1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን፤ እስራኤል ዩናይትድ ስቴትስ ዉዝግብ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2010

የእስራሉ መከላከያ ሚንስትር ኤይዘር ዋይዝማን አሜሪካዊ እንግዳቸዉ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በጠሩት ጋዜጣዊ ጉባኤ «ከእስራኤል የጠላቶች መዝገብ ዉስጥ አንዷ ተቀነሰች» አሉ ጥቂት አመነቱ እና ቀጠሉ፤«አንድ ግን ተጨምራለች….» ጥቂት አመነቱ እና «ኢራን» አሉ።

https://p.dw.com/p/2xKLU
Österreich Wien Atom Verhandlungen
ምስል Getty Images/AFP/J. Klamar

የኢራን፤ እስራኤል ዩናይትድ ስቴትስ ዉዝግብ


ከሚያዚያ 2015 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከዋሽግተን-ብራስልስ፤ከቴሕራን-ሞስኮ፤ ከቪየና-ኒዮርክ  የሠላም ተስፋ ሲነገር፤ የዲፕሎማሲ ድል ሲወደስ፤ የስምምነት ፅናት ሲሰበክ፤ ከየሩሳሌም-ሪያድ የጥፋት መርዶ ሲረገድ ነበር።የሞስኮ፤ ቤጂንግ፤ የቴሕራን፤ ብራስልስ ፖለቲከኞች ዛሬም እንደ አምና ሐቻምናዉ በነበሩበት ለመፅናት ቃል እየገቡ፤ ሌሎችን ያሳስባሉ።የኒዮርክ-ቪየና ዲፕሎማቶች የሰላም ዉሉ እንዲከበር ይመክራሉ።ዋሽግተኖች ግን የሪያድ፤ እየሩሳሌም ተከታዮቻቸዉን ተከትለዉ ለጦርነት ይጋበዛሉ።ቴሕራኖችም ላፀፋ ፉከራ አልሰነፉም።ከሰላም ስምምነት ወደ ጦርነት ቀረርቶ ያፍታ እመርታ።አስፈሪ ሽግግር።ዳራ ምክንያት እድምታዉን እንቃኛለን።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
                           
የእስራኤል እና የግብፅ ፖለቲከኞች በዩናይትድ ስቴትስ  አቻዎቻቸዉ ሸምጋይነት ለተከታታይ ዓመታት በድብቅ ያደረጉትን ድርድር በየመሪዎቻቸዉ ፊርማ ለማስደቀ መስከረም 1978 ሲስማሙ ኢራን ዉስጥ የሚንተከተከተዉ ሕዝባዊ ቁጣ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ለማጤን አልቻሉም ነበር።ወይም ጊዜ አልነበራቸዉም።
ችለዉም ከነበር በስምምነታቸዉ  ይሁን በየጥቅማቸዉ ላይ የሚያደርሰዉን ተፅዕኖ ለመግታት ሰወስቱም መንግስታት ዕቅድ ለ (ፕላን ቢ) የሚሉት አማራጭ አልወጠኑም ነበር።የሁለቱ ወይም ሰወስቱ የቀድሞ ጠላቶች መንግስታት እንደ ወዳጅ የሚያስተሳስራቸዉን ዉል መጋቢት 1979 በየመሪዎቻቸዉ ፊርማ ለማፀደቅ ቀን ቆርጠዉ ተለያዩ።
ጂሚ ካርተር ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሠላም ጥረታቸዉን ዉጤት ለማየት ቀን ያሰላሉ።አንዋር አሳዳት እንደ ከሐዲ የመወገዛቸዉ ንረት፤ እንደ ሠላም አርበኛ በመወደሳቸዉ ድምቀት የሚያደበዝዙበትን ብልሐት ያዉጠነጥናሉ። ሜናሔም ቤግን የቀሪ ጠላቶቻቸዉን ኃይል ይቀምራሉ።
በሰላም ተስፋ ማግስት የጦርነት እቶን የሚለበልበዉ ያ ምድር ግን አንዱን ጥሎ ሌላዉን አንጠልጥሎ የሚባለዉ ዓይነት ዉል የሚፈረምበት ዕለት እስኪደርስ በሰላም አልጠበቃቸዉም።

ጥር 16 1979። ፋርስ ላይ የነበረዉ እንዳልነበር ሆነ።አብዮት።የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች የእስራኤል እና የዩናይትድ ስቴትስን ጠንካራ ወዳጅ የንጉስ መሐመድ ሬዛ ሻሕ ፓሕላቪን ዘዉዳዊ አገዛዝ መንግለዉ የቴሕራን ቤተ መንግሥት ተቆጣጠሩ።
                                
«በመስኮቴ ሳማትር የኾሚንን ፎቶ ግራፍ የያዙ ወጣቶች በኤምባሲዉን የግንብ አጥር ላይ ሲንጠለጠሉ አየኋቸዉ።ወደ ኤምባሲዉ ቅጥር ግቢ ለመግባት እየሞከሩ ነበር።ያቀን በሕይወቴ በጣም አስደንጋጩ ዕለት ነበር።»

በኢራን የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ባሪ ሮዘን። ሻሑ ከሥልጣናቸዉ ከመወገዳቸዉ ከጥቂት ወራት በፊት ሥለፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት PLO የሰጡት አስተያየት አሜሪካዊዉ ጋዜጠኛ ጆን ኬ. ኩሌይ እንደፃፈዉ፤ የያኔዉ የእስራኤል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሞሼ ዳይን ከተናገሩት የተለየ አልነበረም።«ከሰላም ሥምምነት ላይ ለመድረስ» አሉ የኢራኑ ንጉስ፤ « የሰላማዊያኑ ፍልስጤማዉን ስደተኞች ጉዳይ  መፍትሔ ማግኘት አለበት።አሸባሪዎቹ ወይም ያሸባሪዎቹ ድርጅት ብቻ አይደለም።» አከሉ ሻሁ ጋዜጠኛዉ እንደፃፈዉ።
ብዙም አልቆየ።ሻሁ ልክ እንደ እስራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች ሁሉ አሸባሪ ያሉት  ድርጅት መሪ ያሲር አረፋት የእስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን የመጀመሪያዉ የክብር እንግዳ ሆነዉ ቴሕራንን ጎበኙ።የኢራን-እስራኤል-ዩናይትድ ስቴትስ ወዳጅነት በጠላትነት ተቀየረ።የካቲት 1979።
እስራኤል ከተመሰረተችበት ከ1948 ጀምሮ ያን ምድር ለሚያወድመዉ ግጭት ጦርነት፤ ሽብር ጥፋት መሠረታዊዉ ምክንያት የፍልስጤሞች ነፃነት አለመከበር ነዉ እያሉ የሚከራከሩ።ክርክሩ እዉነትም-ሐሰትም ሊሆን ይችላል።የፍልስጤሞች የነፃነት ጥያቄ እስካሁን መልስ አለማግኘቱ ግን ሐቅ ነዉ።
እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ «ጠላት» ከሚሏቸዉ ኃይላት ጋር ሠላም አወረድን ባሉ ወይም «ጠላት» የሚሉትን ባጠፉ ማግስት ሌላ ጠላት ማፍራታቸዉም እዉነት ነዉ።
ገማል አብድ ናስር፤ አንዋር አሳዳት፤ ሐፌዝ አል-አሰድ፤ ሳዳም ሁሴን፤ ሁሴይን አብደላሕ፤ ያሲር አረፋት፤ ኦስማ ቢን ላደን፤ ሙዓመር ቃዛፊ ብዙዎች እየመጡ ሔደዋል።ሌሎቹ ታድነዉ ተገድለዋል።

USA PK Präsident Trump über Atomabkommen mit Iran
ምስል Reuters/K. Lamarque

የቀድሞዉ ዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ሐሮልድ ብራዉን ቴልአቪቭ የገቡት የግብፅ እና የእስራኤል መሪዎች መስከረም 1978 ካምፕ ዴቪድ-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ያደረጉትን ሥምምነት መጋቢት 1979 በየመሪዎቻቸዉ ለማፅደቅ ሳምናትት ሲቀራቸዉ ነበር።የካቲት 1979።
የእስራሉ መከላከያ ሚንስትር ኤይዘር ዋይዝማን አሜሪካዊ እንግዳቸዉ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በጠሩት ጋዜጣዊ ጉባኤ «ከእስራኤል የጠላቶች መዝገብ ዉስጥ አንዷ ተቀነሰች» አሉ ጥቂት አመነቱ እና ቀጠሉ፤«አንድ ግን ተጨምራለች….» ጥቂት አመነቱ እና «ኢራን» አሉ።
ኢራን አረብ አይደለችም።ከእስራኤል ጋር አትዋሰንም።የቴሕራንን ቤተ=መንግሥት ከያዙ ሁለተኛ ወራቸዉን የያዙት የኢራን አያቶላሆች ከፕሮፓጋንዳ ልፈፋ በስተቀር የዉጪ መርሐቸዉን ገና በቅጡ አላስታወቁም ነበር።በእስራኤል አሜሪካኖች ዘንድ «ጠላት» ለመባል ግን አረፋትን ቴሕራን መጋበዛቸዉ ወይም የፍልስጤሞችን የነፃነት ጥያቄ መደገፋቸዉ በቂ ነበር።
ሚያዚያ 2015 ሎዛን ሲዊዘርላድ ዉስጥ የተፈረመዉ የኢራን የኑክሌር ጉዳይ ሥምምነት አስራ-ሁለት ዓመታት ያስቆጠረዉን የኑክሌር ዉዝግብ ማስወገዱ ምንም አያጠራጥርም።ብዙ ታዛቢዎች እንዳሉት ደግሞ ስምምነቱ ከኑክሌር ዉዝግቡ አልፎ ከ1979 ጀምሮ ሥር የሰደደዉን የኢራን እና የዩናይትድ ስቴትስ-እስራኤልን ጠብ ለማርገብ ጥሩ መደላድል ይሆናል የሚል ተስፋ የተጠላበትም ነበር።
                                 
የእስራኤል-ግብፆች ስምምነት፤ የእስራኤል ዮርዳኖስች ሥምምነት፤ የእስራኤል ፍልስጤሞች ድርድር፤ የእስራኤል ሶሪያ ድርድር፤ ያስገኘዉ ዘላቂ ሠላም እንደሌለ ሁሉ የ2015ቱ ዉል የጫረዉ ተስፋም ከተስፋ አለማለፉ ነዉ ቀቢፀ-ተስፋዉ።ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ አምስቱ ኃያላን መንግሥታት እና ጀርመን የፈረሙትን ስምምነት ፤ በተፈረመ ማግስት፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢንያሚን ኔታንያሁ «ኢራን የኑኬሌር ቦምብ እንድትሰራ የሚፈቅድ» በማለት አወገዙት 
ስምምነቱ በተፈረመ ባመቱ ሥልጣን የያዙት ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የትጭበረበረ ብለዉታል።በቀደም ደግሞ በበሰበሰ መሠረት  ላይ የተጣለ አሉት።
                            
«ይሕ በበሰበሠ መሰረት ላይ የተጣለ ዉል ነዉ።መጥፎ መዋቅር ነዉ።እየተንኮታኮተ ነዉ።ጨርሶ (መፈረም) መደረግ አልነበረበትም።ምክር ቤቱን እወቅሳለሁ፤ ብዙ ሰዎችን እወቅሳለሁ።ጨርሶ መደረግ አልነበረበትም።በ12 የሚሆ ነዉን እናያለን።»

Hassan Rouhani
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Noroozi

እስከያዝነዉ ሳምንት ማብቂያ ግንቦት 12 የስምምነቱ ፈራሚዎች ስምምነቱን ትራምፕ በሚያዙት መሠረት ካላደሱ የልዕለ ኃያሊቱ ሐገር መሪ ስምምነቱን አሽቀንጥረዉ ለመጣል እየዛቱ ነዉ።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያም ኔታንያሁ ደግሞ እስከ ግንቦት 12 አልታገሱም።ወትሮም ኢራንን ሲወነጅሉ የነበሩት ኔታንያሁ ባለፈዉ ሳምንት የኢራንን ወንጀል ያረጋግጣል ያሉትን ፎቶ ግራፍና እና ፊልም እንደ ጥሩ አስተማሪ ቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ደቅነዉ ይዘረዝሩ ያዙ።
     

ኢራን የአዉቶሚክ ጦር መሳሪያ እንዲኖራት መንገድ ከፍቷል።መንገድ የሚከፍተዉ ኢራኖች ይሕን መሳሪያ ለማምረት የሚጠቅም ሰወስት ነገሮችን ሥለሚፈቅድ ነዉ።አንደኛ በጥቂት አመታት ዉስጥ ያለገደብ ማብላላት እንዲችሉ (ይፈቅዳል)።ይሕን ሊያደርጉ አቅደዋል።ቀደም ሲል ላሳየኃችሁ የሚዉል የዩራኒየም ክምር ለማምረት  በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ማቀጣጠያ ለማምረት አቅደዋል።---ሁለተኛ፤ ስምምነቱ ኢራን አሁንም የቀጠለችዉን ተምዘግዛጊ ሚሳዬል እንዳታመርት አያግድም።ሰወስተኛ፤ ይኸኛዉ አዲስ ነዉ።የኢራንን ድብቅ የኑክሌር ቦምብ መርሐ-ግብር (ስምምነቱ) አይመለከትም።» 
የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር የሚቆጣጠረዉ ዓለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት IAEA የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዉንጀላን ማረጋገጥም፤ መካድም አልፈለገም።ይሁንና አንድ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ባለፈዉ ሳምንት እንዳስታወቁት ድርጅታቸዉ የሚያዉቀዉ ኢራን ከ2009 ጀምሮ የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ማቋረጥዋን ነዉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አቶኒዮ ጉተሩሽ እንዳሉት ኢራን ከእስራኤል፤ከዩናይትድ ስቴትስ፤ ከሳዑዲ አረቢያ ጋርም የቆየ ጠብ አላት።ይህን ጠብ ለማስወገድ ሌላ ድርድር እና ዉይይት ማድረግ ጠቃሚ ነዉ።የቆየዉን ጠብ ለማስወገድ ከመጣር ይልቅ የተፈረመ ዉል ማፍረስ ግን አስጊ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል።
                                      
«አደገኛ ጊዜ ዉስጥ ነን።ባንድ በኩል በየስፍራዉ፤ ሶሪያ፤የመን፤ሊቢያም ሆነ ሌላ ስፍራ ያሉ ቀዉሶችን ለመፍታት መጣር አለብን።ለእነዚሕ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ አለብን።በሌላ በኩል በተለያዩ ኃይላት መካከል ከቁጥጥር ዉጪ የሆነ ጠብ ሊያጭሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስወገድ ድርድር የሚደረግበት ሥልት መኖር አለበት።እንደሚመስለኝ ይሕ ስምምነት ጥሩ ዉጤት ነዉ።አንድ ቀን ይሕን ስምምነት የሚተካ የተሻለ ሥምምነት ከተደረገ እሰዬዉ።ጥሩ አማራጭ ከሌለን ግን መሰረዝ የለብንም።»
የቤጂንግ፤ የሞስኮ፤ የፓሪስ፤የበርሊን፤ የለንደን፤የብራስልስ መሪዎችም ስምምነቱ ይፍረስ የሚለዉን የትራምፕ-ኔታንያሁን ሐሳብ አልተቀበሉትም።ዶናልድ ትራምፕ ግን  የዲፕሎማቶችን ምክር፤ የሐገራቸዉን ሸሪኮች አስተያየትም ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም።ኢራንን እንደ ሰርቢያ፤ እንደ አፍቃኒስታን እንደ ኢራቅ ወይም እንደ ሊቢያ ሊያጠፉ እየፎከሩ ነዉ።
                              
«ኢራን በየትኛዉም መንገድ እኛን ካሰጋችን፤ ከዚሕ ቀደም ጥቂት ሐገራት ብቻ የከፈሉትን ዓፕነት ዋጋ ይከፍላሉ።»
ኢራኖችም ዛቻ-ፉከራዉን ያዥጎደጉዱት ይዘዋል። ልዕለ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ሐሚኒ «እንተያያለን» አሉ። 
                                 
«ይሕን ያዉቁታል።ከኛ ጋር ግልፅ ወታደራዊ ዉጊያ ከገጠሙ መዉጪያ አይኖራቸዉም።አዎ ይመቱናል።ግን በጣም የከፋ ዱላ ያርፍባቸዋል።አሜሪካኖች እና ብጤዎቻቸዉ ከዚሕ አካባቢ ለመዉጣት ይገደዳሉ።»
ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሐኒ በፋንታቸዉ  ኢራን የሚበቃትን ያክል ጦር መሳሪያ ብትታጠቅ የሚያገባዉ የለም ባይ ናቸዉ።
«ለመላዉ ዓለም ለአዉሮጳ፤ለአሜሪካ፤ ለምዕራቡም ለምስራቁም የምንናገረዉ ሐገራችን በምትታጠቀዉ መሳሪያ እና በመከላከያ (ኃይሏ) ላይ አንደራደርም።ሐገራችን የሚያስፈልጋትን የጦር መሳሪያ፤ሌሎች ቁሳቁሶች እና ሚሳዬሎች እንገነባለን።እናከማቻለንም።»

Tel Aviv Netanjahu PK Iran Atomprogramm (picture alliance / Photoshot)
ምስል picture-alliance/Photoshot

በሶሪያዉ ጦርነት በኢራን እና በሩሲያ የሚደገፈዉ የፕሬዝደንት በሽር አልአሰድ መንግሥት አማፂያንን ተራ በተራ እየደፈለቀ ነዉ።በየመኑ ጦርነት በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን ሁቲዎች ለማጥፋት የዘመተዉ የሳዑዲ አረቢያ እና የተባባሪዎችዋ ጦር በደም እየዋኘ ነዉ።በሊባኖሱ የምክር ቤት ምርጫ የኢራን ቀኝ እጅ የሚባለዉ ሒዝቡላሕ እና ተባባሪዎቹ አብላጫዉን መቀመጫ አሸንፈዋል።በዚሕ መሐል ትራምፕ ኔታንያዉ፤ ኻሚኒ-ሩሐኒ የፎከሩትን ያደርጉት ይሆን?ነጋሽ መሐመድ ነኝ።ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ