1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰሞኑ፦ የሻሸመኔ ግድያ፣ ዘመቻ ለሃጃጆች

ዓርብ፣ ነሐሴ 11 2010

ባለፈው እሁድ በሻሸመኔ ከተማ ቢያንስ አራት ሰዎች የሞቱበት መርኃ ግብር በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለቀናት መወያያ ሆኖ ቆይቷል። ዓመታዊ ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ለማከናወን ወደ ሳዑዲ አረቢያ በሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ የደረሰው እንግልትም ሌላው የሳምንቱ መነጋገሪያ ነበር።

https://p.dw.com/p/33KRO
Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

ከሰሞኑ፦ የሻሸመኔ ግድያ፣ ዘመቻ ለሃጃጆች

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ. ኤም. ኤን) ቴሌቭዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሐመድ በየጊዜው ውዝግብ አያጣቸውም። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ወዲህ እንኳ ከሚናገሯቸው እና ተሳትፎ ከሚያደርጉባቸው ክንውኖች ጋር ተያይዞ ስማቸው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲነሳ ሲጣል ነው የሰነበተው። ባለፈው እሁድ ነሐሴ 6 እርሳቸውን ለመቀበል በሻሸመኔ በተሰናዳ መርኃ ግብር ላይ የተፈጸመው ግድያ ቁጣ እና ውግዘትን ቀስቅሷል። እርሳቸው የተሳተፉበት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተደረገ የውይይት መድረክን፤ የሚመሩት ኦ. ኤም. ኤን ጣቢያ የዘገበበት ሁኔታ አነታርኳል። ናሁ ከተሰኘ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ያነሷቸው ነጥቦችም አወዛግበዋል። 

በሳምንቱ ውስጥ ከሌሎች ጉዳዮች የላቀ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው በሻሸመኔ በአንድ ወጣት ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ግድያውን በኢትዮጵያ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ ከመጣው የደቦ ፍትህ (mob justice) ጋር አያይዘው ክፉኛ የተቹት አሉ። ሌሎች ደግሞ የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮዎች) “ከጸጥታ አስከባሪዎች አቅም በላይ እየሆኑ መጥተዋል” የሚል ስጋታቸውን አጋርተዋል። 

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ምስጋናው ሙሉጌታ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “የሆነው አንገት ያስደፋል” በሚል ርዕስ ባለፈው ሰኞ ባስነበቡት ጽሁፋቸው ብዙዎች ያነሱትን ሀሳብ አንጸባርቀዋል። “መቃወምም፣ መደገፍም፣ መተጋገልም ገደብ አለው። ፓለቲካችን ለከት አጥቶ ሰው መሆናችንን ካጠፋው ምን ላይ ቆመን ነው የምንሸጋገረው? ጭራሽ በሀይማኖትና በባህል የተገነባ፣ ድህነትና ረሀብ እንኳን ያላረከሰው ሰብዓዊነታችን እየተሸረሸረ የነበረንንም እሴት እያጣን ነው። ከተፈጸመውና እየተፈጸመ ካለው ሰቅጣጭ ተግባር ይልቅ ትርጓሜው፣ የፓለቲካ ትርፉና ኪሳራው ካሳሰበን ነገራችን የሞራል መለኪያውን አጥቷል። ሰው በዚህ ደረጃ ሲወርድ፣ ስሜታዊነት ሲጀግን፣ የሴራ ፓለቲካ ሲገን ግፍ ይለመዳል። የዛኔ ፍትህ፣ ዲሞክራሲና ሰላም ዋስትናቸውን ያጣሉ። አንዲት ንፁህ ነብስ የማታንገበግበው ትግል ደግሞ ዘላቂ ውጤት አይኖረውም። ከምንም ነገር በፊት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ይሄ ደግሞ ከማንም በላይ የመንግስት ሀላፊነት ነው።”

በሻሸመኔ ለተፈጠረው አሳዛኝ ሁነት ከመንግስት ባሻገር ቄሮዎችም “ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው” የሚሉ አስተያየቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተንሸራሽረዋል። ፌር ናዝ በሚል ስም ፌስ ቡክ የሚጠቀሙ ግለሰብ “ቄሮ ያፋፋመው ህዝባዊ ማዕበል ለተፈጠረው የስርዓት ለውጥ የጎላ ሚና እንደነበረውና በዚህም በህዝቡ ዘንድ ሸጋ ነጥቦችን መሠብሠቡ እሙን ነው፡፡ ሰሞነኛው የሻሸመኔ ተግባሩ ግን ምንም እንኳን መላ ቄሮዎችን የሚወክል ባይሆንም ቄሮ በገዛ ሜዳው አንድ ነጥብ እንዲጥል አስገድዶታል፡፡ ምናልባትም ቄሮ ተጠርጣሪውን ለፍትህ አካላት አሳልፎ መስጠት ቢችል ኖሮ ከመብጠልጠል ይልቅ ተጨማሪ ነጥብ አስቆጥሮ ሙገሣን በተጎናፀፈ ነበር፡፡ እናም ቄሮ የጣለውን ነጥብ ለመመለስ የድርጊቱን ፈፃሚዎች ከማጋለጥ ባለፈ ይፋዊ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

ፊሊሞና መንግስቱ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው “የዓብይንስ መንግስት አድራሻውን ስለምናቀው ለማም ጠፋም የምንጠይቅበት መንገድ አናጣም። ይህን የቄሮ መንግስት የት አግኝተን አቤት እንበለው? የለም እንዳንል አለ ተባልን። ‘አረ ቄሮ ተው’ ስንልም ‘ቄሮ ማለት እኮ’ ተብሎ ማብራሪያ ይሰጠናል” ሲሉ በቄሮ ደጋፊዎች እና ተቺዎች መካከል ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የነበረውን ምልልስ ታዝበዋል። ማዲ ዮናስ በዚያው በትዊተር “ ‘ጫካ ገብቼ ፣ ደሜን አፍስሼ ነፃ አወጣሁህ’ የተሰኘው ጸጥ የማስባያ ስልት ‘ጎዳና ወጥቼ ፣ መስዋእትነት ከፍዬ ነፃ አወጣሁህ’ በሚለው በሚገባ ተተክቷል።  እንደአምናው ባለቀን ‘ ዝም በል!’ ማለት ካመጣ አዲስ ነፃ-አውጪ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?” ሲሉ የቴዲ አፍሮ ዘፈንን በሚያስታውስ መልኩ ጠይቀዋል።

ዮናስ ፓፒ በፌስ ቡክ ገጹ  ከወጣቶች ጋር በተያያዘ መፍትሄ ነው ያለውን አስነብቧል። “አሁን ለመጣው ተስፋ ሰጪ ለውጥ ከሰፊው ህዝብ በመቀጠል የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የየክልሉ ወጣቶች” መሆኑን የሚጠቅሰው ዮናስ “ለቀጣይ የሃገሪቱ ህልውና፣ ሰላም እና አብሮነት ወጣቶች ቁልፍ” ተዋናዮች መሆናቸውንም ያነሳል። “የቄሮ፣ የፋኖ፣ የዘርማ እና የሌሎች ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ የክልል ወጣቶች ስብስቦች በፌዴራል መንግስቱ አስተባባሪነት በቂ የመወያያ፣ የመግባቢያ እና ችግሮችን በዘላቂነት የመፍቻ መድረኮች ቢዘጋጁላቸው አሁን የምናየውን ስርዓት አልበኝነት፣ ሞት፣ ስደትና መፈናቀል፣ እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከመሰረቱ ለመፍታት በቀጣይም እንዳይከሰቱና ተጋግዞ ሁሉም የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ እና እንዲያለማ ይረዳል” ሲል ጥቆማውን ሰጥቷል። 

Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ የሻሸመኔው ዓይነት ድርጊቶች የስርዓቱ ደጋፊዎች የሚባሉትንም ጭምር ያሳሰቡ ይመስላሉ። ኦህዴድን በመደገፍ የሚታወቁት ደረጀ ገረፋ ቱሉ “ስርዓት አልበኝነት የወቅቱ ፈተና ነው። ይህንን በጊዜ መቀልበስ ካልቻልን ወደ ነበርንበት አዙሪት መመለሳችን አይቀሬ ነው” ሲሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው መጻፋቸው ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። ሰላም አባቦራ በዚያው በፌስቡክ “በየቦታው ስርዓት አልበኝነት ነግሷል፡፡ የደቦ ፍትህ (mob justice) ይቺን ሀገር ወደ ማትወጣበት አዘቅት ዉስጥ ሊከታት ይችላል፡፡ በምንም ጉዳይ ላይ ብንለያይ በእንደዚህ አይነት የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥል ጉዳይ ላይ አንድ አቋም ሊኖረን ይገባል” ብለዋል።  

በድሉ ሌሊሳ የተሰኙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በየአካባቢው ለሚታዩ ግጭቶች በግልጽ ያልጠቀሷቸውን አካላት ተጠያቂ ያደርጋሉ። “ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በአፈ- ሙዝ ታፍኖ ሲተዳደር የነበረ ሀገር ለቀቅ የሚያደርግ መንግስት ሲፈጠር ግጭቶች መከሰታቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ከተመሳሳይ ስህተቶች አለመማራችን ያስቆጫል። ከግጭቱ ጀርባ የተኮለኮሉ አካላት ግብ ህዝቡ በለውጡ ተስፋ እንዲቆርጥ ለማድረግ እንደሚሆን እንገምታለን” ሲሉ ጽፈዋል። ከወራት በፊት ከእስር የተለቀቀው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እነዚህን አካላት “ተስፋ የቆረጡ ፈርጣጮች” ሲል ይጠራቸዋል። ውብሸት በሰሞነኛ ሁነቶች ላይ ሀሳቡን ባከፈለበት የፌስ ቡክ አስተያየቱ በኢትዮጵያ “ስኬትና ክሽፈት እየተፋለሙ ነው” ብሏል።  

“በቅርብ ጊዜያት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን፣ መፈናቀሎችን እና የወገኖቻችንን ሰቆቃ እየተመለከትን ነው። ስኬትና ክሽፈት እየተፋለሙ ነው። ማን ያሸንፍ ይሆን?ይህ ጥያቄ ብዙዎቻችንን እንደሚያስጨንቀን አያጠራጥርም። እንድንጨነቅ፣ ተስፋችንን በጥርጣሬ እንድናዳምን እና በተቃወሰ የነግ እይታ፣ በልጆቻችንን የደም ዋጋ የጨበጥነውን ሳናስበው እንድንጥል፣ ከቀን ከሌሊት  የሚሰሩ እንዳሉም በገሃድ እየታዘብን ነው። የአቀበት ሸሺዎች ጥቃት የሆነው፤ ናዳ እየለቀቁ ማፈግፈግ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየወረደ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ተስፋ የቆረጡ ፈርጣጮች አሁን እያጋጠመን እንዳለው ብዙ የናዳ ጉዳት ያደርሳሉ። የማሕበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች እንደሚነግሩን ግን በፍጹም አያሸንፉም። ድርጊታቸው ዘመኑን የዋጀ አይደለም። የዛሬይቷን ቀን በትግሉ የፈጠራትን የኢትዮጵያን ሕዝብ ገና በወጉ አላወቁትም። ማን ወደኋላ መመለስ ይፈልጋል? ሰቆቃው በቅርቡ ያልፋል። ይህች ምንም ቢሆን ኢትዮጵያ ናት! ያንን ያለመርሳት ተገቢ ነው።” 

ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ ተሻግረናል። የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑ ኢትዮጵያውያን የሃጅ ተጓዦች ላይ የደረሰ እንግልት ሌላው የዚህ ሳምንት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ አጀንዳ ነበር። አቅሙ የፈቀደ እና ጤናው የተሟላ ሙስሊም ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት አንዱ የሆነውን የሃጅ ጉዞ በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ የማድረግ ግዴታ አለበት። ይህን ሃይማኖታዊ ግዴታ ለመወጣት በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ቢጓዙም በጉዞው አስተባባሪዎች ምክንያት ተደጋጋሚ እንግልት እንደሚደርስባቸው ሲነገር ቆይቷል።

ለሃጅ ተጓዦች (ሃጃጆች) የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አየር መንገዶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተመሳሳይ ወቀሳ ሲቀርብበት ቢቆይም የዘንድሮው ግን ገፍቶ በተቋሙ ላይ በትዊተር ዘመቻ እስከማካሄድ ደርሷል። የዘመቻው ሀሳብ የተወለደው የእዚህ ዓመት የሃጅ ተጓዦች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ እየተንገላቱ መሆኑን የሚሳዩ በምስል እና ቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ከተሰራጩ በኋላ ነበር። ከዘመቻው አስተባባሪዎች አንዷ የሆነችው ሙኒራ አብዱልመናን ዓላማውን እና አየር መንገዱ የሰጠውን ምላሽ ለዶይቼ ቬለ አብራርታለች። 

“የትዊተር ዘመቻው ዓላማችን የነበረው ሁለት ነገሮችን ነው። የመጀመሪያው አየር መንገዱ ላጉላላቸው የህብረተሰብ አካላት፣ ለደረሰው እንግልት እና ጥፋት ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚል ነው። አየር መንገዱ ተቃውሟችንን ፌስ ቡክ ላይ ባሰማን እና የትዊተር ዘመቻ እንደሚኖረን ባስተዋወቅን ጊዜ ምላሽ ሰጥቶ ነበረ። የመጀመሪያው ምላሽ በእንግሊዘኛ የተጻፈ ነበር። የመልዕክቱ ወጥ ትርጉም አንደኛ ይሄ እንግልት የተፈጠረው የሃጅ ኮሚቴው ከተስማማነው ቁጥር በላይ የሆኑ ሃጃጆች (የሃጅ ተጓዦች) ስለላከብን ነው ይላል። ሁለተኛው በጸጥታ ምክንያት ከጅጅጋ ዘግይተው የመጡ ስለነበሩ ነው ይላል። እንደውም የዜግነት ግዴታችን ነው ብለን ግዴታችን ከሆነው በላይ ሰዎቹን ግልጋሎት ሰጥተናቸዋል የሚል ነበር። 

ከአየር መንገዱ የሚወጡ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ግን እንደዚያ አልነበሩም። በጣም ትልልቅ ሰዎች፣ እናቶች እና አባቶች የአየር ማረፊያው ወለል ላይ ተኝተው ነበረ የምናየው። ከዚያ በኋላም በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞችን ስልክ ደውለን ለማናገር ስንሞክር በጣም ተከታታይ የሆኑ የበረራ መሰረዞች ነበሩ። ምግብ የሚባል ነገር አልቀረበላቸውም፤ ማረፊያ አልተሰጣቸውም። የአቬዬሽን ህግ ደግሞ በአየር መንገዱ ምክንያት በረራዎች ሲሰረዙ እና ሲራዘሙ ለተጓዦች እነዚህን ግልጋሎቶች መስጠት ግዴታ ነው ይላል።

ስለዚህ አየር መንገዱ መንገደኞቹ እርሱ terminal ውስጥ ባሉበት ሰዓት በሙሉ ለተከሰተው እንግልት ተጠያቂ አየር መንገድ ብቻ ነው። ግልጽ የሆነ ይቅርታ እንዲጠይቅ እንፈልጋለን። የእገሌ ነው እያለ ሰበብ መደርደር እና ምክንያቶችን እንዲጽፍ ሳይሆን የምንፈልገው ይቅርታ እንዲጠይቅ ነው። ይቅርታ እንዲጠየቅ የምንፈልገው ለምንድነው የተፈጠረው ችግር እና እንግልት ችግር መሆኑን ካመኑበት ችግሩን ማመን የመፍትሄው ግማሽ አካል ነው አይደል? ስለዚህ ለሌላ ጊዜ ላለመደገሙ ግማሽ ማረጋገጫ ይሆነናል ማለት ነው።  የዘመቻው ሁለተኛ ዓላማ የነበረው ደግሞ ይህ ነገር ሲከሰት የመጀመሪያው አይደለም። ላለፉት በጣም ብዙ ዓመታት የዚህ ዓይነት እንግልቶች አሉ። የዘንድሮው ሃጃጆች ሲመለሱም ሆነ ከዚህ በኋላ የሃጅ ጉዞ ላይ እንደዚህ ዓይነት ዝርክርክ አሰራሮች እንደማይደገሙ ማረጋገጫ እንፈልጋለን” ስትል ዘመቻው የተካሄደባቸው ምክንያቶችን አስረድታለች።

Boeing 787 Ethiopian Airlines
ምስል Reuters

“በአየር መንገዳችን አፍረናል” በሚል ሃሽታግ ረቡዕ ዕለት በተካሄደው የትዊተር ዘመቻ ከተሳተፉት ውስጥ ኤዶም ብርሃኔ “ቅድሚያ ዜጋ መከበር አለበት። መጀመሪያ ለኢትዮጵያውያን ኩራት ሳይሆን ለአፍሪካ ኩራት?! ቀልድ ነው” ስትል አየር መንገዱ ራሱን ለማስተዋወቅ የሚጠቅበትን መገለጫ ጠቅሳ ድርጊቱን ተችታለች። ሃበሽ የሚል የትዊተር ስም ያላቸው ዳጊ ዳጉም “ዜጎችን የማያከብር አየር መንገድ ኩራታችን ሊሆን አይችልም! አዛውንቶችን እና ሴቶችን ሜዳ ላይ ማሳደር ኢሰብዓዊነት ነው” ሲሉ እንግልቱን ኮንነዋል። 

ልጅ ኡስማን የተሰኙ የትዊተር ተጠቃሚ “ሙስሊሞች ወይም ሀጃጆች ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ገንዘባቸውን ከፍለው የሚጓዙ ደንበኞች ስለሆኑ ሊከበሩ እና ጥሩ መስተንግዶ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል። ትግስት ኤም በዚያው በትዊተር “መቼ ይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያውያን ደንበኞቹ አክብሮት እና እንክብካቤ ሚኖረው? ሌላው ይቅር በስልክ እንኳን ጥሩ አገልግሎት የምታገኘው በሌላ ሃገር ቋንቋ ስታናግራቸው ነው” ትዝብቷን አስፍራለች።

አበበ ብርሃኑ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ግን “በሀገሪቱ ብቸኛ በአግባቡ ስራውን የሚያከናውን ተቋም” ባሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ዘመቻ መከፈቱ አልተዋጠላቸውም። “ጦርነት እና አስቸጋሪ የገብያ ፉክክርን ተቋቁሞ ከ 70 ዓመት በላይ ምልክታችን ሆኖ መቀጠል የቻለ አየር መንገድን መደገፍ ካልቻልን ይሄ በሽታ ነው። ችግርም ቢኖረው የራሳችን በሆነ ነገር ላይ እንዲህ ለማጥፋት መሯሯጡ አያዋጣንም” ሲሉ የትዊተር ዘመቻውን ተችተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትዊተር ዘመቻው መጠናቀቅ አንድ ቀን በኋላ በአማርኛ ባወጣው መግለጫ “በበረራዎች መዘግየት” ተፈጠረ ላለው “መጉላላት”  የሀጅ ተጓዦች እና ሌሎች መንገደኞችን ይቅርታ ጠይቋል። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ