1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ እፎይታዋን ለማዳን የአይኤምኤፍ ባለሙያዎችን የጉብኝት ውጤት ትጠብቃለች

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መጋቢት 18 2016

የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ሥምምነት የሚጠባበቀው የዕዳ ክፍያ እፎይታ “ዋጋ ቢስ” የመሆን ሥጋት ተጋርጦበታል። እፎይታው ለመንግሥት 1.5 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የሚያድን ነው። የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች የአዲስ አበባ ጉብኝት ኢትዮጵያ ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ በጠየቀችው 3.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

https://p.dw.com/p/4eC7A
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የዶላር ብድር በመድሐኒት መልክ እንደሚሰጥ የሚያሳይ ምስል
ኢትዮጵያ ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ውይይት ላይ እንደምትገኝ ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ጠቅሶ ዘግቧል። ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

ኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ እፎይታዋን ለማዳን የአይኤምኤፍ ባለሙያዎችን የጉብኝት ውጤት ትጠብቃለች

ኢትዮጵያ ከኦፊሴያል አበዳሪዎቿ ባለፈው ሕዳር ያገኘችው የብድር ክፍያ እፎይታ ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ “ዋጋ ቢስ” የመሆን ሥጋት ተጋርጦበታል። ይኸ “ጊዜያዊ የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሥምምነት” ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለዕዳ ትከፍል የነበረውን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ያስቀረ ነው። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የዕዳ ክፍያ እፎይታውን ለመታደግ እስከ መጋቢት 22 ቀን፣ 2016 ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በባለሙያዎች ደረጃ ከሥምምነት ላይ መድረስ ይኖርበታል። አለበለዚያ የኢትዮጵያ ይፋዊ አበዳሪዎች ሥምምነቱን “ዋጋ ቢስ” ብሎ የማወጅ መብት እንዳላቸው ፓሪስ ክለብ የተባለው ኢ-መደበኛ የአበዳሪዎች ቡድን ባለፈው ሕዳር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ዕዳዋን ትክፈል የተባለ እንደሆነ “የመንግሥት በጀትም ላይ፤ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችትም ላይ ከፍተኛ ጫና ይኖረዋል” ሲሉ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አነስተኛ መሆኑን ያስታወሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “መንግሥት ዕዳ ከከበደው ወደ ለመደው የገንዘብ ሕትመት ተመልሶ እንዳይገባ ያሰጋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የዕዳ ክፍያ እፎይታ የሰጠው የአበዳሪዎች ኮሚቴ የተቋቋመው በመስከረም 2014 ነው። ለኢትዮጵያ ገንዘብ ያበደሩ ሀገራትን በአባልነት ያቀፈውን ኮሚቴ ፈረንሳይ እና ቻይና በተባባሪ ሊቀ-መንበርነት ይመሩታል። ኮሚቴው የተቋቋመው የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል በአበዳሪዎች የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ እንዲደረግ በሐምሌ 2013 ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው።

የቡድን 20 ሀገራት እና የፓሪስ ክለብ ድጋፋቸውን በሰጡት ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ እንዲደረግ በቅድሚያ ካመለከቱ ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ብትሆንም ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ሒደት የታቀደውን እስካሁን አላሳካም። ከኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የዕዳ ክፍያ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደጋግመው የሚያማርሩበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት በዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሲከፍል መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ምስል Office of the Prime Minister Ethiopia/UPI Photo/Newscom/picture alliance

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሣምንት “ታማኝ” ለተባሉ ግብር ከፋዮች በሰጡት ማብራሪያ “ላለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ በአማካኝ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንከፍል ነበር” ሲሉ ጫናውን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ-ቴሌኮም የሚከፍሉትን ሳይጨምር መንግሥታቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ገደማ 9.9 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንደከፈለ ዐቢይ ተናግረዋል።  

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የተጀመረው ድርድር እስኪጠናቀቅ አበዳሪዎች የሰጡት እፎይታ የኢትዮጵያ መንግሥት ከታኅሣሥ 2015 እስከ ታኅሣሥ 22 ቀን፣ 2017 ባሉት ሁለት ዓመታት መክፈል የሚጠበቅበትን ዕዳ የተመለከተ ነው። በፓሪስ ክለብ መግለጫ መሠረት በሥምምነቱ የታገደውን ዕዳ የእፎይታ ጊዜው ካበቃ በኋላ ኢትዮጵያ ከጎርጎሮሳዊው 2027 እስከ 2029 ባሉት ዓመታት እንድትከፍል ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሚቀጥሉት አራት ቀናት ማለትም እስከ መጋቢት 22 ቀን፣ 2016 ድረስ በባለሙያዎች ደረጃ ከሥምምነት ካልደረሱ ግን የዕዳ እፎይታው “ዋጋ ቢስ” ሊባል ይችላል። በእርግጥ ተመሳሳይ የዕዳ ክፍያ እፎይታ በተናጠል ለኢትዮጵያ በሰጠችው በቻይና እና በፈረንሳይ ተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የሚመራው የአበዳሪዎች ኮሚቴ “ተገቢ ሆኖ ካገኘው” ቀነ-ገደቡን ሊያራዝም ይችላል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ባለፈው ሣምንት ወደ አዲስ አበባ እንዳቀኑ ተቋሙ እና የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሬውተርስ አረጋግጠዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሰዎች ለብሎምበርግ እንደተናገሩት ባለሙያዎቹ አዲስ አበባ የደረሱት መጋቢት 10 ቀን፣ 2016 ነው።

ለአንድ ሣምንት የሚዘልቀው የባለሙያዎች ጉብኝት ለዕዳ ክፍያ እፎይታው እጣ-ፈንታ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በጠየው ዕገዛ ጉዳይ ላይ ኹነኛ ተጽዕኖ የሚኖረው ነው።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት
በገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ 28 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ዕዳ አለባት። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት ለመርሐ-ግብሩ ማስፈጸሚያ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ለመደበር ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ሬውተርስ ዘግቧል። የገንዘብ መጠኑ መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ተቋም ለመጀመሪያው የሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ለማበደር ቃል ከገባው 2.9 ቢሊዮን ዶላር በመጠኑ ላቅ ያለ ቢሆንም ከሀገሪቱ ፍላጎት አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እስካሁን ኢትዮጵያ ምን ያክል ለመበደር እንደጠየቀች አላረጋገጡም። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ ጁሊ ኮዛክ ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የምግብ ዋስትና እጦት፣ የሰብአዊ ርዳታ፣ ከግጭት በኋላ ለታቀደ መልሶ ግንባታ እና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ብርቱ ፈተናዎች እንድትቋቋም ለመርዳት የፋይናንስ ዕገዛ ጥያቄ ቀርቦልናል” ሲሉ ተናግረዋል።  

የዐቢይ መንግሥት ከዓለም አቀፉየገንዘብ ድርጅት የጠየቀው ዕገዛ “የኢትዮጵያን ከፍተኛ የኤኮኖሚ አቅም ለማሳካት ያቀደውን የሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ ጭምር ያለመ” እንደሆነ ጁሊ ኮዛክ ገልጸዋል።

ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ስድስት ወራት ያስቆጠረው ሁለተኛው ምዕራፍ የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ማክሮ ኤኮኖሚውን ማረጋጋት እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ላይ ያነጣጠረ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ሠነዱን ለሕዝብ ይፋ ባያደርግም የኢንቨስትመንት እና የንግድ ከባቢን ማሻሻል፣ በማምረቻ እና በሲቪል ሰርቪስ ዘርፎች  ማሻሻያዎች ተግባራዊ የማድረግ ዕቅዶች እንደተካተቱበት ዶይቼ ቬለ መገንዘብ ችሏል። የችርቻሮ እና የጅምላ ንግድ ዘርፉ በሒደት ለውድድር ክፍት የሚሆነው ለሦስት ዓመታት በሚዘልቀው በዚሁ መርሐ-ግብር ነው።

ሠነዱን የተመለከቱ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅድ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የድጋፍ መርሐ ግብር ጋር ሊስማማ የሚችል እንደሆነ ያምናሉ። የዕቅዱን ተግባራዊነትም ሆነ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ጋር የሚደረገውን ድርድር የሚያወሳስበው ግን የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን የማድረግ ጉዳይ ነው።

ሽንኩርት እና ድንች ለሽያጭ በቀረበበት የአዲስ አበባ መደብር ብር ይታያል
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግፊት ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ቢዳከም በገበያው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎች ሥጋት አላቸው። ምስል Eshete Bekele/DW

“በብዙዎቹ ጉዳዮች የሚስማሙ ይመስለኛል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “የውጭ ምንዛሪን ማስተካከል የሚለው ጉዳይ” ትልቅ ፈተና እንደሆነ አላጡትም። “በጥቁር ገበያ እና በኦፊሴያል ተመን መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ገበያው እንዲመጣ እና ሰፊ ማስተካከያ እንዲያካሒድ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በጣም ጫና እያሳደረበት ነው” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “የኢትዮጵያ መንግሥት ይኸን ማድረግ ከባድ ፈተና ሆኖበታል። በኤኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና ከባድ ስለሆነ ይኸንን ለማድረግ በጣም አመንትቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

በመንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክን የመሣሰሉ ተቋማት እንደሚገፋፉት በገበያው ፍላጎት እንዲከወን የሚሹ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ቢኖሩም በርካቶች ዳፋው ያሰጋቸዋል። በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋት በሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ቢሆንም እንደታቀደው አልተሳካም።

ባለፉት ዓመታት ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በሽርፍራፊ ሣንቲሞች እየተዳከመ ቢሔድም በተለምዶ ጥቁር እየተባለ ከሚጠራው የጎንዮሽ ግብይት ጋር ያለው ልዩነት መጥበብ አልቻለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቀጥታ ይኸን ጉዳይ ባያነሱም ባለፈው የካቲት መንግሥታቸው ተግባራዊ የሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር “ቆንጠጥ የሚያደርግ” ሆኖ ሊስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የምትሻውን ድጋፍ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በሀገሪቱ የበረታው ግጭት ጥላ ጭምር አርፎበታል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ ጁሊ ኮዛክ “በቅርቡ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የታዩ ግጭቶች አስጨናቂ እና አሳሳቢ ናቸው። እነዚህን ግጭቶች በቅርብ እየተከታተልን እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሎጎ
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ከመጋቢት 10 ቀን፣ 2016 ጀምሮ ለአንድ ሣምንት አዲስ አበባ ሰንብተዋል። ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍ ያለ ድምፅ ያላት እና በአማራ እና በኦሮሚያ የሚታዩ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ ለአፍሪካ ቀንድ በመደበቻቸው ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር በኩል ግፊት የምታደርገው አሜሪካ ሥጋቷን በተደጋጋሚ ገልጻለች። የአሜሪካ ሥጋት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ላይ ተጽዕኖ ያሳድር እንደሆነ የተጠየቁት የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጁሊ ኮዛክ “አሜሪካ የተሰማትን ሥጋት ልብ ብለናል። ችግሮቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ተስፋ እና ደርጋለን” የሚል ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ ያጸደቀው 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት እጅ ሳይገባ የተቋረጠው በመስከረም 2014 ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተባለው ማዕቀፍ እንዲቀጥል ወዲያው ቢጠይቅም እስካሁን ድረስ አልተሳካም። ሦስት ክልሎች ያዳረሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥያቄው በአፋጣኝ ምላሽ እንዳያገኝ ዕክል እንደፈጠረ ይታመናል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጦርነቱን በይፋ በምክንያትነት እንዳላቀረበ የሚያስታውሱት ዶክተር አብዱልመናን “ግጭቱ እስካልተፈታ ድረስ” በሚል ሳይጓተት እንዳልቀረ ያምናሉ። ጉዳዩ “ከኤኮኖሚ የበለጠ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ ነው ሲጓተት የነበረው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “አሁንም እንደ አንድ ጉዳይ አቅርበውት ሊያራዝሙት ይችላሉ” ሲሉ ሥጋታቸውን አጋርተዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ባለፈው መስከረም ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት ወቅት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በጠየቁት ድጋፍ ላይ ያደረጉት ውይይት “በጎ እመርታ” ማሳየቱን ልዑካን ቡድኑን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ ገልጸው ነበር።

ከረዥም ጊዜ መጓተት በኋላ ባለፈው ሣምንት አዲስ አበባ የደረሱት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ከምን ውጤት ላይ እንደደረሱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከገንዘብ ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ