1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያውያኑ ዶላር፣ ሥራ እና መመለሻ በጠፋባት ሊባኖስ

ረቡዕ፣ ሰኔ 10 2012

በሊባኖስ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸው ጎዳና ላይ ተጥለዋል።የወደቁትን እኛ ለእኛ የተባለው የበጎ አድራጎት ማኅበርና የሊባኖስ መንግሥት ቢያነሱም ችግሩ ወደፊት ለሚከሰት ሌላ ቀውስ ማስጠንቀቂያ ይመስላል።የእኛ ለእኛ አባል የሆነችው መቅደስ «ዛሬ የተዋረድንው እንደግለሰብ ነው። ነገ የምንዋረደው እንደ ሀገር ነው» ስትል አስጠንቅቃለች

https://p.dw.com/p/3dwXq
Libanon Beirut | entlassene Haushaltshilfen aus Äthiopien
ምስል Mekdes Ylima

«ዛሬ የተዋረድንው እንደግለሰብ ነው። ነገ የምንዋረደው እንደ ሀገር ነው» ኢትዮጵያውያኑ በሊባኖስ

ላለፉት ሶስት አመታት በሊባኖስ በሰው ቤት ተቀጥራ የሰራችው ንጹህ ፍቅር ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ብትፈልግም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ድንበሮች ተዘግተው የአውሮፕላን በረራዎች በመቋረጣቸው አልተሳካላትም። "ከኢትዮጵያ ስንመጣም [አሰሪዎቻችን] ናቸው የቆረጡልን። መሸኘት ያለባቸውም እነሱ ናቸው።  አሁን ግን የትኬት ዋጋ በጣም ውድ ነው። [መመለስ እንደምፈልግ አሰሪዎቼ] ያውቃሉ። ግን መደበኛ በረራ እስካልተጀመረ ድረስ እንደማይሸኙኝ ነው የነገሩኝ" ስትል ትናገራለች።

ከአሰሪዎቿ የገባችው ውል ተጠናቆ መመለስ አለመቻሏ ሁለት ተጨማሪ ሥጋቶች ይዞ መጥቷል። አንድም በውሏ መሠረት ባለመመለሷ በነፃ ልትሰራ ትገደዳለች፤ አንድም ባለፉት ሳምንታት ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑት አሰሪዎቿ ጎዳና ላይ አውጥተው ይጥሏታል። 

ይኸ ሥጋት ግን የንጹህ ብቻ አይደለም። ሶፊ መሐመድ ሊባኖስ በሰራችባቸው አመታት ያጠራቀመችውን ገንዘብ ለቤት ኪራይ እየከፈለች የለት ኑሮዋን ትገፋለች። "አገሬ ከገባሁ ብዬ ለትኬት ቀድሜ ያስቀመጥኩትን ወይ ከታመምኩ ብዬ ያስቀመጥኩትን ብር ነው እስካሁን ስበላ የነበረው" የምትለው ሶፊ ከሶስት ጓደኞቿ ጋር በወር 300 ዶላር የሚከፍሉበት ቤት ተከራይታ ትኖራለች። የኮሮና ወረርሽኝ ከበረታ በኋላ ግን ቀድሞም ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በተዘፈቀችው ሊባኖስ እንደ ሶፊ ላሉ ኢትዮጵያውያን ሥራ ጠፍቷል። "በዚህ ከቀጠለ እኔም [ጎዳና] መውጣቴ አይቀርም። ምክንያቱም ካልከፈልክ ማንም አያኖርህም" ስትል ሥጋቷን ለዶይቼ ቬለ አጋርታለች።

የሊባኖስ ሰራተኞች ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄኔራል ማርላይን አታላህ ለእንደ ሶፊ እና ንጹህ አይነቶቹ ኢትዮጵያውያን የሚያረጋጋ ምላሽ የላቸውም። አታላህ «በሊባኖስ ባለው የኤኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ለወደፊቱ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል። በቂ ዶላር ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ትውልድ አገራቸው ቢመለሱ የተሻለ ነው። ለሰራተኞቹ ደሞዝ ለመክፈል በአሁኑ ወቅት ዶላር ማግኘት ቀላል አይደለም። ቀጣሪዎቻቸው በሊባኖስ ሕግ የተደነገገውን ዝቅተኛ ደሞዝ መክፈል አይችሉም» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በሊባኖስ ጎዳና

Libanon Beirut | entlassene Haushaltshilfen aus Äthiopien
በአሰሪዎቻቸው ጎዳና ከተጣሉ ኢትዮጵያውያን መካከልምስል Mekdes Ylima

በሊባኖስ ባለፉት ሳምንታት ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች በቀጣሪዎቻቸው ተባረዋል። አሰሪዎቻቸው በቤይሩት ከተማ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ደጃፍ ጥለዋቸው የሔዱ የቤት ሰራተኞች ለቀናት ጎዳና ላይ አንድ ሕንፃ ጥግ የተወሰኑት ተኝተው የተወሰኑ ደግሞ መንገድ ላይ ቆመው ይታዩ ነበር። ኢትዮጵያውያኑን ለመርዳት ደፋ ቀና የሚለው እኛ ለእኛ የተባለው የበጎ አድራጎት ማኅበር አባል የሆነችው መቅደስ ይልማ «በቆንስላው ሥር የሚተዳደረው ኮምዩኒቲ ከሶስት ቀን በፊት ወደ 33 ልጆችን አንስቷል። ካሪታስ ያነሳቸው ወደ 37 ልጆች አሉ። ከካሪታስ [መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት] በኋላ እኛ ለእኛ እና የተለያዩ ድርጅቶች አብረውን ሆነው 28 ልጆች አንስተናል። አሁን ደግሞ ኤምባሲው በር ላይ ስምንት ልጆች አሉ» ስትል ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

መንገድ ላይ ከተጣሉት መካከል አንዷ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ትሰራ የነበረችው ብርሀኔ መንግስቱ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቤይሩት በሚገኝ አንድ ሆቴል ተቀምጣ እየተጠባበቀች ነው። ብርሀኔ ሆቴል ተቀምጣ ወደ ትውልድ አገሯ ለመመለስ እንድትጠባበቅ የተገደደችው አሰሪዋ ቤይሩት ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ደጃፍ ወስደው ከጣሏት በኋላ ነበር። መቅደስ ይልማ አባል የሆነችበት እኛ ለእኛ የተባለው የበጎ አድራጎት ማኅበር ከተጣለችበት የቤይሩት ጎዳና ባያነሳት ኖሮ የምትሔድበት አልነበራትም። አሰሪዋ ሲያባርሯት የምትለብሰው ልብስ እንኳ አልያዘችም። «ታክሲ የሚሰራ ልጅ ቤት አለ። እሱ አምጥቶ ጥሎኝ ሔደ። ምንም ነገር አልነበረኝም። ልብስ እና ሻንጣ እዚህ መጥቼ ነው ጓደኞቼ የሰጡኝ። ምንም ነገር አልነበረኝም። ፔስታል ይዤ ነው የወጣሁት» ስትል ብርሀኔ የተፈጠረውን አስረድታለች።

ብርሀኔ እንደምትለው እግሯ ከኢትዮጵያ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ተቀጥራ የሰራችበት የዘጠኝ ወር ደሞዟ አልተከፈላትም። ከሊባኖሳዊ ቀጣሪዋ በቤት ሰራተኝነት ለምታገለግልበት በወር 150 ዶላር ሊከፍሏት ውል ነበራት። ይሁንና የዘጠኝ ወር ደሞዝ በአጠቃላይ 1350 ዶላር ደሞዟን ከልክለዋታል።

እንደ ብርሀኔ ሁሉ ቤይሩት በሚገኝ አንድ ሆቴል ተቀምጣ ወደ ኢትዮጵያ የምትመለስበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ የምትገኘው ወይንሸት እሸቱ ለሶስት አመታት ከስምንት ወራት ገደማ በሊባኖስ ኖራለች።  ወይሸት እንደምትለው አንድ ቤት ተቀጥራ ለሁለት ቤተሰብ እንድትሰራ ተዳለች፤ ደሞዝ ተከልክላለች። ታማ ሕክምና አላገኘችም። ከአሰሪዋ የተስማማችው የስራ ውል ካለቀ ጀምሮ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ሞክራለች። ጥረቷ ግን አልተሳካም።

ወይንሸት በአሰሪዎቿ የደረሰባትን በደል ከኢትዮጵያ ወደ ሊባኖስ ለወሰዳት ድርጅት ብትናገርም መፍትሔ አልተገኘላትም። የገጠማትን ውጣ ውረድ ስትናገር እምባ እና ሳግ የሚተናነቃት ወይንሸት አሰሪዎቿ ከኢትዮጵያ ቆንስላ ደጃፍ ወስደው እስኪጥሏት ድረስ በሕይወቷ የገጠማት ፈተና ከአቅሟ በላይ ሆኖ ነበር።

የሊባኖስ የሰራተኞች ሚኒስቴር በአሰሪዎቻቸው ተባረው ከኢትዮጵያ ቆንስላ ደጃፍ የተጣሉ የቤት ሰራተኞች መኖራቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። የሊባኖስ ሰራተኞች ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄኔራል ማርላይን አታላህ «በሊባኖስ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ ቢፈልጉም በኮሮና ምክንያት አውሮፕላን ማረፊያ በመዘጋቱ እና በረራ በመቋረጡ ምክንያት ችግር ተፈጥሯል። በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን ሕገ ወጥ ናቸው። መስሪያ ቤታችን ካሪታስ ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር መንገድ ላይ ወድቀው የነበሩትን ለሁለት ቀናት በሆቴል ካቆያቸው በኋላ ወደ መጠለያ ወስዷቸዋል። ወደ አገራቸው መመለስ ስለሚፈልጉ ከሊባኖስ የጸጥታ መስሪያ ቤት ጋር ስላሉበት ሁኔታ እየተነጋገርን ነው። የኢትዮጵያውያኑ የመኖሪያ ፈቃድ እና ሕጋዊነታቸው እየተጣራ ነው» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያኑ የቤት ሰራተኞች እንደሚሉት ቀጣሪዎቻቸው ሲያባርሯቸው "ዶላር የለም" የሚል ምክንያት ይሰጧቸዋል። በእርግጥ ባለፉት አመታት ከፖለቲካዊው ቀውስ ጋር ተደማምሮ የሊባኖስ ኤኮኖሚ ክፉኛ ተዳክሟል። መቅደስ እንደምትለው ግን የኢትዮጵያውያኑ ሁኔታ በኮሮና ወረርሽኝ ይባባስ እንጂ ችግሩ ስር የሰደደ ነው።

በቤሩት ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት «ሰራተኞች ወደ አገራቸው መመለስ ሲፈልጉ እንዲመለሱ የማድረጉ ኃላፊነትም የአሰሪዎች ነው» የሚል ፅሁፍ በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።

ቀጣሪዎች «የትራንስፖርታቸውን ይሁን ሌሎች ወጭዎችንም መሸፈን ግዴታ አለባቸው» የሚለው የኢትዮጵያ ቆንስላ «የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን እና አሰሪዎች ጋ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ራሳቸውን ጨምሮ፣ አሰሪዎች፤ ሊባኖሳውያን እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የሰው አዘዋዋሪዎችም ያለባቸውን ኃላፊነት በመጣስ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ የትራንስፖርታቸውን እና ሌሎች ወጭዎችን ሸፍኖ እንዲልክ በቆንስላው በመገኘት ትልቅ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ» ብሏል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ በቀጥታ ስልክ በመደወልም ሆነ ለኃላፊዎቹ አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረኩት ሙከራ አልተሳካም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ወር ከሊባኖስ 335 የቤት ሰራተኞችን መልሷል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ድዔታ ጽዮን ተክሉ ከሊባኖስ የተመለሱትን ከተቀበሉ በኋላ እንዳሉት ግን መንግሥታቸው «እጅግ ተጋላጭ» ካላቸው ውጪ ያሉትን መመለስ አይችልም። ምኒስትር ድኤታዋ እንዳሉት "እጅግ ተጋላጭ ካልሆኑ በስተቀር በዚህ ወቅት ወደ አገራቸው አይመለሱም። ነገር ግን ከሚኖሩበት አገር መንግሥት፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ከመንግሥታችን ጋር በመተባበር ባሉበት እንረዳቸዋለን። ከዚያ በተጨማሪ ዛሬ ከቤይሩት የተመለሱ 335 ሰዎች ተቀብለናል። ተጨማሪ የሚመለሱ ይኖራሉ። በአጠቃላይ 649 ናቸው። ይኸ ትንሽ ቁጥር ነው። ነገር ግን በሚኖሩበት ለመርዳት የበለጠ ትኩረት አድርገናል" ብለዋል።

በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ ቁጥር አይታወቅም። በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ከ300 ሺህ እስከ 400 ሺህ ሊደርሱ እንደሚችሉ ይገምታል። በኮሮና ወረርሽኝ፤ በሊባኖስ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ካንዣበበባቸው አደጋ ኢትዮጵያውያኑን ማዳን ከባድ የቤት ስራ ይመስላል። መቅደስ ግን ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገራቸው ከመመለስ ውጪ ምንም አማራጭ የለም ስትል ትናገራለች።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ