1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ካብ አዲስ አስመራ»

ሐሙስ፣ ሐምሌ 5 2010

ከአፍሪቃ ኅብረት መዲና አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ስር ዉበትዋና ታሪክዋ ተጠብቆ እንዲዘልቅ በመንግሥታቱ ድርጅት ጥበቃ ስር ወደ ተመዘገበችዉ አስመራ ከተማ የኢትዮጵያዉ አየር አዉቶቡስ ሊጀምር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተዉታል።

https://p.dw.com/p/31MU4
Ethiopian Air Lines
ምስል Ethiopian Air Lines

«ከአዲስ አስመራ ሰላም መንገድ ገብቶአል»

በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ለሃያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረዉ የቀጭኑ ሽቦ መስመር ተቀጥሎ፤ ወዳጅ ዘመድ ሃሎ ሃሎ መባባል ከጀመረ ቀናት አንድ ሁለት ብለዋል። ባለፉት 20 ዓመታት በኩርፍያ የዘለቁት የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት ተጠሪዎች በፍቅር የጥልን ግንብ ንደዉ ግንኙነታቸዉን ከጀመሩ ቀናት ቢቆጠርም፤ በሁለቱ ሃገራት ያሉት ሕዝቦች ግን አንዱ ለአንዱ ናፍቆቱን በቀጥታም ባይሆን በተለያዩ መንገዶች ሲገላለፅ መቆየቱ እሙን ነዉ። የተለያዩ ቤተሰቦች እንደየአቅማቸዉ በሦስተኛ ሃገር በኩል አቋርጠዉ ለዓይነ ስጋ ለመብቃት የቻሉ አሉ፤ ያልቻሉት ጊዜን ሲጠብቁ ኖረዉ ይኸዉ አሁን ጊዜ ሐኪም ሆኖ ፈዉስ አመጣና የሁለቱ ሃገር ሕዝቦች እልል አሉ፤ ለዓይነ ሥጋ በቁ።  ኢትዮጵያና ኤርትራ ሙዚቀኞች በሞያቸዉ ክራር ከበሮ መሰንቆአቸዉን ይዘዉ የሁለቱን ሃገራት ወንድማማችነት ነፍቆት አለመረሳሳትን ሲያዉጁና ሲያዜሙ ግን ዓመታት ተቆጥረዋል።

Eritrea Treffen Abiy Ahmed und Isaias Afwerk  in Asmara
ምስል picture-alliance/dpa/ERITV

አርቲስት አሳየ ዘገየ ይባላል። ድምጻዊ የዜማ እና የግጥም ደራሲ እንዲሁም የአቀናባሪ ነው። ነዋሪነቱ በሰሜን አሜሪካ የሆነው አሳየ የተለያዩ ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎችንም ይጫወታዕ። ሙዚቀኛ አሳየ ይህችን ከአዲስ አስመራ የተሰኘች ነጠላ ዜማን የዛሬ ሁለት ዓመት ለአድማጭ ጆሮ ሲያደርስ በርግጥ የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች ወዳጅነታቸዉን እንደሚቀጥሉ ያዉቅ እንደነበር አስረግጦ ይናገራል። ቢሆንም ይህን ሙዚቃ እንደለቀቀ ችግርም አላጣዉም።     

« በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነዉ። እኔ ይህ ነገር እንደሚከሰት በፈጣሪ ፈቃድ እርግጠኛ ነበርኩ። ሙዚቃዉንም ለአድማጭ ጆሮ ሳደርሰዉም በድፍረት ነዉ። በርግጥ በስራዬ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ። አንዳንድ ነገሮች ይላኩልኝ ነበር። ቢሆንም ግን ደስታዉም በዛዉልክ በበለጠ በምልክት ይደርሰኝ ነበር።»

ሙዚቀኛ አሳየ ዘገየ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለዉ ወንድማማችነት ዳግም ማለምለሙን ማየቱ እጅግ እንዳስደሰተዉ ይናገራል። ይህ ቀን እንደሚመጣም ጠንቅቄ አዉቅ ነበር ሲል ነዉ የሚናገረዉ። ይህንኑ ከኤርትራዉያን ባልንጀሮቹ ጋር በየቀኑ የሚያነሳዉ ጉዳይ ነዉ ብሎአል። ከዝያም አልፎ ሙዚቀኛ አሳየ ከኤርትራዊት የትዳር ጓደኛዉ ዛሬ 28 ዓመት ጎረምሳ ልጅ አድርሶአል። 

Äthiopien Sänger Asaye Zegeye
ምስል Asaye Zegeye

«ከአዲስ አበባ አስመራ የሚለዉን ዘፈን ስደርስ፤ ኤርትራዊ ጓደኞቼን በማየት ነዉ። በእርግጥ ባለቤቴ የልጄ እናት ኤርትራዊ ናት። ከዝያም የመነጨ ስሜት ነዉ። በዝያ ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ምን ያህል ፍቅር እንዳለን በዉጭ ዓለም ዉስጥ ስንኖር የሚታይብን ፍቅር በጣም ደስ የሚልና ተለያይተን የማንለያይ ሕዝቦች ነን። በአንድ ባህል በአንድ መልክ ያለን ሰዎች ነን። ሙዚቃዉን ስደርስ ያ ስሜት ነበር እኔ ዉስጥ የነበረዉ። ይህ ሙዚቃን ካወጣሁ ከሁለት ዓመት በኋላ ዛሬ በሁሉ ቦታ ተቀባይ ከመሆን አልፎ ፤ እንደዉም በአንዳንድ የብዙኃን መገናኛዎች እንደተነገረዉ ሙዚቃዉን ይዤ ወደ አፍሪቃ በመሄድ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ለኤርትራ መንግሥት ይህን ሙዚቃ እንዳቀርብ ብዙዎች ግፊት እየሰጡኝ ነዉ። ይህ በእዉነቱ ግዴታዬም ነዉ። እግዚአብሔር ይመስገን ነዉ የምለዉ።»      

ዘፋኞች ሥራዎቻቸውን በቀጥታ ከመድረክ በሚያቀርቡባቸው አካባቢዎች የሙዚቃ አልበሞቻቸውን ይሸጣሉ። ወደተለያዩ ቦታዎች በመጓዝና የሙዚቃ ዝግጅቶችን በማቅረብ አዲስ አልበማቸውንም ያስተዋውቃሉ።  አዲስ አበባ አስመራ የሚለዉን ይህን ነጠላ ዜማህን ግጥም ለአድማጭ ጆሮ ያበቃኸዉ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ነዉ ። ባለፉት ሁለት ዓመታት ስለዚህ ነጠላ ዜማህ ብዙም አልተሰማም ነበር። « በመጀመርያ ደረጃ ከአዲስ አበባ አስመራ የሚለዉን ዘፈን ግጥም ከመጻፊ በፊት፤ ስለአዲስ አበባ እና አስመራ ወንድማማችነት የሚገልጽ የሙዚቃ ግጥም የዛሬ ሠላሳ ዓመት ፅፊያለሁ። ሌላ ማርታ ኃይሉ ለምትባል አርቲስት ካብ አስመራ የሚል ወይም «ከአስመራ ልጅ ፍቅር ይዞኛል» በሚል የፃፍኩት የሙዚቃ ግጥም ነበር። ሙዚቃዉ በትግርኛ  ዘፈን ስልት የተሰራ በአማርና እና በትግሪኛ የተቀላቀለበት ነበር። በአማርና የተዘፈነ በትግሪኛ የሙዚቃ ስልት የተቀናበረዉ ሙዚቃ ለመጀመርያ ጊዜ የዛሬ ሠላሳ ዓመት የተሰራዉ በእኔ ነዉ። ሙዚቃዉንም ያቀናበርኩት እኔ ነኝ።»           

Eritrea Bevölkerung feiert Referendum 1993
ምስል Imago/United Archives International

የሙዚቃው ኢንዱስትሪ እጅግ በጣም ፈጣን እድገት የሚታይበት፣ ተለዋዋጭና ከፍተኛ ፉክክር ያለበት ነው። የሙዚቃ ምርጫ ይለዋወጣል፤ አሮጌ ቴክኖሎጂዎች በአዲስ ይተካሉ፤ የቆዩ ስልቶችም በአዲስ መልክ ይቀርባሉ።  ከአዲስ አስመራ የተሰኘዉን የሙዚቀኛ አሳየ ነጠላ ዜማዉን ያዳመጡ ምን ዓይነት አስተያየት ሰጥተዉ ይሆን? አርቲስት አሳየ እንደሚለዉ ጥሩዎቹን አስተያየቶች ብነግርሽ ይሻላል፤ ይላል።

«ከኢትዮጵያዉያን እና ከኤርትራዉያን የደረሰኝ የእንኳን ደስ አለህ ጥሩ ሙዚቃ ነዉ የሚል መልክት ቁጥሩን መናገር ያቅተኛል። እንደዉም ፈጣሪ ለአንተ ፀጋ የሰጠኽ ሰዉ ነህ ያሉኝ ሁሉ አሉ። ይህን አስበህ ስለሰራህ እናመሰግናለን ያሉኝ ብዙ ናቸዉ። ከዛ ባሻገር አንዳንድ በተሳሳተ አመለካከት ላይ የነበሩ እህትና ወንድሞቼ ፤ እንዲሁም አንዳንድ አርቲስቶች ሁሉ እንዴት እንዲህ አይነት ስራ ትሰራለህ ጦርነት ዉስጥ ያለን ሰዎች ላይ፤ ዉግያ ላይ ያለን ሰዎች ላይ። ደሞስ የኢትዮጵያን ሴትች አጥተህ ነዉ ወይ ወደ ኤርትራ የሄድከዉ ለምን እንዲህ አይነት ነገር አደረክ ብለዉ ያሉኝ ሁሉ ነበሩ።  ግን ይሄ አለማወቅ እንጂ በእዉነት ቢያስቡት እና አንዳንድ የዘፈኑን ግጥም ስለፍቅር ስለሰላም መሆኑን ቢያጤኑ ኖሮ እንዲህ ባላሉኝ ነበር።  እኛ ለኩርፍያ መኖር የለብንም። እኛ መኖር ያለብን ለሰላም ለፍቅር ለአንድነት ነዉ። እያንዳንዳችን ማሰብ ያለብን ይሄንን ነዉ። ከኩርፍያ ምን ይገኛል? ከጠብ ምን ይገኛል? ከሰላምና ከፍቅር ግን ብዙ ነገር ይገኛል። ይሄንን ነዉ ማሰብ ያለብን።»

አርቲስተ አሳየ እንደገለፅከዉ ይህ ሙዚቃ ከወጣ ሁለት ዓመት ሆነዉ የኤርትራዉ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አስመራ ላይ ሲገኛኙ በተለይ የነበረዉ አቀባበል በሆታ በእልልታ በደስታ እናቶች አምባሻ ጋግረዉ ፈንድሻ ቆሎ ይዘዉ አረንጓዴ ቄጤማና አበባን እያዉለበለቡ ፤ አበሻ ልብስ አድርገዉ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ እያዉለበለቡ ነዉ ደማቅ አቀባበል ያደረጉት ። ከዚህ ወድያ የአንተን ሙዚቃ ያደመጠ እና ስለአንተ ሙዚቃ ያነሳልህ አለ? 

Eine afrikanische Insel der Architektur
ምስል DW/Y.Tegenewerk

«አዎ። አብዛኞች አንስተዉልኛል። እንደዉም በአንዳንድ ሚዲያዎች ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ መሄድ እንዳለብኝ ግፊት እየሰጡኝ ነዉ። ሚዲያም ላይ የተበተኑ ነገሮች አሉ። ከኤርትራ ቆንስላ ጽ/ቤት እንደዚሁ አንዳንድ ነገሮች ሰምቻለሁ፤ ለምሳሌ ለአዲሱ ዓመት ወደ ኤርትራ ሄጄ ይህን ሙዚቃዬን የምጫወትበትን ወደ ኢትዮጵያም መድረክ ላይ እንድጫወት ዝግጅት እየተደረገልኝ ነዉ። ይህንም በፀጋ ተቀብየዋለሁ።»  

የዘፈን ድርሰትን በመፃፍ የኢትዮጵያን የተለያዩ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎች በመጫወት ፤ በሙዚቃ ቅንብር እና በዜማ ሲያገለግል ወደ 40 ዓመት የሆነዉ አርቲስት አሳየ ዘገየ በቅርቡ በሙዚቃዉ መዲና አስመራ እና ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ክራር መሰንቆዉን ይዞ ወደ አፍሪቃዉ ቀንድ እንደሚያቀና አጫዉቶናል ። ከአርቲስት አሳየ ዘገየ ጋራ ለነበረን ቆይታ በዶይቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ  

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ