪ፤ በአሜሪካ ተከራካሪ የአሜሪካ መሪዎችን ዱላ መከቱ።የዋና ፀሐፊነቱን ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ በመሠረቱት ተቋም አማካይነት የኬንያዎችን ደም አፋሳሽ ዉዝግብ አስወግደዋል።አምባሳደር ተፈራ ሻዉል እንደሚሉት አናን የኬንያዎችን ሲሸመግሉ ቀኝ እጃቸዉ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።

Angola - Nelson Mandela und Kofi Annan
ምስል picture-alliance/AP/S. Kralj

                                     

የሶሪያን ጦርነት በሠላም ለማስወገድ የመጀመሪያዉ ልዩ መልዕክተኛ ሆነዉ ጥረዋል።ጥረታቸዉ አልተሳካም።ያሁኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የሠላም ሻምፒዮን ይሏቸዋል።የ80 ዘመን ሩጫቸዉ አበቃ።ኮፊ አታ አናን።እንደ አናን ሁሉ ንኩሩማሕ፤ ማንዴላ፤ ሙጋቤ፤ ንዮማ ኢትዮጵያ ኖረዉ፤ከኢትዮጵያ ተምረዉ ወይም በኢትዮጵያ ተደግፈዉ ሲያስ ሐገራቸዉን ሲመጠን አፍሪቃን ሲሰፋ ዓለም ዘዉረዋል።ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊ ንኩሩማሕ፤ ማንዴላ፤አናን ትፈጥር ይሆን? መቼ?

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ