1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አንዳርጋቸው ይፈታ» ዘመቻና የእነ እስክንድር አቀባበል

ዓርብ፣ ግንቦት 3 2010

«አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ» የሚል የማኅበራዊ መገናኛ ዘመቻ እና የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም የአቶ በቀለ ገርባ ዩናይትድ ስቴትስ የተደረገላቸው አቀባበል ያስከተለው እሰጥ አገባ የሳምንቱ መነጋገሪያ ርእሰ ጉዳዮች ነበሩ። በሁለቱም ርእሰ-ጉዳዮች ላይ በፌስቡክ እና ትዊተር የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/2xYIg
Symbolbild Twitter
ምስል imago/xim.gs

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሣምንቱ ዐበይት መነጋገሪያ

በሳምንቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶችን ካሳተፉ ርእሰ ጉዳዮች መካከል «አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ» የተሰኘው የትዊተር እና የፌስቡክ ዘመቻ ቀዳሚው ነው። ለሦስት ቀናት በዘለቀው በዚህ ዘመቻ የድረገጽ መለያ ፎቶዋቸውን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የቀየሩም ነበሩ።  አቶ አንዳርጋቸው እንደሌሎቹ ፖለቲከኞች ሁሉ ያለአንዳች ቅድመ ኹናቴ ሊፈቱ ይገባል የሚሉና ያንን የሚቃወሙ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ፖለቲከኛው አቶ በቀለ ገርባ እና ጋዜጠኛው እስክንድር ነጋ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ መግባታቸው እና አቀባበሉ ሌላ የመነጋገሪያ ርእስ አጭሯል።  አቶ በቀለ ገርባ፦ ከአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ውጪ ሌላ ምልክት የሌለበት ባንዲራ የያዙ ሰዎች ባደረጉት አቀባበል ላይ ላለመገኘታቸው የሰጡት ምክንያትም ብርቱ ትችት እና ድጋፍ አግኝቷል። 

«አንዳርጋቸው ይፈታ» የተሰኘው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ የተከናወነው ከሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓም አንስቶ እስከ ረቡዕ ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓም ድረስ ነበር። የዚህ ዘመቻ ተሳታፊዎች ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በጽሑፍ፣ በተንቀሳቃሽ ምስል እና በፎቶግራፍ የተደገፉ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። የዘመቻው ተሳታፊዎች በመልእክታቸው፦ እንደ ሌሎቹ ከእስር የተፈቱ ፖለቲከኞች ሁሉ አቶ አንዳርጋቸውም ይፈቱ ሲሉም ወትውተዋል። የዘመቻው ተቃዋሚዎች በአብዛኛው መልእክታቸው ስድብ እና ዘለፋ የተቀላቀለበት ነበር።

በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች እንንደርደር፦ «ሌቦች አብበው፣ ደምቀውና ተከብረው በሚኖሩባት ሀገር የነፃነት ታጋዮች በእስር ይማቅቃሉ።፡አዎ፤ የነፃነት ታጋዩን ፍቱልን» የሞሱ አሹ አስተያየት ሲኾን፤ ዖመር ሙክታር፥ «ይህ የነፃነት ታጋይ ይፈታ!» ሲል በዘመቻው ጥሪውን አስተላልፏል። «ሥንት ሌባ እየተፈታ ለምንድነው አንዳርጋቸው ፅጌን ማይፈቱት? ይፍቱልን» በሰለሞን ሰለሞን የተሰጠ አስተያየት ነው። መኮንን ቀጀላ፦ «ምንምጥያት አልሠሩም ይፈቱ» ሲል፦ ላዮን አምሀሪክ በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ ደግሞ፦ «ኧረ ይፍቱት ለህፃኗ ሲሉ እንኳን፤ አቦ አይ ወያኔ በገዛ ሀገራች ተበቀለን» ሲል ምሬቱን አንጸባርቋል።  ሕይወት እምሻው፦ «ልባችሁ ያውቃል፣ አሳቢ እንጂ ሃሳብ፣ አብዮተኛ እንጂ አብዮት ታስሮ አያውቅም። ይልቅ ቁጥ ቁጥን ትታችሁ፣ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ፍቱ» ስትል ጽፋለች።

Jemen Sanaa Flughafen
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተላልፈው ተሰጡበት የተባለው የመን ሠንዓ የሚገኘው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያምስል picture-alliance/dpa/Y. Arhab

ሠላም ለሁሉ በሚል የፌስቡክ ስም ደግሞ ቀጣዩ መልእክት ሠፍሯል። «እኔ የምለው ወያኔ ምረት አረጋለው ብሎ በትንሹም መፍታት ጀምሯል። ነገር ግን የይቅርታ ልዩነት አለ እንዴ?» ሲል በማጠየቅ ይንደረደራል። «ከፈታ ሁሉን መፍታት አለበለዝያ ምኑን ይታመን፤ ያላንዳች ሁኔታ አንዳርጋቸውም ሌሎችም ይፈቱ» ሲልም የሠላም መልእክት ይጠናቀቃል። ታዴ ዘፋና ደግሞ በአጭሩ፦ «እንኳን ፈተውት አስረውትም ይፈሩታል» ብሏል።

አቶ «አንዳርጋቸው ጽጌ የኢሕአዴግ መንግሥት ሲበቃው ይፈታቸዋል። እኛ ግን መቼ ነው ከታሰርንበት የዘረኝነት ማእከላዊ የምንወጣው? ማእከላዊ እንኳን ተዘግቧል አሉ፤ እኛስ መቼ ነው የዘረኝነት ፋይላችን የሚዘጋው?» ሲል የጠየቀው ይርጋለም ዳምጠው ነው። 

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈቱ ለሚለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ አጭር ምላሽ የሰጠው ታምራት ገር፦ «አሸባሪ መቼም መፈታት የለበትም» ብሏል።

የዘመቻው ተሳታፊ ከነበሩ የትዊተር ተጠቃሚዎች ከተሰነዘሩ አስተያየቶች የተወሰኑትን እናሰማችሁ። «የኢትዮጵያ አምባገነን መንግሥት አንዳርጋቸው ጽጌን መፍታት አለበት!»  ሲል በጀርመንኛ የጻፈው በኃይሉ ነው።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

«አንዳርጋቸው ጽጌ ታላቅ ጸሐፊ፣ አሰላሳይ እና ቁርጠኛ የዲሞክራሲ ተሟጋች ነው» ሲል በእንግሊዝኛ የጻፈው ደግሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ የቀድሞው አዘጋጅ አዐቢይ ተክለ ማሪያም ነው ። «ነጻ ልቀቁት፣ ቃል የገባችሁትን የፖለቲካ ለውጥ አነቃቁ፤ እናም ኢትዮጵያ ማገገሟን ትጀምር» በማለትም ጠይቋል ዐቢይ።

በኪል-ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አወል አሎ በበኩሉቸው እዛው ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ቀጣዩን ጽፈዋል። «አንዳርጋቸው ጽጌ የፖለቲካ እስረኛ ነው፤ ልክ እንደ በቀለ ገርባ፤ እንደ እስክንድር ነጋ፤ ልክ እንደ አኅመዲን ጀበል» ሲሉም ይንደረደራሉ። «ፍቱት፤ ከቤተሰቡ ጋር እንዲቀላቀል ፍቀዱለት»ም ብለዋል ዶክተር አወል። «አንዳርጋቸው ጽጌ እና ቡድኑ የመረጡትን መንገድ እንዲመርጡ ያስገደዳቸው» ሲሉ የጠቀሱትን ልክ ያልኾነ ነገር እንዲያስተካክሉም ጠይቀዋል። ያ ለብሔራዊ መግባባት አስፈላጊ መኾኑን አክለዋል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ በቀለ ገርባ ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ሲገቡ የተደረገላቸው አቀባበል የሳምንቱ ሌላኛው የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ርእስ ነበር። እስክንድር ዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ከተማ የሚገኘው ዳላስ አየር ማረፊያ ሲደርስ እጅግ ደማቅ የኾነ አቀባበል እንደተደረገለት የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በስፋት ተንሸራሽሯል። በአንጻሩ አቶ በቀለ እዛው ዩናይትድ ስቴትስ ሲገቡ የሚታይበት ቪዲዮ ላይ አቀባበል ያደረጉላቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው።  

Äthiopien Kaliti Gefängnis
ምስል Befekadu Hailu

ይኽ ቅር ያሰኛቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች አቶ በቀለ ገርባ ለምን እንደ እስክንድር ነጋ ደማቅ አቀባበል አልተደረገላቸውም ሲሉ አስተያየቶች ሰንዝረዋል። ከዚያም አቶ በቀለ በኦኤም ኤን ቴሌቪዥን በኦሮሚኛ ባካሄዱት ቃለ-ምልልስ፦ «ለእኔና ለእስክንድር ነጋ ትልቅ አቀባበል ሊያደርጉልን እንደነበረ ቀድመው ነግረውን ነበር» ማለታቸውንም ጋዜጠኛ መልካም ሠላም ሞላ በፌስቡክ ገጿ አቅርባለች።  የቃለ መጠይቁን የአማርኛ ትርጉም ከቪዲዮው ጋር አያይዛለች።

አቶ በቀለ ለምን በአቀባበሉ ላይ እንዳልተገኙ ሲናገሩም፦«መንግስት የማይቀበለውን ባንዲራዎች ይዘው ሊመጡ ይችላሉ። በዛ ላይ የተለያዩ መፈክሮችን ቢያሰሙ እኔ እንደዛ አይነት ቦታ በመገኘቴ ሊያስጠይቀኝ ይችላል ብዬ በመስጋቴ ነው» ብለዋል የሚል የአማርኛ ትርጉም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭቷል። 

የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የአቶ በቀለ ገርባ አቀባበል ላይ የተሰጡ በርካታ አስተያየቶች ወዳልተፈለገ መቧደን እና መዘላለፍ ሲሸጋገሩ ተስተውሏል። ኾኖም ደርዛቸውን የጠበቁ አስተያየቶችም ነበሩ።

መንጋቱ አይቀርም የሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ፦ «OMN ወያኔ አሸባሪ ማለቱን ነውምናውቅ። አረጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዴራ ተይዞ አቀባበል ሲደረግለት አሸባሪ ካስባለው አሸባሪ ከተባለ ሚዲያና ሰዎች ጋር ግንኙነት መፍጠርስ አያስብልም ወይብሏል።  ተመሳሳይ አስተያየት ዋልተር ኋይት በሚል የፌስ ቡክ ስም እንዲህ ይነበባል፦ «OMN በሽብር እንደተከሰሰ አያውቁም?»

Äthiopien Politiker Bekele Gerba
ምስል Addis Standard Magazine

ዘሪሁን ተስፋዬ ፌስቡክ ላይ፦ ስለ አቶ በቀለ ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «ባንዲራን የመጥላት መብቱ ጭምር እንዲከበር አይደል እንዴ ትግሉ?» ሲል ጠይቋል። «ታጋይ ወዳጆች- ጠባብ ብሔርተኛ የተባለ ሁሉ ሥልጣን እንዳይጨብጥ ዴሞክራሲያዊ መንገዶችን ሁሉ መጠቀም ተገቢና የሚደገፍ ቢሆንም የመናገር መብቱን ማፈን ግን ወዴትም አይወስደንም» የሚል አስተያየትም አክሏል።

«ጥፋቱ የበቀለ ገርባ አይደለም» ሲል የሚንደረደረው መስፍን ተክሌ ነው በፌስቡክ።  «ውሽልሽሉ የአንድነት ኃይሉ ነው» ሲልም ይቀጥላል። «በቀለ እንደ መለስ ዜናዊ የምታገለው ለብሄሬ ነው ብሎ በግልፅ አስቀምጧል» ሲልም የአንድነት ኃይሉ የብሔር ፖለቲካ የሚያራምድ ግለሰብ ተመሳሳዩን እንዲያደርግ መጠበቁን ወርፎታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ