1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1 2010

እቅዱን የተቀበሉት ጥቂት ፌደራል ግዛቶች ናቸው። ምሥራቃዊቷ ግዛት ዛክሰን በስርዋ በሚገኘው በድሬዝደን ከተማ መሰል ማዕከል ልታዘጋጅ ከመሆኑ ሌላ ከምዕራቦቹ ከሄሰን እና ከኖርድራይን ቬስት ፋለን ፌደራዊ ግዛቶች በስተቀር በእቅዱ የተማረኩ የሉም።

https://p.dw.com/p/32loy
Deutschland Ankerzentren in Bayern gehen in Betrieb
ምስል picture-alliance/dpa/S. Puchner

የስደተኞች ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል

  
 

በደቡብ ጀርመንዋ በባቫርያ ፌደራዊ ግዛት አወዛጋቢዎቹ፣ የስደተኞች ጊዜያዊ ማቆያ የተባሉ 7ማዕከላት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሥራ ጀምረዋል። የፌደራል መንግሥቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ማዕከላቱ የተገን አሰጣጥ ሂደትን በአንድ ስፍራ ለማከናወን እና ለማፋጠን ይረዳሉ የሚል ተስፋ አላቸው። ተችዎች ግን ይህ ዓይነቱ አሠራር ችግሮችን ያባብሳል እንጂ አያስወግድም ሲሉ ይቃወማሉ። የነዚህ ማዕከላት ዓላማ በአጭሩ የተገን አሰጣጥ ሂደቶችን ማቀላጠፍ እና በአንድ ጣሪያ ስር ማከናወን መሆኑ ተገልጿል። ማዕከላቱ ከቀድሞው በተለየ ስደተኞችን መቀበያ፣ ጉዳያቸውን አይቶ መወሰኛ እና ተቀባይነት ያላገኙትን ማባረሪያ ይሆናሉ ተብሎ ነው የተነገረው። እያንዳንዳቸው እስከ 1500 ስደተኞች እና ፈላስያንን መያዝ በሚችሉት በእነዚህ ማዕከላት ካለፈው ረቡዕ አንስቶ የተገን አሰጣጥ ሂደት የሚመለከተው እያንዳንዱ መስሪያ ቤት እንደሚገኝ የባቫርያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጆአሂም ሄርማን በቅርቡ አስታውቀዋል። ማዕከሉ ባቫርያን የሚያስተዳድረው የወግ አጥባቂው የጀርመን ሶሻል ክርስቲያን ህብረት ፓርቲ ሊቀ መንበር እና የፌደራል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የኽርስት ዜሆፈር  የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ መሪ እቅድ ነው። ጉዳዩ መነሳት የጀመረው በመጋቢት ወር የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ሲዲዩ ከ እህት ፓርቲው ከክርስቲያን ሶሻል ህብረት ሲ ኤስ ዩ እና ከሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር ጥምር መንግሥት ለመመስረት ከተስማሙ በኋላ ነው። ከዚህ በኋላ የሀገሪቱ የተገን አሰጣጥ ስርዓት በተለይም በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞች ጀርመን መግባት የለባቸውም የሚለው የዜሆፈር አቋም ከሜርክል ጋር አወዛግቧቸው ሥልጣን እለቃለሁ እስከማለት ደርሰው የጥምር መንግሥቱ መፍረስም አስግቶ ነበር። ይሁን እና ከቀናት ድርድር በኋላ መግባባት ላይ ተደርሶ ችግሩ ተወግዷል። ከስደተኞች ማቆያ ማዕከላቱ ጀርባ ያለው ሃሳብ ተገን ጠያቂዎች ጀርመን መቆየት መቻል አለመቻላቸው እስኪወሰን ድረስ በዚያ እንዲቆዩ  እና ጉዳያቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን የማባረሩ ሂደት እንዲፋጠን ማድረግ ነው። ይህን አዲስ አሰራር ከ6 ወራት በኋላ የመገምገም እቅድ ተይዟል። ምዘናዎቹ ከተጠናቀቁ በኋላም የጀርመን ፌደራል መንግሥት ሁኔታዎችን የሚያመቻች ህግ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ይህን ለማድረግም በ16 ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች ተቀባይነት ማግኘት አለበት።ይሁን እና እቅዱን የተቀበሉት ጥቂት ፌደራል ግዛቶች ናቸው። ምሥራቃዊቷ ግዛት ዛክሰን በስርዋ በሚገኘው በድሬዝደን ከተማ መሰል ማዕከል ልታዘጋጅ ከመሆኑ ሌላ ከምዕራቦቹ ከሄሰን እና ከኖርድራይን ቬስት ፋለን ፌደራዊ ግዛቶች በስተቀር በእቅዱ የተማረኩ የሉም። አብዛኛዎቹ ጊዚያዊ የማቆያ ማዕክላት እንዳይገነቡ እና የዚህ የፖለቲካ መርህ አካል ላለመሆን ወሰነዋል። ከስደተኞች ማቆያ ማዕከሉ ግቦች አንዱ በተገን ጥያቄ ማመልከቻዎች ላይ የሚሰጡ ውሳኔዎችን ማፋጠን ነው ቢባልም  ቨርነር ሺፋወር የተባሉት የጀርመን የፍልሰተኞች ጉዳይ ምክር ቤት ቦርድ ሊቀ መንበር ይህ ይሆናል ብለው አያምኑም። በርሳቸው አስተያየት ምንም እንኳን የተገን ጥያቄ ጉዳይ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች በሙሉ በነዚህ ማዕከላት ቢገኙም ሁሉም ነገር ይፋጠናል ብለው አያምኑም።
«ጥያቄው ከዚህ ጋር በተያያዘ የተገቡትን ቃሎች ማክበር ይቻላል ወይ ነው? ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው? ግልጽ በሆኑ ጉዳዮች በተለየም በቀጥታ ከጦርነት ቀጠና የሚመጡ ሶሪያዎችን በሚመለከት ፣ሂደቱ በርግጠኝነት ይፋጠናል። ያን ያህል ሊለወጡ የማይችሉት ግልጽ ያልሆኑት ጉዳዮች ናቸው። እኔ እንደምለው ሁሉም የአፍጋኒስታን ስደተኞች ፣ለሁለተኛ ጊዜ የመጡ የአፍጋኒስታን ስደተኞች ጉዳዮችም መፋጠናቸው ያጠራጥራል። ከዚያ ይልቅ እንደ ቀድሞው ጊዜ መውሰዳቸው አይቀርም።»
ሺፋወር በዚህ ረገድ ማንሺንግ እና ባምበርግ በተባሉት የባቫርያ ግዛት ከተሞች ያለውን ተሞክሮ በምሳሌነት በማንሳት ሂደቱን ማፋጠን አለመቻሉን አስረድተዋል። በነዚህ  ከተሞች በሚገኙ ሁለት ማዕከላት በእያንዳንዳቸው ከ1ሺህ በላይ ስደተኞች እንዲገቡ ተደርጓል። የሚኖሩትም በተቀራረቡ ስፍራዎች ያለምንም ስራ ነው። ከተቀረው ዓለምም ተገለዋል። ይህን መሰሉ አያያዝ ለስደተኞች መብት በሚከራከሩ ድርጅቶች ይተቻል። የባቫርያ የስደተኞች ጉዳይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ በማንሺንግ ከተጠለሉት 10 በመቶው ከ18 ወራት በላይ በማዕከሉ እንዲቆዩ መደረጉን አስታውቋል። በቆይታቸውም እንዳይሰሩ መከልከላቸውን፣በእጃቸው ያለ ገንዘብ መወሰዱን እና የጀርመንኛ ቋንቋ እንዳይማሩ መደረጉን በቂ ትምሕርትም እንደማያገኙ ምክር ቤቱ ገልጿል።ዜሆፈር እንዳሉት በአዳዲሶቹ ጊዜያዊ የማቆያ ማዕከላት ስደተኞች ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ እንዲኖሩ አይደረግም። ይህን  የዜሆፈርን  እቅድ የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ይቃወማሉ። በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በአንድ ቦታ ማቆየት አደገኛ ነው ሲሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ይህን የሚቃወሙትም ካለፉ ልምዶች በመነሳት መሆኑንንም ይናገራሉ። ብዙዎች አንድ ላይ በሚኖሩበት ስፍራ በጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር በቀላሉ በሚነሳ አለመግባባት እና ግጭት ፖሊስ ሊያስጠራ የሚችሉ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ስጋታቸው ይገልጻሉ። አዲሱን አሰራር የሚቃወሙት የስደተኞች እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ብቻ አይደሉም። በጀርመን ላዕላይ ምክር ቤት ስደተኞችን ከህብረተሰቡ ጋር የማዋሀድ ክፍልም ጭምር እንጂ። የዚሁ ክፍል ቃል አቀባይ ሬጊና ክራይዲንግ ህግን ተከትለው የሚካሄዱ ተግባራትን እንደሚደግፉ አስታውቀው አዲሱን አሠራር ግን የማይጠቅም ብለውታል።
«የምንቆመው ለህጋዊው ሁኔታ ነው። ሆኖም በመጀመሪያው የፖለቲካ ግመገማችን ብዙ ሰዎችን በአንድ ሰፊ ቦታ ለረዥም ጊዜ ማስቀመጥ ውጤታማ ያልሆነ እና ለውህደትም የማይጠቅም ሆኖ አግኝተነዋል። ይህን ጠቃሚ አድርገን አንቆጥረውም።»
የማዕከላቱ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ዋናው ዓላማቸው ስደተኞች ወደ ጀርመን ዝር እንዳይሉ ማድረግ ነው። የፍልሰት ጉዳዮች ተመራማሪም የሆኑት ሺፋወርም አስተያየት ተመሳሳይ ነው።
«የመሸጋገሪያ ማዕከላቱ ተስፋ ማስቆረጫ መሆናቸው ግልጽ ነው። ለስደተኞቹ  ምልክት መስጫ ነው። እዚህ መምጣታችሁን አንፈልግም የሚል። ይህ ሊሰራ ይችል ይሆናል። ሆኖም ለውህደት ዋጋ እስከማስከፈል ይሄዳል።»
በነዚህ ማዕከላት እንዲኖሩ የሚያስገድዱ ቅድመ ሁኔታዎች የስደተኞቹን ልብ ሊሰብሩ ይችላሉ። ሺፋወር የሚያስጠነቅቁት ሌላ ጉዳይም አለ። በተለይ ማዕከላቱ የሚገኙበት ቦታ የሚያስከትሏቸው መዘዞች። በርሳቸው አስተያየት እነዚህ ማዕከላት በስደተኞቹም ሆነ በአካባቢው ህብረተሰቡ እንደ እስር ቤት ስለሚቆጠሩ የተለያዩ መዘዞችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። 
«አንድ ከተማ የመሸጋገሪያ ማዕከል ካላት ሸክም ነው የሚሆንባት።የአካባቢውን ማህበራዊ ድባብ ይመርዛል።አሉታዊ ስሜትም ይፈጥራል።»  
በአጠቃላይ በሺፋወር እምነት ፖለቲከኞች እነዚህን ማዕከላት በመፍጠር ለመራጩ ህዝብ ፖለቲካዊ ምልክቶችን እየሰጡ ነው። ሆኖም  የተሳሳተ ያሉት ይህ ምልክት እና የፖለቲካ መርህ  ሰዎች ወደ ህገ ወጥ እርምጃ እንዲያዘነብሉ የሚገፋፋ ይሆናል።
«ለብዙሀኑ የህብረተሰብ ክፍል ምልክት መተላለፍ አለበት። እኛ አንድ ነገር እያደረግን ነው። ሁሉንም ነገር በቁጥጥር ስር እናደርጋለን የሚል። ይህ ምልክት አሳሳች ነው። ምክንያቱም ስርዓተ አልበኝነትን ያሰፋፋል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚዘፈቁት ቁጥር ይጨምራል። ከስዊዘርላንድ ያገኘነው ተሞክሮ አለ። እዚያ ከሚገኙ የስደተኞች የመሸጋገሪያ ማዕከላት መጠረዝ የነበረባቸው ጠፍተዋል። ስዊዘርላንድ አለያም ጎረቤት ሀገራት ውስጥ በህገ ወጥ ስደተኝነት ነው ያሉት ። የባየርን የስደተኞች ጉዳይ ምክር ቤት እንዳለው ከባቫሪያዎቹ ከማንሺንግ እና ከባምበርግ ምዕከላት ሊጠረዙ ከነበሩ ስደተኞች 30 በመቶ ያህሉ የመጠረዣ ቀናቸው ሳይደርስ ጠፍተዋል። »
ስደተኞች ከነዚህ ማዕከላት መሸሻቸው የተለያዩ እንደ ሺፋወር ሌሎች ችግሮችንም ሊያስከትል ይችላል።
«በተለይ ወጣት ወንዶች በነዚህ ማዕከላት ከሚታየው ገፊ አቀባበል በመሸሽ  ወደ ከተማ ሊያመልጡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ግጭት ሊያስነሳ ይችላል። ያ ማለት በአካባቢያቸውም ሆነ በቀጥታ በከተማው ውጥረት ሊፈጥር ይችላል።»
በሺፋወር አስተያየት ስርዓት ለማስከበር ቃል ተገብቶ ተጨማሪ ትርምስ እየተፈጠረ ነው። እነዚህን የመሳሰሉ ትችቶች የሚሰነዘሩበት የነዚህ የስደተኞች ጊዜያዊ የማቆያ ማዕከላት ሥራ መቀጠል አለመቀጠል ከ6 ወራት በኋላ በሚካሄድ ግመገማ ውጤት የሚወሰን ይሆናል። በመጪው ጥቅምት ምርጫ የሚጠብቃቸው የባየርን አስተዳዳሪዎች ግን በማዕከላቱ ሥራ መጀመር፣ ለመራጮቻቸው የሚፈልጉትን መልዕክት አስተላልፈዋል። ያሰቡት ይሳካላቸው አይሳካላቸው ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል።

Horst Seehofer Innenministerkonferenz in Quedlinburg
ምስል picture-alliance/dpa/H. Schmidt
Deutschland Asylpolitik Bayerisches Transitzentrum
ምስል picture-alliance/dpa/S. Puchner
Bayerisches Transitzentrum - mögliches Ankerzentrum
ምስል picture-alliance/dpa/S. Puchner
Bayerisches Transitzentrum - mögliches Ankerzentrum
ምስል picture-alliance/dpa/S. Puchner

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ