1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ከሮቦቷ ሶፊያ ጀርባ ያሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች

ሐሙስ፣ ግንቦት 30 2010

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ እና የኮምፒውተር ባለሙያዎች ከ“ሰው ሰራሽ አስተውሎት” (Artificial intelligence) በዓለም አቀፍ መድረክ ስማቸው ይነሳ ይዟል። የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ለተሰጣት ለዝነኛዋ “ሶፊያ” ለተባለው ሮቦት የሶፍትዌር ምርቶች በማቅረብ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ድርጅት ለዚህ በአብነት ይነሳል። 

https://p.dw.com/p/2z2vW
USA UN Hauptquartier in New York Sophia humanoider Roboter
ምስል picture-alliance/Photoshot/L. Muzi

ባለሙያዎቹ የ“ሰው ሰራሽ አስተውሎት” ቴክኖሎጂን ተጠቅመዋል  

የኖርዌይዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ እና በሶፊያ መካከል ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በኦስሎ በተደረገ አንድ ስነ ስርዓት ከአንዲት የሀገራቸው እንግዳ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ በመድረክ ታይተው ነበር። የ57 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሚያቀርቡላት ጥያቄ አቀላጥፋ ምላሽ ስትሰጥ የነበረችው እንግዳ ገና ሶስት ዓመቷ ነው። ስሟ ሶፊያ ይሰኛል፤ ዜግነቷ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያዊ። «የሶስት ዓመት ዕድሜ ብቻ ያለው ፍጡር እንዴት አቀላጥፎ ይናገራል?» ለሚል ጠያቂ ሶፍያ የፈጠራ ውጤት እንጂ የሰው ፍጡር አይደለችም ይሆናል መልሱ። 

ሶፍያ ሮቦት ናት - እንደሰው መናገር፣ መቆጣት፣ ማዘን እና መደሰት የምትችል የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ድንቅ ፈጠራ። መቀመጫውን በሆንኮግ ኮንግ ባደረገው እና ሀንሰን ሮቦቲክስ በተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰራችው ሶፍያ ከ50 የሚበልጡ የፊት ገለጻዎችን ማሳየት የምትችል መሆኗ ለየት ያደርጋታል። ሶፍያ ይህን ለማድረግ “ሰው ሰራሽ አስተውሎት” (artificial intelligence) የሚባለውን ቴክኖሎጂ ተገጥሞላታል። ለመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋግሞ የሚነሳው “ሰው ሰራሽ አስተውሎት” (በእንግሊዘኛ ምህጻረ ቃሉ AI) ምን ማለት ነው? የ31 ዓመቱ ጌትነት አሰፋ አይኮግ ላብስ የተባለ በ“ሰው ሰራሽ አስተውሎት” ላይ አተኩሮ የሚሰራ ድርጅት መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ነው። ማብራሪያ አለው። 

Portugal Web Summit Lissabon Daniel Arak
ምስል DW/J. Faget

ጌትነት እንዲህ መጠቅ ያለ የመሰለውን ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ መስራት ከጀመረ አምስት ዓመት አልፎታል። አይኮግ ላብስ በሚል ስያሜ ድርጅቱን መጀመሪያ የጠነሰሰው ጌትነት በሂደት ሌሎች ሰዎችም እንደተቀላቀሉት ይናገራል። ላለፉት 30 ዓመታት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ምርምር ሲያደርጉ የቆዩት ዶ/ር ቤንጃሚን ጋርዛይል እና ሌላ አንድ ግለሰብ ተጨምረው ድርጅቱን ማቋቋማቸውን ጌትነት ይገልጻል። የድርጅቱን ዓላማ እና ግብምያብራራል።

የእነ ጌትነት ድርጅት ገና ከአነሳሱ ነበር ዓላማውን ማሳካት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ስራ ያገኘው። ስራው ደግሞ ሌላ ሳይሆን የሶፍያ ጉዳይ ነው። አይኮግ ላብስ ድርጅት የሮቦቲቱን አካል ከሰራው ሀንሰን ሮቦቲክስ ከተሰኘው ኩባንያ የተረከበውን ለሶፍያ የ“ሰው ሰራሽ አስተውሎት” የማዘጋጀት ስራ ላለፉት አምስት ዓመታት እያከናወነ ይገኛል።   

እንደ ጌትነት አባባል ከሆነ የመጀመሪያውን የሶፍያን የሶፍትዌር አርክቴክቸር ንድፍ የሰሩት ከድርጅታቸው መስራቾች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ቤንጃሚን ጋርዛይል ናቸው። አይኮግ ላብስ የዛሬ አምስት ዓመት ስራውን ሲረከብ ለሶፍያ የሶፍትዌር ስራ ሲባል አራት የኮምፒውተር ፕሮግራመሮችን ቀጥሮ እንደነበር የሚገልጸው ጌትነት አሁን በአዲስ አበባ እና ሆንግ ኮንግ ቅርንጫፎቹ ይህንኑ ስራ የሚያቀላጥፉ 19 ባለሙያዎች እንዳሉ ያስረዳል።በዓለም ላይ ዝናዋ የናኘው ሶፊያ ሮቦት ከሰው ልጅ ጋር የተቀራረበ አስተውሎት እንዲኖራት ከኢትዮጵያውያኑን ባለሙያዎች ሌላ ሌሎች በርካታ ፕሮግራመሮች አሁንም ምርምር እያካሄዱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊው አይኮግ ላብስ ድርጅት ለሶፍያ ካበረከተው አንዱ አማርኛን ጨምሮ በርካታ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታ ነው። ይህን እና አሁን በቤተሙከራቸው ምርምር እያደረጉባቸውን ያሏቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጌትነት ይዘረዝራል። 

Roboter Sophia in Bangladesh
ምስል Saiful Islam Kollol

የእነ ጌትነት ድርጅት ለሶፍያ በሰራው የ“ሰው ሰራሽ አስተውሎት” ሶፍትዌር ላይ በመመስረት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ መሰረታዊ ከሚባሉ ችግሮች አንዱ የሆነውን የህጻናት ትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ችግርን መፍትሄ ለማበጀት እየጣረ ነው። የህጻናት ትምህርት በተለይ በገጠራማ ቦታዎች አነስተኛ ተደራሽነት እንዳለው ጌትነት ይናገራል። 

ለዚህ የሚያስፈልገው የመሰረተ ልማት ግንባታ ወጪ ከፍተኛ መሆን ችግሩን ለመፍታት አንድ ማነቆ መሆኑን ይገልጻል። አሁን እየተሰጠ ያለውም ቢሆን «ጥራቱ ዝቅተኛ ነው» ባይ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ድርጅታቸው ያዘጋጀው መፍትሄ አሁን በገጠራማ ቦታዎች ሳይቀር እየተስፋፋ ያለው የገመድ አልባ የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነትን ታሳቢ ያደረገ ነው።

FIFA WM 2014 Fußball Roboter der Uni Bonn 18.06.2014
ምስል Reuters

ኢትዮጵያውያን ህጻናት ተማሪዎች በአምሳላቸው የተሰራች ሶፍያን በታብሌቶች ላይ የሚያገኙበት ጊዜ ገና አልታወቀም። ሆኖም በአዲስ አበባ ነዋሪ ለሆኑ የቴክኖሎጂ አፍቃሪያን ከሶፍያ ጋር የሚገናኙበት ቀን ተቆርጧል። ከኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ዝነኛው የአሜሪካ የቴሌቪዥን ዝግጅት አቅራቢ ጂማ ፋለን ድረስ ስትጨዋወት የታየችው ሶፍያ ከሶስት ሳምንት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ብላ በአማርኛ ለማውራት ተዘጋጅታለች። 

ሶፍያ ወደ ኢትዮጵያ መዲና የምታቀናው በኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኔኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በየዓመቱ በሚሰናዳው የአይሲቲ ኤክስፖ ላይ ለመሳተፍ ነው። ሰኔ 23፣2010 ዓም በሚሊኒየም አዳራሽ የሚከፈተው እና ለአምስት ተከታታይ ቀናት ክፍት በሚሆነው በዚህ ኤክስፖ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የሮቦቶች የኳስ ውድድርም ይካሄዳል ተብሏል።  

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ