1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦነግ ሶስተኛ ወገን ባለበት ከመንግሥት ጋር ለመነጋገር ጠየቀ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2011

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተፈራረመው ስምምነት ላይ ሶስተኛ ወገን ባለበት ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ። ስምምነቱ አሁን ያለውን አዲስ ኹኔታ "ለማስታረቅና ለመፍታት በሚያስችል" መንገድ እንዲታደስ እና እንዲጠናከር ጠይቋል። የኦነግ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነት ግን እስካሁን ይፋ አልሆነም።

https://p.dw.com/p/3B9H8
 Logo Oromo Liberation Front

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የፈረመው ሥምምነት አሁን ያለውን አዲስ ኹኔታ "ለማስታረቅና ለመፍታት በሚያስችል" መንገድ እንዲታደስ እና እንዲጠናከር ጥሪ አቀረበ። ኦነግ በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረገው መግለጫ ስምምነቱ ሶስተኛ ወገን ባለበት ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የትጥቅ ትግሉን አቁሞ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስማማቱን ያስታወቀው ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ነበር።

በወቅቱ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ ግንባሩ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንደ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ ለመስራት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መስማማቱን ገልጸው ነበር።

አቶ ቶሌራ ስለተደረሰው ስምምነት ሲናገሩ «ኦነግ ወደ ሐገር ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ እንዲሰራ ተስማምተናል።ስምምነቱ ኦነግ ከዚህ በኋላ በኦሮሚያና በመላ ሐገሪቱ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ነዉ።በኦነግ ስም በይፋ፤ ያለምንም ፍራቻ፣ ነፃ ሆኖ መስራት እንደሚቻል ተስማምተናል» ብለው ነበር።

አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች እና በኤርትራ መሽገው የነበሩ ታጣቂዎች ባለፈው መስከረም ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም ሁለቱ ወገኖች የደረሱበት ስምምነት ግን እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በዛሬው መግለጫው "ኢሕአዴግና የመንግስት ስርዓቱ ከጸረ-ዴሞክራሲ ኣቋምና ኣካሄዱ ፈቀቅ ባለማለቱ እዉነተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ወገኖች ለዉጡን ለማሳካትና ስርዓቱንም ለማሻሻል ተሳታፊ እንዲሆኑ ኣልተደረገም" ሲል ተችቷል።

ኦነግ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል ብሏል። ግንባሩ "ጽሕፈት ቤቶቹን ከፍቶ በኣግባቡ እንዳይንቀሳቀስና እንዳይሰራ ለማደናቀፍና ለመገደብ" ጫና እየተደረገበት እንደሆነም አስታውቋል። ኦነግ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነት ተከፍቷል ሲል ወንጅሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሞ ነፃነት ግንባር ግንኙነት በተለይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ክፉኛ ሲሻክር ታይቷል። የኦሮሚያ ክልልን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ ሰንብተዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል በተባሉ የምዕራብ እና የምሥራቅ ወለጋ ዞኖች በተፈጠሩ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በአካባቢው ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ የትምህርት እና የጤና ማዕከላት የሚሰጡት ግልጋሎት ተስተጓጉሏል።

ግጭት እና ኹከት በጠናባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች መሠረታዊ የጤና ግልጋሎት ለመስጠት መቸገሩን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ "የጤና ባለሙያዎች ሆስፒታሎች፣ በጤና ኬላዎች መሥራት እየቻሉ አይደለም። ስፔሻሊስቶቻችን ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎቻችን በዛ አካባቢ በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ የመስራት ፍላጎት የላቸውም። እየተመለሱ ነው ያሉት። አዲስ መመደብም እየተቻለ አይደለም። በአምቡላንስ እጦት ቤታቸው እየወለዱ የሚሞቱ እናቶች ቁጥራቸው እየተበራከተ መጥቷል። በተለያየ ቦታ መድሐኒቶችን ለማድረስ ችግር ሆኗል። የማሕጸን በር ካንሰር የሚከላከል ክትባት እየተሰጠ ነበር። በእነዚህ ዞኖች ውስጥ መስጠት አስቸጋሪ ነው። የሕፃናት ክትባት መስጠት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል" ሲሉ ተናግረዋል

ከሳምንት በፊት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ በስድስት ዞኖች የሚገኙ 810 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን አስታውቆ ነበር። ትምህርት ቤቶች ከተዘጉባቸው ስድስት ዞኖች መካከል ምሥራቅ ወለጋ፤ ቄለም ወለጋ ሖሮ ጉዱሩ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሹማምንት በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከዚህ ቀደም የተፈረመውን ስምምነት እያከበረ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ። የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ቃል-አቀባይ አቶ ታዬ ደንደዓ በአቶ ዳውድ ኢብሳ በሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር "ከ 30 በላይ አመራሮች ተገድለዋል" ሲሉ ወቅሰው ነበር። አቶ ታዬ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የፈረመውን ስምምነት ባለማክበሩ ምክንያት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የጸጥታ መናጋት መፈጠሩን ከአንድ ሳምንት በፊት ተናግረዋል።

በኦሮሞ ነፃነት ግንባር እና በመንግሥት መካከል የተፈጥረውን መቃቃር ለመፍታት በተደጋጋሚ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ሽምግልና ተሞክሯል። እስካሁን የተሞከረው ሽምግልና በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣቱ የታየ ምልክት የለም።