1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጠ/ሚ ዐቢይ የጉብኝት መድረክ ጀርባ የነበሩ ውዝግቦች

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2011

ባለፈው ጥቅምት 21፤ 2011 ዓ.ም ከተካሄደው የጠ/ሚ ዐቢይ የፍራንክፈርቱ ሕዝባዊ ውይይት መድረክ ጀርባ ልዩ ልዩ የመብት ጥሰቶች እና የተጀመረውን የዲሞክራሲ ለውጥ ሂደት የሚያደናቅፉ ደባዎች መፈጸማቸውን አረጋግጠናል ሲሉ አንዳንድ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገለጹ።

https://p.dw.com/p/38vYJ
Dr Abiy´s Frankfurt welcome event Organizers complaints and resolutions
ምስል DW/E. Fekade

ኤምባሲዎች ዲያስፖራውን መንግሥትን የሚያገናኙ ድልድዮች ሊሆኑ ይገባል

ባለፈው ጥቅምት 21,2011 ዓ.ም ከተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የፍራንክፈርቱ ሕዝባዊ ውይይት መድረክ ጀርባ የሰንደቅ ዓላማ ክልከላን ጨምሮ ልዩ ልዩ የመብት ጥሰቶች እና የተጀመረውን የዲሞክራሲ ለውጥ ሂደት የሚያደናቅፉ ደባዎች መፈጸማቸውን አረጋግጠናል ሲሉ አንዳንድ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች እና የንዑሳን ኮሚቴዎች አባላት ገለጹ።

በመርሃ ግብሩ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ከመላው አውሮጳ የኢትዮጵያውያኖች እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህብረት ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በመላው አውሮጳ ለውጡን የሚያደናቅፉ ዲያስፖራውን የሚከፋፍሉ እና ያልተደመሩ ናቸው ያሏቸውን የኤምባሲ ሰራተኞችና ዲፕሎማቶች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መንግሥትን ጠይቀዋል። ኤምባሲዎች ዲያስፖራውን የሚከፋፍሉ ሳይሆኑ ህዝብና መንግሥትን የሚያገናኙ ድልድዮች ሊሆኑ ይገባል ያሉት አስተባባሪዎቹ ሙያና ክህሎች ያላቸውን ለቦታው የሚመጥኑ ዲፕሎማቶችን ከመደቡ ጎን ለጎን ወጭ አባካኝ የሆኑ መዋቅሮችንም ለማስተካከል የፖሊሲ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል :: በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስል ጽህፈት ቤት ጄኔራል ቆንሱል አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ ባንዲራ ክልከላን በተመለከተ ለተነሳው ቅሬታ ተጠያቂው ኤምባሲው ሳይሆን ዝግጅቱ የተካሄደበት የአሬና ስታዲየሙ የጸጥታ አስከባሪ ሰራተኞች መሆናቸውን ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ማረጋገጡን ለ «DW» አስረድተዋል:: ያም ቢሆን በሕዝብ ላይ ለተፈጠረው ችግር እና መጉላላት ለንዑሳን ኮሚቴዎች ኤምባሲው ይቅርታ መጠየቁን ነው አቶ ሙሉጌታ ጨምረው የገለጹት:: ለዝግጅቱ የተደረጉ ወጭዎች እና ገቢዎችንም በተመለከተ ለሕዝብ ይፋ እና ግልጽ ናቸው ብለዋል:: ዝርዝሩን እንዳልካቸው ፈቃደ አጠናቅሮታል::

PM Abiy Ahmed in der Frankfurt Arena
ምስል DW/W. Tesfalem

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ባለፈው ጥቅምት 21,2011 ዓም በፍራንክፈርት ከተማ ያካሄዱት ውይይት የልዩነት እና የጥላቻውን ግንብ በማፍረስ ዲያስፖራው በአገር ልማት እና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ግንባታ ላይ የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርግ ታሪካዊ መሰረት መጣሉ ተነግሯል። ይሁን እንጂ ከመድረክ ጀርባ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ አንዳንድ ታዳሚዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ገልጸው ነበር ::  የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፍራንክፈርት ዝግጅት አስተባባሪዎች እና የንዑሳን ኮሚቴዎች አባላት በዕለቱ ከሕዝባዊ ጉባኤው ጀርባ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን እና ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት የመጡ የሃይማኖት አባቶችን በክረምት ብርድ ለሰዓታት በር ላይ እንዳይገቡ አቁሞ ማጉላላትን ጨምሮ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ወደ ስታዲየሙ እንዳይገባ ክልከላ መጣሉ ብዙሃኑን እንዳስቆጣ ገልጸዋል::ሙስሊም ሴቶች በራሳቸው ላይ በሂጃብ መልክ የጠመጠሙትን በጸጉራቸው ላይ ያሰሩትን የሰንደቅ ሪቫን እና በእጃቸው ላይ ያጠለቁትን የባንዲራ ምልክት ጭምር በማስወለቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ኮንቴነሮች ውስጥ እንዲጥሉ መደረጉ ከሕጻናት ልጆች ጋር የመጡ ሴቶችም እንዲሁ የእጅ ቦርሳቸውን ይዘው እንዳይገቡ ማገድ በፖለቲካው የተቃውሞ ጎራ የነበሩ ግለሰቦችን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአቀባበል ኮሚቴ እና በዝግጅት ውስጥ ተሳትፎ እናዳያደርጉ መከልከል ከባጅ እና ከመግቢያ ካርዶችም ጋር በተያያዘ በቀጥታ የሚመለከታቸውን አካላት ለይቶ አለማደል ለስራ እና ለማስተናበር የመጡ ሰዎችንም እንቅስቃሴ በስታዲየሙ ውስጥ መገደብ ከፍተኛ ቅሬታን ከፈጠሩት ችግሮች ዋንኞቹ መሆናቸውን ከሕዝብ መረጃ በማሰባሰብ እና በቴሌኮንፈረንስ ተጨማሪ ውይይቶችን በማካሄድ የጋራ ግንዛቤ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል:: በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ከመላው አውሮፓ የኢትዮጵያውያኖች እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህብረት ጋር በጋራበሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኤምባሲው ለተፈጠሩት ችግሮች ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ በሚድያዎች ዝግጅቱ ያለ እንከን ተጠናቋል እያለ የሚሰጣቸው መግለጫዎች በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል::

በስታዲየሙ መግቢያ በሮች ላይ ሕዝቡን የሚያጉላሉ እና ሰንደቅ ዓላማ እንዳይገባ የሚከለክሉ ከኮሚቴው እውቅና ውጭ የተመደቡ ትግርኛ እና አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ግለሰቦች እንደነበሩ ደርሰንበታል ብለዋል የማህበራቱ አባላት:: ችግሩንም የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ መቋቋም ሲገባው የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የነበረን እና ጉዳዩ የሚመለከተውን ግለሰብ የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አድርጎ በመምረጥ ምድብ ስራ ላይ የነበሩት የኮሜርስ ባንክ አሬና ስታዲየም የጸጥታ አስከባሪ ሰራተኞች የፈጸሙት ስህተት ነው የሚል ማስተባበያ ለመስጠት የተሞከረበት ሂደትም ተቀባይነት እንደማይኖረው ነው ይፋ ያደረጉት:: ከአሁን ቀደም ኢትዮጵያ እና የጀርመን መንግሥት የስደተኝነት ተገን ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያጣ ኢትዮጵያውያንን  ወደ አገራቸው ለመመለስ ተፈራርመውታል የሚባለው ስምምነት በአገሪቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እስኪረጋጋ ተፈጻሚ እንዳይሆን ዶክተር ዐቢይ ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንግላ ማርኬል ጋር እንዲነጋገሩበት ኤምባሲው ትኩረት ሰቶ እንዲጠይቅ ሃላፊነት ቢሰጠውም ጥያቄውን አለማቅረቡም እንዳሳዘናቸው ነው የገለጹት።

Abiy Ahmed in Frankfurt Vorbereitungen
ምስል DW/E. Fekade

ምንም እንኳ ይቅርታ የተፈጠረውን ስህተት ባይቀይረውም ለወደፊቱ በመግባባት እና በመተማመን አብሮ ለመስራት ጠቃሚ ነው የሚሉት አስተባባሪዎቹ የኤምባሲ ቀንስላ ጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች ግን ለዚህ ዝግጁ አለመሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል ብለዋል:: ሕዝብን በማጉላላት በመከፋፈል እና ሃላፊነት የጎደለው  የመብት ጥሰት በመፈጸም ዜጎች በአገር ልማት በእውቀት ሽግግር እና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ማቅረብ የተፈለገውን ያህል ውጤት አያመጣም የሚለው የኮሚቴ አባላቱ መግለጫ መንግሥት ለተፈጠረው ችግር አፍጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥም ጠይቋል::

አሁን የተገኘው ለውጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን የገበሩበት ግፍ መከራ እና ሰቆቃ የተቀበሉበት እንዲሁም አካላቸውን ያጡበት እና ለስደት የተዳረጉበት መሆኑን ያወሳው የድርጅቶቹ መግለጫ በመላው አውሮፓ የሚገኙ ኤምባሲዎች ላለፉት 27 ዓመታት ዲያስፖራውን እና አገርን አገናኝ ድልድይ ከመሆን ይልቅ ዜጎችን በብሄር እና በቋንቋ ከፋፋይ ፖሊሲ አደራጅተው አፋኝ እና ቅራኔን የሚፈጥር መዋቅር የዘረጉበት መናኸሪያ እንደነበር አውስቷል::የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ አባካኝ ነው ያለውንም የዲያስፖራ ጉዳዮች ክፍል ከኤምባሲዎች መዋቅር እንዲሰረዝ እና እስካሁን በለውጡ ሂደት ያልተደመሩ የኤምባሲ ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶችም በአስቸኳይ እንዲቀየሩ ብሎም የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ ነው መንግስትን የጠየቀው ::

በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ጄኔራል ቆንሱል አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ ባንዲራ ክልከላን በተመለከተ ለተነሳው ቅሬታ ተጠያቂው ኤምባሲው ሳይሆን የአሬና ስታዲየሙ የጸጥታ አስከባሪ ሰራተኞች መሆናቸውን ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ማረጋገጡን አስረድተዋል:: ያም ቢሆን ኤምባሲው በጠራው ስብሰባ ለአዘጋጅ እና ንዑሳን ኮሚቴ አባላት ይቅርታ መጠየቃቸውን ነው የገለጹት:: እስካሁን ሕዝቡ እንዲያውቀው የሚድያ ሽፋን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ግን አልተሳካልንም ነው ያሉት:: ለዝግጅቱ የተደረጉ ወጭዎች እና ገቢዎችንም በተመለከተ ለሕዝብ ይፋ እና ግልጽ ናቸው ያሉት ጄኔራል ቆንሱል ነጻ የመኪና ማቆሚያ ተዘጋጅቷል ተብሎ ከተነገረ በኋላ ሰዎች ለመኪና ማቆሚያ እንዲከፍሉ መገደዳቸው አግባብ እንዳልሆነ እና ከስታዲየሙ አከራዮች ስምምነት ውጭ እንደነበረም ተናግረዋል ::

Frankfurt Ministerpräsident Äthiopien Abiy Ahmed  in  Commerzbank-Arena
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

DW የአሬና ስታዲየም የጸጥታ አስከባሪ ሰራተኞች የባንዲራውን ክልከላ መፈጸማቸውን አምነዋል ተብሎ በቆንስላው ጽህፈት ቤት የተሰጠውን ምላሽ ለማጣራት ሙከራ እያደረገ ነው:: በመላው አውሮፓ የሚገኙ ኤምባሲዎች ሕዝብን እና አገርን አገልጋይ ሆነው ዳግም እንዲዋቀሩ የጠየቁት ባለፈው ወር በፍራንክፈርት ከተማ የተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አቀባበል ዝግጅት ኮሚቴ አባላት መንግሥት የጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማገዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ በንቃት እንደሚሳተፉም ገልጸዋል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሠ