1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የዚምባብዌ ምርጫ ውጤት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 28 2010

በዚምባቡዌ ባለፈዉ ሰኞ አጠቃላይ ምርጫ ከተደረገ ወዲህ ሀገሪቱ ት ውጥረት ውስጥ ትገኛለች። በዚምባቡዌ ባለፈዉ ሰኞ አጠቃላይ ምርጫ ከተደረገ ወዲህ ሀገሪቱ ት ውጥረት ውስጥ ትገኛለች። የአስመራጩ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ፕሪሲሊያ ቺጉምባ እንዳስታወቁት፣ በፕሬዚደንታዊው ምርጫም ምናንጋግዋ ዋነኛ ተፎካካሪያቸውን ኔልሰን ቻሚሳን አሸንፈዋል።

https://p.dw.com/p/32bSa
Simbabwe Wahlen Nelson Chamisa
ምስል Reuters/P. Bulawayo

ዚምባብዌ

« የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ እጩ  ምናንጋግዋ ኤመርሰን ዳምቡድዞ  ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ ከተሰጠው የመራጭ ድምፅ መካከል ከግማሽ የሚበልጠውን አግኝተዋል፣ ስለዚህ፣ የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲው ምናንጋግዋ ኤመርሰን ዳምቡድዞ ከጎርጎሪዮሳዊው ነሀሴ ሶስት፣ 2018 ዓም ጀምሮ ሕጋዊው የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ሆነው ተመርጠዋል።  »
እንደ አስመራጩ ኮሚሽን፣  ምናንጋግዋ በፕሬዚደንታዊው ምርጫም ቻሚሳን 50,8 ከመቶ በ44,3 ከመቶ በሆነ ድምፅ አሸንፈዋል።
የዚምባብዌ አስመራጭ ኮሚሽ ይፋ ባወጣው ውጤት መሰረት፣  ገዢው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ በምክር ቤታዊው ምርጫ ሁለት ሶስተኛውን መንበር   አግኝቷል፣ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ደግሞ  ባለፈው ህዳር ፣ 2010 ዓም በጦር ኃይሉ ተገፍተው ስልጣን የለቀቁትን የቀድሞ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ የተኩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ዋነኛ ተፎካካሪያቸውን ሰባት ፓርቲዎች የተጠቃለሉበት የተቃዋሚው ህብረት እጩ እና  የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ፣ በምህፃሩ ኤምዲሲ መሪን ኔልሰን ቻሚሳን ማሸነፋቸው ታውቋል። ገዢው ዛኑ ፒኤፍ  144 የምክር ቤት መንበሮችን፣ የተቃዋሚው ህብረት  64 መንበሮችን፣ እንዲሁም፣ የቀድሞው ፕሬዚደንት ታማኞች ያቋቋሙት ብሔራዊ የአርበኞች ግንባር አንድ መንበር አግኝተዋል።
ፕሬዚደንት ምናንጋግዋ ከአከራካሪው ድላቸው በኋላ ትናንት በትዊተር ገጻቸው ለሕዝቡ ባስተላለፉት ጥሪ፣ « ይህ አዲስ ጅማሬ  ነው። እጅ ለእጅ ተያይዘን በሰላም፣ በአንድነት እና በጋራ አዲሲሷን ዚምባብዌ እንገንባ።» ብለዋል። 
ዛኑ ፒኤፍ  በምክር ቤቱ አብላጫውን መንበር ይዟል፣ ምናንጋግዋም አሸንፈዋል  መባሉ የምናንጋግዋ ደጋፊዎችን ቢያስደስትም፣ ውጤቱ በተቃዋሚው ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።  የተቃዋሚው እጩ ቻሚሳ  የፕሬዚደንታዊውን ምርጫ ውጤት ያልተረጋገጠ እና የተሳሳተ በሚል አጣጥለው ፣ በውጤቱ አንጻር ክስ እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል። የተቃዋሚው ህብረት ሊቀ መንበር ሞርገን ኮሚቺ  ፓርቲያቸው ተጭበርብሯል ያለውን የምርጫ ውጤት እንዳያጣራ አስመራጩ ኮሚሽን አከላክሏል በማለት ወቀሳ ሰንዝረው፣ ምርጫው ተዓማኒ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
 « እኛ እንደ ኤምዲሲ ህብረት ውጤቱን ውድቅ አድረገነዋል። ምክንያቱም ውጤቱ በያንዳንዱ እጩ ተወካይ አልተጣራም። »
የ94 ዓመቱ ሙጋቤ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ የተካሄደው የመጀመሪያው አጠቃላይ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ቢጠናቀቅም፣ ድህረ ምርጫ ክስተቶች የዚምባብዌ ህብረተሰብ ምን ያህል መከፋፈሉን እና የጦር ኃይሉ ጠንካራ ቁጥጥርም አለመላላቱን ግልጽ አድርጓል።
ዛኑ ፒ ኤፍ የምክር ቤቱን አብዛኛ መቀመጫዎች መቆጣጠሩ እንደተሰማ  ቁጣውን ለመግለጽ በመዲናይቱ ሀራሬ አደባባይ በወጡት  የተቃዋሚ ደጋፊዎች  ላይ የጦር ኃይሉ በከፈተው ተኩስ  ስድስት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። 
የተቃዋሚው ህብረት ደጋፊዎች ኤመርሰን ምናንጋግዋ  አሸነፉ በመባላቸው ቅር መሰኘታቸውን ነው አንድ ታክሲ አሽከርካሪ የገለጹት።
« ኑሯችን ከባድ ትግል ስለሆነ  ምርጫው ለውጥ ያመጣል ብለን ጠብቀን ነበር። ይሁንና፣ አሁን የወጣውን ውጤት ስመለከት፣ ሁኔታዎች ይበልጡን ይበላሻል። »
« ዚምባብዌ ከፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ጋር ወደፊት አትራመድም። በእውነቱ፣ በዛኑ ፒኤፍ በጣም ተሰላችተናል። »
የጦር ኃይሉ የሰው ሕይወት የጠፋበትን ርምጃ መጠቀሙን በጥብቅ የነቀፈው የአውሮጳ ህብረት ታዛቢ ቡድን ምርጫው ብዙ ችግሮች እንደነበሩበት ገልጸዋል። የመገናኛ ብዙኃን ለገዢው ፓርቲ  መወገኑን፣ መራጮችን ማስፈራራትን፣ እና በአስመራቹ ኮሚሽን ላይ እምነት ማጣትን የመሳሰሉ እንደሚጠቀሱ የቡድኑ መሪ ኤልማር ብሮክ አስታውቀዋል።
« ምርጫው ትክክለኛ አልነበረም ምክንያቱም የፖለቲካው ሜዳ እኩል አልነበረም። ይሁንና፣ ካሁን ቀደም በሀገሪቱ ከተደረጉት ምርጫዎች ጋር ሲነጻጸር መሻሻል ታይቷል። እና የራሳችንን ግምገማ ማድረግ ይኖርብናል። »
ምርጫውን ተከትሎ የታየው የኃይል ርምጃ እንዳሳሰባቸው የገለጹት የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተረሽ  የሚመለከታቸው ሁሉ ከኃይል ተግባር በመቆጠብ ስርዓተ ዴሞክራሲን እንዲያጎለብቱ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የዋና ጸሀፊው ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሀን ሀቅ አስታውቀዋል።
« የፖለቲካ መሪዎች እና በምርጫ የተወዳደሩት ሁሉ ውጤቱን ካልተቀበሉ በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይት እና በህጉ መሰረት መፍትሔ እንዲፈልጉለት በተጨማሪ ጥሪ አቅርበዋል።  ምርጫው በዚምባብዌ  ስርዓተ ዴሞክራሲ ሂደት ላይ አንድ ዋነኛ ርምጃ ነው። ዋና ጸሀፊው በምርጫ ዕለት ሰላማዊው እና ዴሞክራሲያዊ መንፈስ መታየቱን ከብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ሰምተዋል። የዚምባብዌ ሕዝብ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እና ትኩረታቸውንም በሀገሪቱ ልማት ላይ ለማድረግ ያሳዩትን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል። »

Simbabwe Wahlen
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Safodien
Simbabwe Wahlen
ምስል Getty Images/D. Kitwood

በዚምባብዌ ከአከራካሪው የምናንጋግዋ ድል በኋላ ኤምዲሲ ጠንካራ ተቃዋሚ ድምፅ ሆኖ መስራት ከቻለ የዚምባብዌ የወደፊት እጣ ፈንታ ሊሻሻል እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይገምታሉ፣  አዲሱ ፕሬዚደንትየቀድሞውን ፕሬዚደንት ከስልጣን እንዲወርዱ ያስገደዳቸውን የወደቀውን የሀገሪቱ ኤኮኖሚ እንዲሰራራ የማድረግ፣ ከፍተኛውን ዋጋ ግሽበት እና የስራ አጥነት ችግር የመቀነስ፣ እንዲሁም፣ ወረት ወደ ሀገራቸው የመሳብ፣ የተንኮታኮተውን የጤና እና የትምህርቱን ዘርፍ መልሶ የመገንባት  ከባድ ስራ ይጠብቃቸዋል።  

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ