1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ምርጫ

ማክሰኞ፣ መስከረም 2 2010

በዚህ ምርጫ የጀርመናውያንን ትኩረት የሚስቡት ማህበራዊ ፍትህ፣ ፀጥታ፣ የተመጣጠነ ደሞዝ እና የመሳሰሉት ብሔራዊ ጉዳዮች ናቸው ሆኖም የጀርመን ፓርቲዎች ሥልጣን ቢይዙ የሚከተሉትን መርህ ባካተተው ማኒፌስቶአቸው ውስጥ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ አፍሪቃን አካተዋል።

https://p.dw.com/p/2jpUY
Deutschland | Bundestagswahl 2017 | Wahlplakat CDU
ምስል picture-alliance/R. Goldmann

ከጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ምን ይጠበቃል?

መስከረም 14፣2010 ዓም በሚካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የሚካፈሉ ፓርቲዎች  የምርጫ ዘመቻ ላይ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የምርጫ አጀንዳዎቻቸውን እና ከሌሎቹ እንሻላለን የሚሉባቸውን እቅዶቻቸውን እያስታወዋቁ ነው። ምርጫውን ማን እንደሚያሸንፍ ከወዲሁ ለመናገር አስቸጋሪ ቢመስልም ብዙዎች በእድሜ ትንሹ «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ በጀርመን ምክር ቤት ውስጥ መግባት የሚያስችል ድምፅ ሊያገኝ ይችላል የሚል ግምት አላቸው። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ምርጫውን የሚወስኑ ጉዳዮችን እና ከምርጫው የሚጠበቀውን እንቃኛለን። 

በዛሬ 12 ቀኑ የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የሚካፈሉት 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻቸውን አጧጡፈዋል። እነዚሁ ፓርቲዎች በጀርመን የምርጫ ህግ መሠረት 5 በመቶ የመራጭ ድምጽ እና ከዚያም በላይ አግኝተው በጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ ለመያዝ የሚካሂዱት ፉክክር አሁን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ይገኛል። ውጤቱም በጉጉት እየተጠበቀ ነው። ከዛሬ አራት ዓመቱ ምርጫ በተለየ ዘንድሮ «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ የጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ ሊገባ ይችላል  ተብሎ እየተባለ ነው ። የመስከረም 14፣2010 ዓም ምህረቱን ምርጫ ይወስናሉ ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱም ይህ ፓርቲ የሚያገኘው ድምጽ ነው። የፖለቲካ ሳይንስ እና የህግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ከዚህ ጋር ምርጫውን የሚወስኑ ሌሎችም ጉዳዮች እንዳሉ ያስረዳሉ።  

Deutschland Wahlkampf CDU- Merkel in Bitterfeld
ምስል DW/K.-A. Scholz

በዚህ ምርጫ የጀርመናውያንን ትኩረት የሚስቡት ማህበራዊ ፍትህን ፀጥታን የተመጣጠነ ደሞዝ እና የመሳሰሉት ብሔራዊ ጉዳዮች  ናቸው ሆኖም የጀርመን ፓርቲዎች ሥልጣን ቢይዙ የሚከተሉትን መርህ ባካተተው ማኒፌስቶአቸው ውስጥ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ አፍሪቃን አካተዋል። ይህ የሆነውም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ ጀርመን ስደተኞች በብዛት መግባታቸው ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ በመዝለቁ ምክንያት ነው። ከጥቂት ወራት በፊት ጀርመን ውስጥ በተካሄደው የቡድን ሀያ አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው አድርገዋል። ሦስት የጀርመን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ለዚሁ ዓላማ ይረዳሉ ያሏቸውን የልማት እገዛዎች አቅርበዋል። ከዚህ በመነሳትም ዋና ዋና የሚባሉ የጀርመን ፓርቲዎች ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚደረግ ስደትን ለመግታት ለክፍለ ዓለሙ ድጋፍ መስጠት ይረዳል የሚል አቋም ይዘዋል።አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ የአፍሪቃ ጉዳዮች ቡድን ሊቀመንበር አንድሪያስ ሌሜል ችግሩን ለመፍታት የጀርመን ባለሀብቶች በአፍሪቃ ተጨማሪ ውረታዎች ማካሄዳቸው ጠቃሚ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

Deutschland - Live-Fünfkampf der kleinen Parteien in der ARD
ምስል picture-alliance/B. v. Jutrczenka

«በኔ አመለካከት የድህነት ችግር ፣ካለ ተጨማሪ የግል ውረታ ሊወገድ አይችልም። ይህንንም ችግር  መንግሥት ሊፈታው አይችልም። ለብዙ ዓመታት የልማት እርዳታ ስንሰጥ ቆይተናል። ይሁንና ያስገኘው ውጤት እንደታሰበው አይደለም። በኔ የግል እምነት በአፍሪቃ ተጨማሪ የግል ውረታዎች መካሄድ አለባቸው።  ይሁንና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ለዚህ ዓላማ ከአምባገንን የአፍሪቃ መንግሥታት ጋር መሰራት የለብንም ሲሉ  እየተቃወሙ እና እየተቹ  ነው። ዶክተር ለማ ይፍራሸዋም ይህን እቅድ ከሚተቹት አንዱ ናቸው። ድምጽ

AfD Parteitag in Rendsburg
ምስል picture-alliance/dpa/M. Scholz

በአሁኑ ጊዜ የሚያነጋግረው እና የሚያሳስበው የቀኝ ጽንፈኛው የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ሆኗል። በዛሬ አራት ዓመቱ ምርጫ 4.7በመቶ ድምጽ አግኝቶ ፓርላማ ሳይገባ የቀረው ይኽው ፓርቲ በአሁኑ ምርጫ ከ10 በመቶ በላይ ድምጽ ሊያሸንፍ ይችላል እየተባለ ነው። ዶክተር ለማ ምክንያቱን እና የርሳቸውንም ግምት አብራርተዋል።

በጀርመን የምርጫ ህግ አንድ መራጭ ሁለት ድምጾች አሉት። አንዱ ለእጩ ተወዳዳሪ በቀጥታ የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለፓርቲ የሚሰጥ ድምጽ ነው። አሸናፊው መስከረም 14 2010 ነው የሚለየው  ። ይሁን እና «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ በዚህ ምርጫ የሚያገኘው ድምጽ  እስካሁን የቆየውን የጀርመን የፖለቲካ ስርዓት ሊቀይረው ይችላል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ