1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ ወይስ ሠላም?

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2011

ወጣቱ የኦሮሚያ፤ የአማራ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞችን ከ2008 ጀምሮ በሰልፍ ሲያጥለቀልቅ፤ ሕይወት፤ አካል ደሙን ሲገብር  እንደ ሩቅ ታዛቢ በፀጥታ ሲመለከቱ የነበሩት የትግራይ ከተሞች በለዉጥ ሒደት አሁን የተቃዉሞ ሰልፍ መናኸሪያ መሆናቸዉ በርግጥ ካንዴ ባላይ የሚያሳስብ ነዉ።

https://p.dw.com/p/38wAa
Büro des National Electoral Board of Ethiopia NEBE
ምስል DW

ኢትዮጵያ፣ ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ

 

ከመቀሌ-እስከ ሐረር፤ ከባሕር ዳር እስከ አዋሳ፤ ከሠመራ እስከ አሶሳ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጅጅጋ ያሉ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ እና ያጋሮቹ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲካዊ ለዉጡን እንደሚደግፉ ቃል ያልገቡ፣ ያልተናገሩበት ጊዜ የለም።የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች የሐገር ዉስጥ ይባሉ፣ ከዉጪ የገቡ ለዉጡ የነሱ ትግል ዉጤት እንደሆነ ባደባባይ ይናገራሉ።ከወልቃይት ጠገዴ እስከ ሐረር፣ ከቅማንት እስከ ወለጋ፣ከገዋኒ እስከ ካማሺ ፣ ከቡራዩ እስከ መስቃን-ማረቆ፤ ከጉጂ እስከ ሞያሌ ሕይወት፤አካል፤ ሐብት ንብረት የሚያጠፋዉን ግጭት ለማስቆም ግን ባለስልጣናቱም ሆኑ ተቃዋሚዎቹ አልቻሉም። አልፈለጉም ወይም በተቃራኒዉ የግጭት ጥፋቱ አቀጣጣይ ናቸዉ።የለዉጡ መሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ባዲሱ አጠራር ( ተፎካካሪ) የሚባሉትን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ሥለ ምርጫ  ዝግጅት ለመነጋገር ለነገ ስብሰባ ጠርተዋል።ግጭት ትርምሱ ለየክልል ሹማምት ዐብይ ርዕሥ እንዳልሆነ ሁሉ ዐብይ ለሚመሩት ስብሰባም ርዕሥ አለመሆኑ በርግጥ ግራ ነዉ።

 «ኢትዮጵያ፤ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ» ይላል የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ፅሕፈት ቤት አዲስ መሪ ቃል (ሎጎ)።ለነገ-የተጠራዉ ሥብሰባም ከብዙ ተስፋዎች ባንዱ ላይ ለመነጋገር ያለመ መሆኑን ባዲሱ አጠራር «ተፎካካሪ» ለተባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰራጨዉ ደብዳቤ ያመለክታል።ተስፋዉ፣ምርጫ ነዉ።

«በአገራችን ሥለተጀመረዉ የዲሞክራታይዜሽን ጉዞና----- አገራዊ ምርጫን ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግ ---አስፈላጊ የፊፎርም ሥራዎች ዙሪያ---»እያለ ይቀጥላል በጉራማይሌ ቋንቋ፤ በጎርባጭ ቃላት የተፃፈዉ ደብዳቤ።የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝደንት ዶክተር በዛብሕ ደምሴ መልዕክቱ ደርሷቸዋል።ገብቷቸዋል።በስብሰባ ላይ ይገኛሉም።

ዶክተር በዛብሕ «ነገርን ከስሩ ዉሐን ከጥሩ» ዓይነት ባይ ናቸዉ።ሥለነገዉ ስብሰባ ዓላማና ይዘት ከመነገራቸዉ በፊት፣ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢሕአዴግ መሪዎች አዲስ መሪ ለመምረጥ አዲስ አበባ ላይ ተሰብስበዉ በነበረበት  ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሲያትል-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ሥላሳለፉት ዉሳኔ ይናገራሉ።

 ዶክተር በዛብሕ ነገ በሚደረገዉ ስብሰባ የሚያነሱት ሐሳብም ከጠቅላይ ሚንስትሩ ፅሕፈት ቤት በተሰራጨዉ ደብዳቤ ከተጠቀሰዉ «በምርጫ ዙሪያ» እና «ዲሞክራታይዜሽን» ይልቅ ሥለ ሠላም እና እርቅ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ባለፈዉ ሳምንት ለምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር መንግስታቸዉ «የሠላም እና የእርቅ» ኮሚሽን ለማቋቋም መዘጋጀቱን አስታዉቀዋል።ዶክተር በዛብሕ የሚመሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮሚቴ ያለመዉ የእርቅ ጉባኤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ካስታወቁት ኮሚሽን ጋር መጣጣም-መቃራኑ ላሁኑ ግልፅ አይደለም።ዶክተር በዛብሕ ግን አይቃረንም ባይ ናቸዉ።

Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahmed
ምስል DW/G. Giorgis

 ዶክተር ዐባይ አሕመድ የሚመሩት ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ መስራች የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሪዎችን ሰሞኑን ብዙ ያስጨነቀዉ እርቀ-ሠላም ማዉረድ፤ ለምርጫ መዘጋጀት፤ ወይም በጠቅላይ ሚንስትሩ ፅሕፈት ቋንቋ «የዲሞክራታይዜሽን ጉዞ» እና «የሪፎርም ሥራዎች» አይደለም።የሕወሓት ሊቀመንበር እና የትግራይ ርዕሠ-መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል  ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት የትግራይን ሕዝብ የሚያሳስበዉ «የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብአዊ መብት ረገጣ እና በሙስና በሚጠረጠሩ የቀድሞ ባለሥልጣናት ላይ የሚወስደዉ እርምጃ ነዉ።

የመሪዉን መልዕክት ላንድ ሳምንት ያሕል ሲያስተነትን የሰነበተዉ የትግራይ ሕዝብም ትናንት «ተጠርጣሪዎች በሌላ አካል መዳኘት የለባቸዉም፤ የትግራይ ሕዝብን ለማንበርከክ የሚደረግ እንቅስቃሴን አንቀበልም» የሚሉ መፈክሮችን በየአደባባዩ ሲያቀነቅን ዉሏል።

ለዉጥ የሚጠይቀዉ ህዝብ በጣሙን ወጣቱ የኦሮሚያ፤ የአማራ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞችን ከ2008 ጀምሮ በሰልፍ ሲያጥለቀልቅ፤ ሕይወት፤ አካል ደሙን ሲገብር  እንደ ሩቅ ታዛቢ በፀጥታ ሲመለከቱ የነበሩት የትግራይ ከተሞች በለዉጥ ሒደት አሁን የተቃዉሞ ሰልፍ መናኸሪያ መሆናቸዉ በርግጥ ካንዴ ባላይ የሚያሳስብ ነዉ።

የተቃዉሞ ሰልፉ የሕወሓት መሪዎች ግፊት የለበትም ብሎ ማሰብ በርግጥ የዋሕነት ነዉ።የፖለቲካ ታዛቢዎች በተደጋጋሚ እንዳሉት የሕወሓት መሪዎች አዲስ የተጀመረዉን ለዉጥ ለማደናቀፍ «እያደቡ» ነዉ።የተቃዋሚዉ የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብረሐ ደስታ እንደሚገምቱት ግን ለዉጡን የማይደግፉት የሕወሓት መሪዎች ብቻ አይደሉም፣ የአዴፓ (ብአዴን) መሪዎች ጭምር-እንጂ

የፖለቲካ ተንታኞቹ አስተያየትም ሆነ የአቶ አብረሐ ግምት፤ እዉነትም ሆነ ሐሰት ጠቅላይ ሚንስትር ዐባይ ተቃዋሚዎችን ሥለ ምርጫ ለማነጋገር የጠሩት ለዉጡን እንደግፋለን የሚሉት የኢሕአዴግ መሪዎች በሚሻኮቱበት መሐል መሆኑ ሐቅ ነዉ።ለስብሰባዉ ከተጋበዙት የተቃዋሚ ፓርቲዎ መሪዎች ሰወስቱን አነጋግረናል።ሰወስቱም ከምርጫ በፊት ሰላም እና መረጋጋት መስፈን አለበት ባይ ናቸዉ።ሠላም እና መረጋጋት በማስፈኑ ስልት ግን ይለያያሉ።

Karte Äthiopien englisch

የአረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አብረሐም ደስታ ሠላም እና መረጋጋት ለማስፋን ሁለት ስልቶችን ይጠቁማሉ።አረናን ጨምሮ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያሰባሰበዉ ኢትዮጵያ ፌደራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ ባጭሩ) ምክትል ሊቀመንበር እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙላቱ ገመቹም ፓርቲያቸዉ የፀጥታ ችግሩን፣ የችግሮች ሁሉ ችግር አድርጎ ያየዋል።ፀጥታ እስኪሰፍን ምርጫዉ ይዘግይ የሚለዉን ሐሳብ ግን አቶ ሙላቱ ችግሩን የበለጠ ማራዘም ነዉ ባይ ናቸዉ።

የመኢአድ ሊቀመንበር ዶክተር በዛብሕ ደምሴ ግን ሠላም እና መረጋጋት ሳይሰፍን ምርጫ መጠራቱን አይቀበሉትም።በ2012ት ምርጫ ለማድረግም ያለዉ የመዘጋጃ ጊዜ በቂ አይደለም ባይ ናቸዉ።የአረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አብረሐ ደስታም እንደ ዶክተር በዛብሕ ሁሉ ምርጫ ለማድረግ ሠላም ከማስፈን ቀጥሎ ተቋማት መለወጥ እና መጠናከር አለባቸዉ ባይ ናቸዉ።

የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙላቱ ገመቹ እንደሚሉት ደግሞ ፓርቲያቸዉ ከዚሕ ቀደም ያቀረበዉ ጥያቄ ገቢር እንዲሆን ይፈልጋል።ብሔራዊ የአንድነት መንግስት።የብሔራዊ የአንድነት መንግስት መቋቋም በተለያዩ አካባቢዎች ያለዉን ግጭት እና አለመረጋጋት ለማስወገድም ጠቃሚ ነዉ፣ እንደ አቶ ሙላቱ።

አቶ ሙላቱ አክለዉ እንዳሉት መድረክ እንደ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚመሩትን የለዉጥ ሒደት ይደግፋል።ይሁንና መንግሥት የብሔራዊ የአንድነት መንግስት ምሥረታ ጥያቄን ባለመቀበሉ እና «አንዳድ» ባሏቸዉ  እርምጃዎቹ መድረክ ቅሬታ ያለዉ መሆኑን አቶ ሙላቱ አልሸሸጉም።

 የነገዉ ስብሰባ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፅሕፈት ቤት እንዳለዉ ሥለምርጫ እና የዴሞክራሲ ሒደት ተነጋግሮ፣ ተስማማም አልተስማማ ኢትዮጵያ ዛሬም ከተስፋ አድማስነት ይልቅ የዉዝግብ፤ ግጭት፤ አለመረጋጋት ሐገር መሆንዋን የፖለቲከኞችዋ ብሒል-እርምጃ መስካሪ ነዉ።የሐገሪቱ ተስፋ ከዜጎችዋ ሠላም እና ደሕንነት ዉጪ ሊታሰብ አይችልም።ሠላም እና ደሕንነት ለማስጠበቅ ደግሞ ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ የገዢ ይሁኑ-የተቃዋሚ፤ የአጋር ይባሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ፖለቲከኞችዋ የጋራ ጥረት ማስፈለጉን ለማወቅ ተንታኝ አያሻም።

Addis Abeba
ምስል Haile

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ