1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ አበባ አስተዳደር ሞተር ሳይክሎችን ሊያግድ ነዉ

ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2011

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር «ለከተማው ሰላም ስጋት ናቸው» ያላቸውን በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ማናቸውንም የሞተር ሳይክሎች ከሰኔ 30 ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ ሊያግድ ነው። የመጫን እና የማውረድ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችም ከንጋት እስከ ምሽት በከተማይቱ እንዳያንቀሳቀሱ እንደሚታገዱ ዛሬ አስተዳደሩ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። 

https://p.dw.com/p/3KhCM
Äthiopien Addis Abeba Motorräder aus Stadt verbannt
ምስል DW/Solomon Musche

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር «ለከተማው ሰላም ስጋት ናቸው» ያላቸውን በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ማናቸውንም የሞተር ሳይክሎች ከሰኔ 30 ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ ሊያግድ ነው። የመጫን እና የማውረድ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችም ከንጋት እስከ ምሽት በከተማይቱ እንዳያንቀሳቀሱ ከተመሳሳይ ጊዜ ጀምሮ እንደሚታገዱ ዛሬ አስተዳደሩ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። 
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማይቱ በተደራጀ መንገድ የቅሚያ፣ የስርቆት እና አልፎ አልፎ ዝርፊያ እየተፈጸመ በመሆኑ እና ለዚህም ሰሌዳቸው አዲስ አበባ ያልሆኑ ሞተር ሳይክሎች ዋነኛ የችግሩ ምንጭ ስለሆኑ ከሰኔ 30 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንዳይንቀሳቀሱ ታግደውል ብለዋል። በመሆኑም የሞተር ሳይክል ባለቤቶች ንብረታቸውን እንዲሰበስቡ እና ከከተማው እንዲያስወጡ አሳስበዋል። 
«ይህ ውሳኔ የተላለፈው ሌላ አማራጭ ጠፍቶ ነው» ተብለው የተጠየቁት ምክትል ከንቲባው «ሞተር ሳይክሎች የትራንስፖርት አማራጭ አይደሉም» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ታከለ በሞተር ሳይክሎች ላይ እገዳ ቢተላለፍም ፖስተኞች፣ ኤምባሲዎችና ሌሎች የግል ተቋማት ግን እንደገና ፍቃድ አውጥተው በጥብቅ ኃላፊነት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አብራርተዋል። የኮድ ቁጥር 2 ሰሌዳ ባላቸው አነስተኛ ተሽከርካሪዎች እና በታክሲዎች በተመሳሳይ እየተፈጸሙ ያሉ ዝርፊያዎችን እና ወንጀሎችን በተመለከተ ደግሞ ያንን ለመከላከል «በሂደት የምንሰራበት ነው» ብለዋል።
በሌላ በኩል የጭነት ተሽከርካሪዎች ከተማዋን እያጨናነቁ በመሆኑ ከሰኔ 30 ጀምሮ ማንኛውም የመጫንና የማውረድ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውን ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል። በቀጣይ ግን የግዙፍ ግንባታዎች እና የመንግስት ተቋማት በልዩነት እንደገና ተመዝግበው እንዲንቀሳቀሱ የሚደረግበት እድል ይኖራል ብለዋል።

Äthiopien Addis Abeba Motorräder aus Stadt verbannt
ምስል DW/Solomon Musche
Äthiopien Addis Abeba Motorräder aus Stadt verbannt
ምስል DW/Solomon Musche

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ተስፋለም ወልደየስ