1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኤርትራውያን ስደተኞች እና የሥራ ፈቃድ እጦት 

ረቡዕ፣ የካቲት 29 2009

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖሩ  ኤርትራውያን ስደተኞች ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ አለማግኘታቸው ፈተና እንደጋረጠባቸው የብሪታኒያው ዓለም አቀፍ የልማት ጥናት ተቋም ይፋ ያደረገው ዘገባ ገልጧል። ዘገባው የሥራ ፈቃድ እጦት ኤርትራውያኑ ለሁለተኛ ስደት እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል ብሏል።

https://p.dw.com/p/2Yqlc
Bildergalerie Flüchtlingscamp Tigray in Äthiopien
ምስል Milena Belloni

ኤርትራውያን ስደተኞችና የሥራ ፈቃድ እጦት 

ኤርትራዊው ዳዊት ድንበር አቋርጦ በትግራይ ክልል ከሚገኘው የአዲ ሐሩሽ የስደተኞች ጣቢያ ሲጠለል በሙያው ሰርቶ አረጋዊ ቤተሰቦቹን ለመርዳት እቅድ ነበረው። በትውልድ አገሩ ኤርትራ የጤና ባለሙያ ሆኖ የሰለጠነው ዳዊት በአውሮጳ ተምረው ሰርተው ለመኖር ወደ ቻሉ ጓደኞቹ መሔድም ያልማል። ግን መንገዱን አላገኘውም። በዩናይትድ ስቴትስ፤ አውሮጳ አሊያም ካናዳ ዘመድ የለውም። በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መንገድ ለመጓዝ የሚከፍለው ገንዘብ አሊያም የሚከፍልለት ወዳጅ ዘመድ የለውም። ወጣቱ ኤርትራዊ በሚኖርበት የአዲ ሐሩሽ የመጠለያ ጣቢያ አካባቢ አነስተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ከሚኖረው ይልቅ በሙያው በሕክምናው ዘርፍ መሰማራትን ይሻል። 

ዳዊት፤ የብሪታኒያው ዓለም አቀፍ የልማት ጥናት ተቋም ባለፈው ወር ይፋ ባደረገው ዘገባ ካነጋገራቸው ኤርትራውያን መካከል አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የተጠለሉ ኤርትራውያን ፈተናዎችን የፈተሸው ዘገባ ሁለተኛ ዙር ስደት እንዳይገቡ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት የመሥራት ፈቃድ ባለማግኘታቸው ምክንያት መንምኗል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።  ስደተኞቹ በሚኖሩባቸው መጠለያ ጣቢያዎች የሚደረግላቸው መሰረታዊ እርዳታ፣የሙያ ሥልጠና እና የብድር አቅርቦት ለአጭር ጊዜ ኤርትራውያኑን ቢረዳቸውም መሥራት አለመቻላቸው ሁነኛ ፈተና መሆኑን ይኸው ዘገባ አትቷል። ዘገባውን ካጠናቀሩት ጄሲካ ሔጀር ዛንከር አንዷ ናቸው። «ኤርትራውያን እና ሌሎች ስደተኞች ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው የተሻለ ሕይወት ይመኛሉ። ጥሩ ሥራ መያዝ፤ ክሒሎቶቻቸውን መጠቀም እንደ ዳዊት የሚፈልጉትን መማር ይፈልጋሉ። ይኸ እንደማይሳካ በኢትዮጵያም ጥሩ ሕይወት መመስረት እንደማይችሉ ሲያውቁት ብዙዎቹ ባገኙት አጋጣሚ ለመውጣት ይወስናሉ።» በጥናቱ መሰረት በየወሩ 5,000  ኤርትራውያን አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። አስገዳጁ ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት፤ ፖለቲካዊ አፈና እና ውስን ኤኮኖሚያዊ አማራጭ ኤርትራውያኑን በተለይም ወጣቶቹን ለሥደት ከሚዳርጓቸው መካከል ይጠቀሳሉ። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) መረጃ መሰረት 155,000 ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ዉስጥ ተጠልለዋል።። ጄሲካ ሔጀር ዛንከር እንደሚሉት ለብዙዎቹ ኑሮ ከባድ ነዉ።
«በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን እና ሌሎችም ስደተኞች ያለባቸው ፈተና የሥራ ገበያውን መጠቀም አለመቻላቸው ነው። ስለዚህ በሕጋዊ መንገድ ተቀጥረው መስራት አይችሉም። በመጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩት አብዛኞቹ ኤርትራውያን ስደተኞች ውስን የኑሮ መደጎሚያ ነው ያሏቸው። እድለኛ የሆኑ ጥቂቶች መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ሥራ ያገኛሉ። ጥቂቶች አነስተኛ የንግድ ሥራዎች አሏቸው። ብዙዎቹ ግን ምንም አይነት ሥራ ማግኘት አይችሉም። ይህም ማለት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅትበሚያገኙት የምግብ እደላ ለመኖር ይገደዳሉ። አይራቡም፦ነገር ግን ቅያሪ ልብስ አሊያም ለልጆቻቸው ጫማዎች የሚገዙበት ቤተሰቦቻቸውንም የሚያግዙበት መንገድ የለም። እንዲያውም በቤተሰቦቻቸው እና ከውጭ በሚላክላቸው ገንዘብ ላይ ጥገኛ ናቸው። በከተማ ለሚገኙ ስደተኞችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በተዘዋዋሪ መንገድ ሥራ ቢያገኙም መደበኛ ያልሆነ እና ዝቅተኛ ክፍያ የሚገኙበት ነው»
ባለፈው አመት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት በኢትዮጵያ በሚገኙ ስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ከመዘገባቸው ኤርትራውያን መካከል 82,000ዎቹ እዚያ አለመኖራቸውን ገልጦ ነበር። ምዕራባውያን አገራት እና ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ኤርትራውያኑ ለሁለተኛ ስደት መንገድ እንዳይጀምሩ የሚያቀርቧቸው ድጋፎች ቢኖሩም እስካሁን ውጤታማ የሆኑ አይመስልም። 
«ሁለተኛ ስደትን ለመከላከል ለጋሾች የመሰረታዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። የክህሎት ስልጠና ይሰጣል። ስደተኞቹ በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ እንዲሁም ወደ ሌላ አገር ዳግም ለስደት እግራቸውን እንዳያነሱ ብድር ይሰጣቸዋል። እነዚህ ድጋፎች በተወሰነ ደረጃ ስደተኞቹ ራሳቸውን እንዲችሉ አግዘዋቸዋል። ስልጠናዎቹ ቢሰጡም ተግባር ላይ አይውሉም። ስደተኞቹ የንግድ ሥራ ቢጀምሩ እንኳ ሁሉም ተመሳሳይ ይሆናል። ገበያቸው እጅግ ውስን ነው። እናም እነዚህ እቅዶች እንደታሰበው በአግባቡ አይሰሩም። ይኸም ብዙዎቹ ሥራ መስራት ወደሚችሉበት ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ወደ ሚጀምሩበት አገር ለመሰደድ እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል።»ባለፈው አመት የሜድትራኒያን ባሕርን በማቋረጥ 360,000 አፍሪቃውያን  ወደ አውሮጳ መሻገራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ይጠቁማል። በዚያው አመት 15,000 ኤርትራውያን ኢጣሊያ መድረሳቸው ተገልጧል። ወደ አውሮጳ የሚጓዙ ስደተኞችን ባሉበት ለመግታት ደፋ ቀና የሚሉት ምዕራባውያን ለኤርትራውያኑ አሁን በተጠለሉበት ሥራ ሊፈጥሩላቸው ይሻሉ።ኢትዮጵያ ከአውሮጳ የመዋዕለ-ንዋይ ባንክ ጋር በመተባበር ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ማቀዷ የተሰማዉ ባለፈው አመት ነበር። በእቅዱ መሠረት ለ30,000 ስደተኞች የሥራ እድል ለመፍጠር ታስቧል። ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቀውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የዓለም ባንክ፣ብሪታኒያ እና የአውሮጳ ኅብረት አባል አገራት እንደሚሳተፉበት ተገልጧል። 
«ባለፈው መስከረም በኒው ዮርክ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግስት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ 'ኢትዮጵያ ኮምፓክት' በተሰኘ ማዕቀፍ ላይ ከሥምምነት ደርሰዋል። የዚህ ማዕቀፍ የመጀመሪያ እርምጃ ለሥደተኞች የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በዚህ እቅድ መሰረት ለኢትዮጵያውያን እና ለስደተኞች የሥራ እድል እንዲፈጠር ፋብሪካዎች እንዲቋቋሙ ታስቧል። ይመስለኛል በፋብሪካዎቹ የሚፈጠረው የሥራ እድል 80 በመቶ ለኢትዮጵያውያን ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ ለስደተኞች እንዲሆን ታቅዷል። ይኸ እቅድ ለኢትዮጵያውያን ጭምር የስራ እድል እንዲፈጥር መታሰቡ ላቅ ያለ ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያንም ያላቸው የሥራ እድል መደበኛ ያልሆነ እና ዝቅተኛ ክፍያ የሚያገኙበት ነው። በአገሪቱ ያለው የሥራ አጥነት ከፍተኛ ነው። እናም የመስራት እድሉን ለስደተኞች ብቻ መስጠት አሳሳቢ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትም ለስደተኞች በቀጥታ የስራ ፈቃድ እንዲሰጥ ልንጠብቅ አንችልም። ይኸ በትናንሽ እርምጃዎች ኤኮኖሚው ሲያድግ በሒደት የሚደረግ ይሆናል።»
የዓለም ባንክ በ300  ሚሊዮን ዶላር ዮርዳኖስ  ላይ ከአንድ አመት በፊት ተግባራዊ አድርጎታል። እቅዱ የዮርዳኖስን ኤኮኖሚ በማሳደግ በአገሪቱ ለተጠለሉ የሶርያ ስደተኞች የስራ እድል በመፍጠር ላይ አተኩሯል። ምዕራባውያን በተለይም የአውሮጳ አገራት ስደተኞችን ባሉበት ለመግታት ከሚወስዷቸዉ አዳዲስ ርምጃዎች መካከል አንዱ ነው። የዓለም አቀፍ የልማት ጥናት ማዕከል ተመራማሪዋ ጄሲካ ሔጀር ዛንከር የኢትዮጵያው ዕቅድ እንደ ዮርዳኖሱ ሁሉ ስኬታማ ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸው። የትግበራው ሒደት ግን ቀላል ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል። የብሪታኒያው ዓለም አቀፍ የልማት ጥናት ተቋም ዘገባ እንደሚጠቁመው አብዛኞቹ ኤርትራውያን ኢትዮጵያን እንደ መሸጋገሪያ ለመጠቀም የመጠቀም ኃሳብ አላቸው። በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት አሊያም በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በኩሉ አውሮጳ፤ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ የመጓዝ ኃሳባቸው ሲዘገይ ህገ-ወጡን መስመር ለመምረጥ እንደሚገደዱ ጄሲካ ሔጀር ይናገራሉ።
«አብዛኞቹ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት በሕይወታቸው መስራት ስለሚፈልጉት ግልፅ እቅድ ሳይኖራቸው ነው። ወደ ኢትዮጵያ ሲሻገሩ ቀዳሚ ዓላማቸው ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ ነው። እዚያ ከደረሱ በኋላ የሕይ,ወታቸውን ግብ መተለም ይጀምራሉ። ለትውልድ አገራቸው ቅርብ በመሆኑ፤ የባሕል መመሳሰል ስላለ ብዙዎቹ በመጀመሪያ በዚያው ለመቆየት ይፈልጋሉ። በተለይ ሕፃናት እና ሴቶች ያሏቸው ቤተሰቦች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሰሐራ በርሐን የማቋረጥ ፍላጎት አልነበራቸውም። በሒደት ግን በኢትዮጵያ የተመቻቸ ኑሮ መምራት እንደማይችሉ እየተገነዘቡ መጥተዋል። በሕጋዊ መንገድ ወደ አውሮጳ ም ሆነ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጓዝ እድላቸው ጠባብ መሆኑን ታዝበዋል። ስለዚህ አመታት ባለፉ ቁጥር ሕጋዊ ያልሆነው የስደት መንገድ ሳይወዱ በግድ አማራጭ ሆኗቸዋል።»

Bildergalerie Flüchtlingscamp Tigray in Äthiopien
ምስል Milena Belloni
21.01.2013 Karte Eritrea Asmara eng
Bildergalerie Flüchtlingscamp Tigray in Äthiopien
ምስል Milena Belloni


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ