1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በአሜሪካ የተዘጋጀውን የሥምምነት ረቂቅ ውድቅ አደረገች

ቅዳሜ፣ የካቲት 21 2012

ኢትዮጵያ ለታላቁ የኅዳሴ ግድብ በአሜሪካ የተዘጋጀው የሥምምነት ረቂቅ «የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም» በማለት እንደማትቀበለው አስታወቀች። ግብጽ እና አሜሪካ ሥምምነቱ እንዲፈረም ጥሪ ቢያቀርቡም ኢትዮጵያ ግን ድርድሩ አልተጠናቀቀም ብላለች።

https://p.dw.com/p/3Yefd
BG Grand Renaissance Dam | Der äthiopische Premierminister Abiy Ahmed Ali mit dem ägyptischen Präsident Abdel-Fattah al-Sisi (2018)
ምስል Imago Images/Xinhua

ኢትዮጵያ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ «የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል» አሜሪካ ያወጣችውን መግለጫ ውድቅ አደረገች። የኢትዮጵያ መንግሥት «ሥምምነት ሳይፈረም የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የመጨረሻ ሙከራ እና የውኃ ሙሌት ሊከናወን አይገባም» የሚለው የአሜሪካ ግምዣ ቤት መግለጫ «ከፍተኛ ቅሬታ» እንደፈጠረበት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ «በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ ፈርሞበታል የተባለው “ረቂቅ” የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም» ብሏል።

ኢትዮጵያ ባለፈው የካቲት 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ሊካሔድ ታቅዶ በነበረው ድርድር ባትገኝም ግብፅ በአሜሪካ የተዘጋጀውን ሥምምነት ለፈረም ዝግጁ መሆኗን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና የአሜሪካ ግምዣ ቤት አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በድርድሩ ሳትሳተፍ መቅረቷ "አሳማኝ አይደለም" ያለው የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥምምነቱን ኢትዮጵያ እና ሱዳን በይፋ ተቀብለው በተቻለ ፍጥነት እንዲፈረም በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ጠይቆ ነበር።

BG Grand Renaissance Dam | Verhandlungsrunde (2019)
ምስል AFP/A. Shazly

ኢትዮጵያ ግን «የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም» ብላለች። «ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ እንደሆነ አቋሟን ቀድማ አሳውቃለች» ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ተዘጋጅቷል የተባለውን ሥምምነት ውድቅ አድርጓል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር «የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሰረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሰረት የምታከናውን ይሆናል» ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱ «የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብን ለማዘጋጀት ቀሪ መሰረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ከግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ እና ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር የጀመረችውን ሂደት ለመቀጠል ቁርጠኛ ናት» ብሏል።