1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ተሸለሙ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 2009

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ ማርያም በጀርመን ሀገር ልዩ ክብር በሚሰጠው በአሌክሳንደር ሁምቦልት ተቋም ተሸላሚ ሆኑ። ፕሮፌሰሩ ለሽልማት የበቁት በሕይወት ዘመን ላበረከቱት አስተዋጽዖ ነው። ከአራት ወራት በኋላ ሽልማታቸውን ጀርመን ከሚገኘው ተቋም እንደሚወስዱም ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/2RjUT
Martin-Luther-Universität Halle-Wittenberg
ምስል Universität Halle-Wittenberg

የኢትዮጵያዊዉ ሳይቲስት መሸለም

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ቴክኖሎጂ ዘርፍ መምህር እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ ማርያም ለሽልማት የበቁት በሕይወት ዘመን ላከናወኑት ሳይንሳዊ ምርምር እና በዘርፉ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ ነው። ፕሮፌሰሩን ለሽልማት ያበቃቸው እጅግ ዝነኛ የሆነው የጀርመኑ አሌክሳንደር ሁምቦልድት ተቋም፤ በጀርመን እና በመላው ዓለም ከሚገኙ ምጡቃን ተመራማሪዎች እንዲሁም ምሁራን ጋር በመተባበር ይታወቃል። ፕሮፌሰር ጽጌ በመድኃኒት ቅመማ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከ200 በላይ የምርምር ጽሑፎችን ለኅትመት ያበቁ ብርቱ ሳይንቲስት መሆናቸውን ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ራይንሃርድት ኖይበርት ይመሰክራሉ። 

አሌክሳንደር ሁምቦልት በጀርመን ሀገር የጥናት እና ምርምር ዘርፍ ስማቸው በክብር ከፍ ብሎ ከሚነሱ ከፍተኛ የምርምር ተቋማት መካከል ቀዳሚው ነው። ይኽ የምርምር ተቋም  ኢትዮጵያዊውን ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም ለታላቅ ክብር አብቅቷል። ፕሮፌሰር ጽጌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ቴክኖሎጂ ተመራማሪ ናቸው። ተሸላሚ የኾኑትም በሕይወት ዘመን ሥራ እና ምርምር ላበረከቱት አስተዋጽዖ መኾኑን ለሽልማቱ ያጩዋቸው ፕሮፌሰር  ራይንሃርድት  ኖይበርት ተናግረዋል። 

«ለጊኦርግ ፎርስተር የምርምር ሽልማት ተቋም በዕጩነት የጠቆምኩት እኔ ነኝ። ሽልማቱ በአሌክሳንደር ሁምቦልት ማኅበረሰብ የሚዘጋጅ ነው።»

የጊኦርግ ፎስተር የምርምር ሽልማት የሚሰጠው በሁሉም የትምህርት ዘርፍ ስኬት ላስመዘገቡ እና የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ተመራማሪዎች ነው። ተመራማሪዎቹ ለሽልማት ለመብቃት በማደግ አለያም በሽግግር ላይ በሚገኙ ሃገራት አዲስ ኃልዮት ወይንም መሠረታዊ ግኝት ላይ መድረስ መቻል አለባቸው። 

Screenshot Uni Halle
ምስል www.uni-halle.de

ፕሮፌሰር ጽጌ በሳይንሳዊ አጠራራቸው (Glinus lotoides)ማለትም  መተሬ የሚባሉትን እና (Plumbago zeylanica) የተሰኙ  ባለ አበባ ቅጠላ ቅጠሎችን እንዲሁም እጽዋት ለመድኃኒትነት አገልግሎት እንዲውሉ በማስቻል ዓለም አቀፍ ዕውቅና በስማቸው አስመዝግበዋል። መተሬ ቅጠል ከትንሿ አንጀት እንደ ኮሦ ያሉ ሕዋሳትን  ያስወግዳል። ይኽን ቅጠል ፕሮፌሰሩ በእንክብል መልክ መድሃኒት እንዲሆን አዘጋጅተዋል። ሌላኛው ፕሉምባጎ ዛይሌኒካ የሚባለው እጽ  ደግሞ ችፌ የሚባለውን ቆዳ ላይ ሽፍ ብሎ የሚያሳክክ ስር የሰደደ ቁስልን ለማከም ይውላል። ፕሮፌሰር ጽጌ መድኃኒቶቹን የሠሩት ከባሕላዊ ሐኪሞች ጋር በመመካከር ነው። በመድኃኒት ቅመማ ዘርፍ ፕሮፌሰር ጽጌ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሣይንሳዊ፣ ጥልቅ፣ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸው ለኅትመት በቅቶላቸዋል። 
 

«በመድኃኒት ቅመማ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከ200 በላይ የምርምር ጽሑፎችን ለኅትመት አብቅቷል። ለአብነት ያህል ሀገር በቀል የሆኑ ተክሎችን ለመድኃኒት ቅመማ ቴክኖሎጂ ጥቅም እንዲውሉ ለማስቻል ከፍተኛ ምርምር አከናውኗል። ለምሳሌ በካሳቫ ተክል ላይ ያደረገውን ምርምር መጥቀስ ይቻላል። ለዶክትሬት መመረቂያው ያከናወነው ጥናት በፋርማሲ ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ነው።»

ፕሮፌሰር ጽጌ በተለይ በእንሰት ተክል እና ካሳቫ በሚባለው ስኳር ድንች መሳይ ተክል ላይ ያደረጉት ጥናትም ልዩ እና ጥልቅ መኾኑን ፕሮፌሰር ራይንሃርድት ኖይበርት ተናግረዋል። በተለይ የእንሰት ተክል በደቡባዊ ኢትዮጵያ ለ10 ሚሊዮን ግድም ነዋሪዎች በዋነኛ ምግብነት እንደሚያገለግል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ጋር ለኅትመት ባበቁት መጽሐፋቸው ተገልጧል። መጽሐፉ ከዕለት ተዕለት የምግብ አቅርቦቶች መድሃኒቶችን ለመቀመም ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ነገሮች በዋናነት ይተነትናል።  

እንደ ፕሮፌሰር ራይንሃርድት ማብራሪያ አንድ አፍሪቃዊ በአሌክሳንደር ሁምቦልድት ተቋም ተሸላሚ ለማድረግ እጅግ ከባድ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ተቋም ተሸላሚዎች በምዕራቡ ዓለም ምርምር እና ጥናታቸውን የሚያከናውኑ ተመራማሪዎች ናቸው። 

«ከአፍሪቃ አንድን ሰው በአሌክሳንደር ሁምቦልት ማኅበረሰብ የምርምር ተሸላሚ ይኹን ብሎ በዕጩነት ማቅረብ እንዲህ እንደዋዛ የሚታይ ነገር አይደለም። ከፍራንክፉርት ወይንም ደግሞ ከታላቋ ብሪታንያ ለዕጩነት የሚቀርብ ሰው ከአፍሪቃ ከሚቀርበው ጋር ሲነፃፀር ለምርምር አመቺ የሆኑ ነገሮችን የማግኘት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ከአፍሪቃ ዕጩ ማቅረብ ቀላል አይደለም።»

Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

ለጀርመኑ አሌክሳንደር ሁምቦልድት ተቋም ሽልማት ዕጩነት የበቁት ፕሮፌሰር ጽጌ በመድኃኒት ቅመማ ዘርፍ ምርምር በማኪያሄድ ብቻ አልተወሰኑም። በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተገኝተው ከ50 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችንም አቅርበዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በድረ-ገጹ ያሰፈረው የሥራ ልምዳቸው እንደሚያመክተው ፕሮፌሰር ጽጌ ከ40 በላይ ተማሪዎችን ለሁለተኛ ዲግሪ ጥናታቸው አማክረዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ለሁለተኛ ዲግሪ የሚያጠኑ 15 ተማሪዎችን እንዲሁም ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ምርምራቸውን የሚያኪያሂዱ አራት ተማሪዎችንም በማማከር ላይ እንደሚገኙ ፕሮፌሰር ጽጌ ተናግረዋል። ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድኅረ-ምረቃ ጥናት እና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የፋርማሲ ትምህርት ቤት ዲን ኾነውም አገልግለዋል። 

እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር እስካሁን ላበረከቱት አስተዋጽዖ በማርቲን ሉተር ሐለ ዩኒቨርሲቲ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ በመባል የ60,000 ዩሮ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ፕሮፌሰር ራይንሃርድት ተናግረዋል። ከዚህ የገንዘብ ሽልማት በተጨማሪም ፕሮፌሰር ጽጌ ጀርመን ውስጥ ጥናት ለማኪያሄድ መቆየት እንደሚችሉም ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ገልጠዋል። 

«ከዚህ በተጨማሪ የዶክትሬት አጥኚዎችን ይዞ ወደ ጀርመን መምጣት ይችላል። ከየካቲት እስከ ሐምሌ ድረስ ለግማሽ ዓመትም እኛ ጋር ሐለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መቆየት ይችላል።»

አሌክሳንደር ሁምቦልት ተቋም በየዓመቱ ሽልማት ከመስጠቱም ባሻገር የምርምር ወጪ ድጋፍም ያደርጋል። ፕሮፌሰር ፅጌ የአሌክሳንደር ሁምቦልት የትምህርት ወጪ ድጋፍ አግኝተው ጀርመን ጥናት ያከናወኑት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1994 እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ ነው። ተቋሙ በመላው ዓለም ለሚገኙ ስድስት ተመራማሪዎች በየዓመቱ የጊኦርግ ፎስተር የምርምር ወጪ ድጋፍ ያደርጋል። በተቋሙ ድጋፍ ጥናት ለማከናወን በየዓመቱ የሚላኩ ማመልከቻዎች ከጥር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ማለፍ አይገባቸውም። 

በርካታ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎችም በአሌክሳንደር ሁምቦልት የምርምር ተቋም የትምህርት ወጪ ድጋፍ እየተደረገላቸው ወደ ጀርመን በማቅናት ሐለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የዶክትሬት ጥናታቸውን አከናውነዋል። ፕሮፌሰር ጽጌ ከሐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተባብሮ በመሥራት እስካሁን ሁለት ዐሥርት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ለጀመሪያ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲው ጋር መሥራት የጀመሩት በ1996 ዓ.ም ነው። ከዩኒቨርሲቲው ጋር የሚያደርጉት ትብብር እንደቀጠለ ነው።

Martin Luther Universität in Halle
ምስል picture-alliance/ ZB

«በዚህ ዓመት አንድ ትልቅ ምርምር ለማከናወን የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት ፍቃድ ጸድቋል። ይኽን ምርምር ገና ከጽንሱ አንስቶ በማሳደጉ ላይ ፕሮፌሰር ጽጌ ድርሻው ከፍተኛ ነው። ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ፣ ቦትስዋና፣ ካሜሩን እንዲሁም ታንዛኒያ የሚገኙ ተመራማሪዎችን የሚያስተሳስር ግዙፍ መረብ ነው። በዚህ የትብብር ፕሮጀክት ፕሮፌሰር ጽጌ ድርሻው ላቅ ያለ ነው። እኔ ጡረታ በመውጣቴ አብሮት የሚሠራው ሌላ ባልደረባዬ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ከጀርባ ሆኜ በመጠኑ ድጋፍ አደርጋለሁ።»

ለዚህ ፕሮጀክት የጀርመን መንግሥት 800 ሺህ ዩሮ እንደመደበላቸው ፕሮፌሰር ጽጌ ገልጠዋል። ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በፊት ፕሮፌሰር ጽጌ በሐለ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ኾነው ሲሠሩ በወቅቱ የቅርብ አማካሪያቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ራይንሃርድት ኖይበርት ነበሩ። ፕሮፌሰር ራይንሃርድት በሐለ ዩኒቨርሲቲ የባዮፋርማሲ ክፍል ውስጥ እስከ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ድረስ በመምህርነት አገልግለዋል። ጡረታ ከወጡ ደግሞ አንድ ዓመት ተቆጥሯል። 

በስልክ ልናናግራቸው በደወልን ጊዜ ከዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል መሆኑን ሲያውቁ ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጽጌን ያገኙ ያኽል እንደተሰማቸው በፈገግታ ተውጠው ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ጽጌም ከጀርመናውያኑ ፕሮፌሰሮች ጋር ቅርበታቸው የቤተሰብ ያኽል መኾኑን ተናግረዋል። ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ሽልማታቸውን ለመቀበል የሚመጡበት ቀን እስኪደርስ በጉጉት ነው የሚጠብቁት። ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ሽልማታቸውን በይፋ የሚቀበሉት ከአራት ወራት በኋላ እንደሆነ የጀርመኑ ሐለ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል። የክብር ተሸላሚው ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም በሕይወት ዘመናቸው ስኬታማ ተመራማሪ ናቸው። ለብዙዎች ላልተሳካላቸው ግን ሕልም አላቸው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 
ሸዋዬ ለገሰ