1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዚምባብዌ ተሀድሶ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 15 2011

የዚምባብዌ የጦር ኃይል ሀገሪቱን ለአራት አሰርተ ዓመታት ገደማ ያህል የመሩትን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን  ከአንድ ዓመት በፊት ከስልጣናቸው እንዲነሱ ባደረገበት ጊዜ የጀርመን ፖለቲካ ዘርፍ እፎይታ ተሰምቶት ነበር።

https://p.dw.com/p/38oGw
Wirtschaftskrise in Simbabwe
ምስል picture alliance/AP Photo/T. Mukwazhi

«የሰብዓዊ መብቶች መከበርን በተመለከተ አሁንም ገና ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ።»

ይሁንና፣ በርሊን የሚገኘው የጀርመን መንግሥት የሙጋቤ ከስልጣን መውረድ ሀገሪቱን ከብዙ ዓመታት የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በኋላ ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና ይመልሳታል  በሚል ይዞት የነበረውን አስተሳሰብ እና አሳድሮት የነበረውን ተስፋ ዛሬ ከአንድ ዓመት በኋላ ያጣ ይመስላል።  
« ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ዓቢይ የፖለቲካ እና ኤኮኖሚያዊ ተሀድሶ ለውጥ ያነቃቃሉ ብለን  ተስፋ አድርገን ነበር ፣ ሆኖም፣ እስካሁን ንዑሱን ለውጥ ብቻ ነው ያየነው። » ሲሉ አንድ  ዲፕሎማቲክ ምንጭ ለ DW ተናግሯል። በምዕራባውያን ታዛቢዎች አመለካከት መሰረት፣ ኤመርሰን ምናንጋግዋ  ለቀድሞው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ዋነኛ ምሰሶ ሆነው ባገለገሉት የፍትሑ እና የደህንነቱ ዘርፎች ላይ እስካሁን ተሀድሶ ማድረግ ተስኗቸዋል። በተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሲቭል ማህበረሰቦች ላይ ጭቆናው አሁንም እንደበፊቱ ቀጥሏል።  ከሙጋቤ በኋላ ባለፈው ሀምሌ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው እና የማጭበርበር ተግባር  ታይቶበታል በሚል ወቀሳ የቀረበበት፣  ግጭት የታከለበት አከራካሪው ፕሬዚደንታዊ ምርጫም የጀርመንን እምነት በማሳደጉ ረገድ ያስገኘው  ድርሻ የለም ። የፕሬዚደንታዊው ምርጫ ውጤት ዘገየ በሚል ባለፈው ነሀሴ ወር ተቃውሞ ለማሰማት አደባባይ ከወጡት መካከል የፀጥታ ኃይላት ስድስቱን መግደላቸውም የሚታወስ ነው።
የፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ መንግሥት ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተሀድሶዎችን ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑን የሚጠቁሙ ብዙ ምልክቶች ማሳየቱን፣ ግን፣ እስካሁን ያን ያህል የተለወጠ ነገር አለመኖሩን DW ያነጋገራቸው በዚምባብዌ የሚገኘው  የክርስትያን ዴሞክራቶች ህብረት ፣ በምህፃሩ ከሴ ዴ ኡ ጋር ቅርበት ያለው የጀርመናውያኑ ኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ዴቪድ ምቤ  ገልጸዋል።
« ስለ ፕሬስ፣  ስለ ሀሳብ የመግለጽ እና ስለ መሰብሰብ ነፃነት፣ እንዲሁም፣ ስለ መሰረታዊ መብቶች መከበር  ተነጋግረናል። እርግጥ፣  ይህ ጥያቄ ፣  የዚምባብዌ መንግሥት  አስፈላጊውን ተሀድሶ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው አዎንታዊ  ምልክት ያሳየበት አንዱ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ፣ እስካሁን በተግባር የታየ ነገር የለም።  ዓለም አቀፍ አጋሮቻችንም  ልክ እንደ እኛ ይህን እውን ሆኖ ለማየት በመጠባበቅ ላይ ያሉ ይመስለኛል። »
በሌላ በኩል ግን፣ የዚምባብዌ መንግሥት የግል ባለሀብቶችን እና ምዕራባውያን መንግሥታትን እንደገና ወደ ሀገሩ ለ  መሳብ ጥረቱን አጠናክሯል። ፕሬዚደንት ምናንጋግዋም « ዚምባብዌ ለንግድ ክፍት ናት» የሚለውን መፈክራቸውን ደጋግመው አሰምተዋል፣ ጀርመን ወይም ብሪታንያን ከመሳሰሉ ከምዕራባውያት ሀገራትም ጋር  ግንኙነቱን መልሰው ለማደስ በይፋ ቃል ገብተዋል።  ይህ አነጋገራቸው ሀገሪቱ  ቢያንስ የቀድሞው ፕሬዚደንት ከተከተሉት ከከሩቅ ምስራቅ ሀገራት ጋር የመቀራረብ ፖሊሲ መለያየቷን የሚጠቁም ሆኖ ታይቷል። እንደሚታወሰው፣ ዚምባብዌ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት በመጀመሪያዎቹ የ2000 ዓመታት ከሻከረ በኋላ ሙጋቤ ከቻይና ጋር የቅርብ ግንኙነት ፈጥረዋል። ሙጋቤ የጭቆና አገዛዛቸውን በማጠናከር፣  በተለይ የነጮች የእርሻ ቦታዎችን ከወረሱ እና በተቃዋሚ ቡድኖች ፖለቲከኞች፣ የግል መገናና ብዙኃን ተቋማት እና በሲብሉ ማህበረሰብ ላይ ጥቃቱ እያለ በሄደበት ጊዜ ጀርመን ለዚምባብዌ ትሰጠው የነበረውን የልማት ርዳታ በጠቅላላ በ2002 ዓም  አቋርጣለች። የጀርመን መንግሥት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰብዓዊ ርዳታዋን፣ እንዲሁም ለሲቭሉ ማህበረሰብ ድርጅቶች የምታደርገውን ድጋፍ ቀንሳለች። ታድያ የዚምባብዌ መንግሥት ይህን ምዕራፍ የመዝጋት ፍላጎት እንዳለው የሀገሪቱ የገንዘብ ሚንስትር ፓትሪክ ቺናማሳ  ገልጸዋል።

GMF Logo Konrad Adenauer Stiftung
Simbabwe Präsidentschaftswahl Emmerson Mnangagwa erklärter Wahlsieger
ምስል Getty Images/D. Kitwood

ቺናማሳ የጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሚውለር ባለፈው ነሀሴ ዚምባብዌን ካደረጉት ጉብኝት በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ግንኙነታቸውን እንደገና አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።  በዚምባብብዌ አስፈላጊ በሆነው የስራ ቦታ ፈጠራ ጉዳይ ላይ፣ እንዲሁም፣ የሙያ ስልጠና ኮሌጆችን ማስፋፋትም ላይ ባለስልጣናቱ ተወያይተዋል። ጌርድ ሚውለር እና ፓትሪክ ቺናማሳ ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከልም ዚምባብዌ ኤኮኖሚያዊ ችግሮቿን መቀነስ የምትችልበት ብድር ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ አንዱ እንደነበር የኮናራድ አድናወር የፖለቲካ ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ዴቪድ ምቤ አስታውቀዋል።
«  የኤኮኖሚው ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በዚህ ወር የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ተመዝግቧል። የምግብ ዋጋ በጣም ተወዷል፣ የሰዉ ደሞዝ ጭማሪ ባላሳየበት ባሁኑ ጊዜ የምግቡ ዋጋ በሁለት እና በሦስት እጥፍ ነው የጨመረው።  ብዙ ገንዘብ የማያገኘው ሰፊው ህዝብ ኑሮውን መምራት እጅግ አዳጋች ሆኖበታል። በሀገሪቱ የዳቦ፣ የምግብ ዘይት እና የየነዳጅ እጥረት ይታያል። አንዳንዴ ሰዎች ነዳጅ ለመግዛት ሁለት ሰዓት ሙሉ ተሰልፈው መጠበቅ ይገደዳሉ።»
ይሁንና፣ በርሊን የሚገኙ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት፣ ለዚምባብዌ ብድር የሚሰጥበት ሁኔታ ገና አልተደረሰም።  ጀርመን ለዚምባብዌ ብድር ከመስጠቷ በፊት በሀገሪቱ እንዲነቃቃ ስለሚፈለገው ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተሀድሶ ምናንጋግዋ ከሚመሩት መንግሥት ተጨባጭ ሀሳቦችን ማግኘት እንደምትፈልግ ግልጽ ማድረጓ ተሰምቷል።  ዚምባብዌ መክፈል ያለባት የውጭ እዳ ውዝፍ  በወቅቱ 11 ቢልዮን ዶላር ነው። የተቋረጠውን የጋራ ልማት ርዳታን መልሶ የማቋቋም  ጉዳይም ቢሆን በእቅድ አልተያዘም።   በዚህ ወር መጨረሻ ገደማ ከጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚንስቴር አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ሀራሬ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።  ያም ቢሆን ግን፣ ሚንስቴር ለ2018 ዓም  ብድር  መስጠትን በተመለከተ  የመስጠት እቅድ እንደሌለው የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ ለDW በማመልከት፣ የዚምባብዌ መንግሥት የፖለቲካ እና ኤኮኖሚ ተሀድሶ ተግባራዊ የማድረግ ዝግጁነት ለወደፊት የጋራ ግንኑነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚምባብዌ መንግሥት ላይ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ግፊት እንዲደረግ የጀርመናውያን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሪ እያደረጉ ነው።  የሰብዓዊ መብቶች መከበርን በተመለከተ አሁንም    ገና ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች መኖራቸውን የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ቃል አቀባይ ኡቨ ኬኬሪትስ አመልክተዋል።
« በእውነት ፣ አንድም  ሀቀኛ የፖለቲካ ለውጥ አልተመለከትኩም። ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በመትከሉም ረገድ ቢሆን የተደረገ ለውጥ አይታየኝም። የሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከተው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፣ የኤኮኖሚው ሁኔታም አሳሳቢ ነው። ሰዎች መራብ ጀምረዋል። ስለዚህ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ጣልቃ ገብቶ ሰብዓዊ ርዳታ ሊያቀርብ  ይገባዋል። »
ለዚምባብዌ የኤኮኖሚ ልማት ርዳታ መስጠት እንደገና መጀመር እንዳለበት ኡቨ ኬኬሪትስ ቢያስገነዝቡም፣ ይህን ርዳታ በተቻለ መጠን ከመንግሥት በማራቅ፣ ከሲቭሉ ማህበረሰብ ጋር በቅርብ በመተባበር  ቢሰጥ መልካም እንደሚሆን አስታውቀዋል።

GMF Partner Logo BMZ
Simbabwe Finanzminister Patrick Chinamasa trifft deutschen Bundesentwicklungsminister Gerd MÜller
ምስል Imago/photothek

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ