1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከዳዳብ መመለስ የጀመሩት የሶማልያ ስደተኞች

ዓርብ፣ ሐምሌ 22 2008

በኬንያ የሚገኘዉ በዓለም ግዙፉ የስደተኞች መጠለያ ዳዳብ ወደ 320 ሺህ ስደተኞችን ይዞአል። ለብዙ አሰርተ ዓመታት በሶማልያ የቀጠለዉን ጦርነትና ግጭት የሸሹ ዜጎች በመጠለያ ጣቢያዉ ይኖራሉ። የኬንያ መንግሥት የዳዳብ ስደተኞች ጣቢያ ለሀገሩ የደህንነት ሥጋት ደቅኖዋል፣

https://p.dw.com/p/1JXMi
Kenia Das Flüchtlingslager Dadaab
ምስል imago/Xinhua

በሃገሪቱ የሚጣሉ ጥቃቶችን ማቀጃ ቦታም ሆኖዋል በሚል እስከ መጭዉ ሕዳር ወር መጨረሻ እንደሚዘጋ አስታውቋል። ይህን ተከትሎ በመጠለያ ጣቢያዉ የሚኖሩ ሶማልያዉያን በመጠለያዉ ከመቆየት ይልቅ ወደ ሃገራቸዉ መመለስን መርጠዋል።
ከሶማልያ ጦርነት ግጭትን ሸሽተው በዳዳብ የስደተኞች ካምፕ ይኖሩ የነበሩ ሶማልያዉያን በፈቃደኝነት ተመልሰዉ «አዴን አዴ» በተባለዉ የመቃዲሾዉ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ ባለፈዉ ማክሰኞች ዕለት ደርሰዋል። ከተመላሾቹ መካከል ቤተሰቦች ሕጻናት ይገኙበታል። በአዉሮፕላን ማረፊያው እንደደረሱ ከሃገሪቱ የሕክምና ርዳታ አገልግሎት የሚሰጠዉን የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ለመቀበል በፀጥታ ቁጭ ብለዉ ይጠባበቃሉ።
ከዳዳብ የተመለሱትን ሶማልያዉያን ከአዉሮፕላን ማረፊያው በሦስት አዉቶቡስ አሳፍረዉ በከተማ ወዳሉት ሁለት የመጀመሪያ ርዳታ ማግኛ ማዕከል ለማድረስ እና ለመርዳት የተመደቡት ሰራተኞች በቁጥር ከአስር አይበልጡም። ተመላሾቹ ሶማልያዉያን በመቃዲሾ በተዘጋጀላቸዉ ጊዜያዊ የመጠለያ ማዕከል ምግብና የሕክምና አገልግሎትን የሚያገኙት ለጥቂት(2) ቀናት ብቻ ነዉ። አርዶ ሞሃመድ አብዱሌ ከ12 ዓመታት ስደት በኋላ ከዳዳብ ወደ መቃዲሾ የተመለሱት ከአምስት ልጆቻቸዉ ጋር ነዉ።

« ወደተወለድኩበት ሃገሬ በመመለሴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከልጆቼ ጋር የምኖርበትን የስደተኞች ካምፕ እንድንለቅ ትዕዛዝ ደርሶኝ ነዉ የተመለስኩት። በሃገራችን ከማኅበረሰባችን ጋር እንዋሃዳለን የሚል ተስፋ አለኝ። በመቃዲሾ ዘመዶች አሉን፤ በከተማዋ ዉስጥ ግን ምንም መኖርያ ቤትም ሆነ መሬት የለንም። ሕይወታችን ለመምራት ግን ጥረት እናደርጋለን። መንግሥታችን ከማኅበረሰባችን ጋር ዳግም እንድንገናን እንዲረዳን እንጠይቃለን።»
የሶማልያ መንግሥት በሚቀጥለዉ ወር ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ በመሆኑ ከስደት የተመለሱትን ዜጎቹን መልሶ የማስፈሩ ስራ ችላ የተባለ ይመስላል። ተመላሽ ስደተኞች ለመቀበል ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ የመጣ አንድ የመንግሥት ባለስልጣን እንኳ አልነበረም። ያካባቢ አስተዳደሮች ደንታ ቢስነት ተመላሾችን የወደፊቱን እድላቸውን በተመለከተ ስጋት እንዲያድርባቸው ማድረጉን የሶማልያ ዜና ምንጮች ገልጸዋል። ስጋት ካደረባቸው መካከል ተመላሽ መራመድ የማይችለዉ የአራት ዓመት ህመምተኛ ልጅ እናት ሃዎ አብዲ ሞሃመድ አንዷ ናቸው።

Afrika Kenya Dagahaley Camp
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Blackwell
Kenia Das Flüchtlingslager Dadaab
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba


« ወደ ትዉልድ ሃገሬ በመመለሴ ደስተኛ ነኝ። ቢሆንም የሶማልያ መንግስት በቅጡ ስላልተቀበለን በቀጣይ ምን ይገጥመኛል በሚል ሰግቻለሁ። በዳዳብ የስደተኛ ጣብያዉን እንድንለቅ ስለተጠይቅን ነዉ ንዑሱን ተስፋ በመሰነቅ የመጣነዉ። አሁን ኑሮዬን በሃገሬ አንድ ብዬ መጀመር እፈልጋለሁ። የስደተኛ መጠለያ ጣብያዉን በመልቀቄ በጣም ደስተኛ ነኝ።»
የኬንያ መንግሥት ዳዳብን እዘጋለሁ ብሎ ካሳወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ የሶማልያ ስደተኞች ወደ ሃገራቸዉ ተመልሰዋል። አንድ ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቁ ከፍተኛ የርዳታ አስተባባሪ እንደገለፁት በየሳምንቱ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ስደተኞችን ያሳፈረ አዉሮፕላን መቃዲሾ ይደርሳል።
ከዳዳብ የስደተኛ መጠለያ ጣብያ ለተመለሱ ሶማልያዉያን ለሦስት ወራት የሚሆን የምግብ እርዳታና ሕይወትን ለመመስረት የሚረዳና ለመጀመርያ ጊዜያት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ያገኛሉ። ከሰባት ሰዎች በላይ የያዘ አንድ ቤተሰብ ደግሞ ከዚሁ ከርዳታ ድርጅት 600 ዶላር ያገኛል። ተመላሾች ግን በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የሶማልያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ሞሃመድ ሼክ ሞሃመድ የሶማልያ መንግሥት ተመላሽ የሶማልያ ስደተኞችን ለመቀበል አልተዘጋጀም ሲል ይወቅሳሉ። « ወደ ሶማልያ የሚመለሱት ዜጎች ቁጥር መጀመርያ ይመለሳሉ ተብሎ ከታሰበዉ እጅግ ከፍተኛ ነዉ። በዚህም የተነሳ ስደተኞቹ እያጋጠማቸዉ ያለዉ መጥፎ ሁኔታ ነዉ።»

ሞሃመድ ኦዶዋ / አዜብ ታደሰ


አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ