1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬምኒትስ እና ቀኝ ጽንፈኞች

ረቡዕ፣ ነሐሴ 30 2010

ፖሊስ ህብረተሰቡ እንዲረጋጋ እና ህዝቡም ሆነ ጋዜጠኞች ስለ ወንጀሉ አፈጻጸም በይሆናል ከመናገር እንዲቆጠቡ ተማጽኗል።ያም ሆኖ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን መላ ምቱ እየተሰራጨ ነው። ቀኝ ጽንፈኛ ቡድኖችም ሆነ ብለው የተሳሳቱ መረጃዎችን በማቅረብ ተጨማሪ ሰልፈኞችን ለመሳብ ቅስቀሳ ያደርጋሉ።

https://p.dw.com/p/34IjX
Rechte demonstrieren in Chemnitz
ምስል picture alliance/Zumapress

ኬምኒትስ እና ቀኝ ጽንፈኞች

ኬምኒትስ በተባለችው የምሥራቅ ጀርመን ከተማ አንድ ጀርመናዊ በተገን ጠያቂዎች ተገድሏል የመባሉ ዜና ከተሰማበት ከዛሬ 10 ቀናት ወዲህ ቀኝ ጽንፈኞች፣አጋጣሚውን ለዓላማቸው ማራመጃ መጠቀማቸውን ቀጥለዋል። በቁጥር እንበልጣቸዋለን የሚሉት የነርሱ ተጻጻሪዎች ደግሞ ህዝቡን አይወክሉም ሲሉ ድርጊታቸውን በተለያዩ መንገዶች እያወገዙ ነው። 
ኬምኒትስ በምሥራቅ ጀርመኑ በዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ውስጥ የምትገኝ 246,353 ህዝብ የሚኖርባት ከተማ ናት። ኬምኒትስ በተባለው አነስተኛ ወንዝ  የተሰየመችው የዚህች ከተማ ኤኮኖሚ መሠረት፣ አገልግሎት ሰጭ ዘርፎች፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና 10 ሺህ ተማሪዎች ያሉት የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዋ ናቸው። ከጎርጎሮሳዊው 1953 እስከ 1990 የኮምኒዝም ፍልስፍና አፍላቂው የ«ካርል ማርክስ» ከተማም ትባል ነበር። በከተማዋ እምብርት የሚገኘው ግዙፉ የማርክስ ሐውልት የጎብኚዎች መስህብ ነው። ይህች ከተማ ካለፉት 10 ቀናት ወዲህ በመገናኛ ብዙሀን ተደጋግማ ትነሳለች። የዚህ መነሻም ከዛሬ 10 ቀናት በፊት በከተማይቱ አንድ ጀርመናዊ በተገን ጠያቂዎች ተገደለ መባሉ ነው። ጀርመናዊው ግድያ እንደተሰማ   ቀኝ ጽንፈኞች የተጋነኑ መረጃዎችን በኢንተርኔት ከማሰራጨት በተጨማሪ ዘረኛ ዘለፋዎችን እያሰሙ በከተማዋ ማዕከል ያጋጠሟቸውን የውጭ ዜጎች እያባረሩ እና እያዋከቡ ጥቃት እስከመፈጸም ደርሰዋል። እነዚሁ «ጀርመን ለጀርመናውያን» የሚሉት ቀኝ ጽንፈኞች የውጭ ዜጎች፣ ከከተማችን ውጡ ይሉም ነበር።
ቀኝ ጽንፈኞች እነርሱን ለማስቆም ከሞከሩ ፖሊሶች ጋርም ተጋጭተዋል። ፖሊስ እንዳለው በእለተ እሁድ በከተማይቱ ይካሄድ በነበረ በዓል ላይ ሟች ሁለቱን ተጠርጣሪዎች በመስደቡ  በተፈጠረ ግጭት በስለት ከተወጋ በኋላ ነው ህይወቱ ያለፈው። እንደ ፖሊስ እውነታው ይሆ ሆኖ ሳለ ቀኝ ጽንፈኞች ሰውየው የተገደለው  አንዲትን ሴት ከጥቃት ለመከላከል ጣልቃ በገባበት አጋጣሚ ነው ብለው በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን የሀሰት መረጃ ካሰራጩ በኋላ ነበር ብጥብጡ የተባባሰው። ።በዕለቱ አደባባይ ከወጡት 800 ሰዎች መካከል 50ው አመፀኞች እንደነበሩ ፖሊስ ተናግሯል። ድርጊቱ በጀርመን ባለሥልጣናት ተኮንኗል። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በኬምኒትስ የደረሰውን ረብሻ እና ስርዓተ አልበኝነት አውግዘዋል።
«እዚያ ያየነው የህግ የበላይነት ባለበት ሀገር ቦታ የለውም። ሰዎቹ በጉልበተኞች እና አመፀኞች በጎዳናዎች ላይ በጥላቻ ሲታደኑ የሚያሳይ ቪድዮ አለን። በበኩሌ የተፈጸመው የህግ የበላይነትን የሚጻረር ለመሆኑ ከዚህ በላይ አጽንኦት ልሰጠው አልችልም።»
የእሁዱ አመጽ የኬምኒትሱ ተቃውሞ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አልነበረም። ተቃውሞው እዚያው ኬምኒትስ በማግስቱ ማለትም ባለፈው ሰኞ ቀጥሎ ቀኝ ጽንፈኞቹን ፣አፍቃሬ ናዚዎች እና በመላ ጀርመን በእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ ረብሻ የሚያስነሱ ቡድኖች ተቀላቅለዋቸው የነርሱ እና የደጋፊዎቻቸው ሰልፈኞች ቁጥር 6ሺህ ደረሰ። እነርሱ ከተሰለፉበት ስፍራው ትይዩ ደግሞ በአመዛኙ የግራ ክንፍ መስመር ተከታዮች የሚያመዝኑባቸው አንድ ሺህ ፀረ ቀኝ ጽንፈኞች ሰልፈኞች ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ነበር።
በወቅቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭት ቢፈጠርም በስፍራው ከተሰማሩት 600 ፖሊሶች አቅም በላይ ሆኖ ፖሊስ ሃላፊነቱን ባለመወጣት ሲወቀስ ከርሟል። በሰኞው ግጭቱ ሁለት ፖሊሶች እና 18 ሰልፈኞች መጎዳታቸው ተነግሯል። ሰልፉን ለመዘገብ የተሰማሩ ጋዜጠኞችም ወከባ ደርሶባቸዋል ።ፖሊስ ወቀሳ የቀረበበት በዚህ ብቻ አልነበረም። የጀርመንን ህግ በመጻረር ለአንድ ተጠርጣሪ የተቆረጠ የእስር ማዘዣን ለቀኝ ጽንፈኞች አሳልፎ ሰጥቷል ተብሎም ስሙ ሲጣል ሲነሳ ነበር። ቀኝ ጽንፈኞች በኢንተርኔት ባሰራጩት በዚሁ የእስር ማዘዣ የተጠርጣሪዎቹ ሙሉ ስም፣የጥቃቱ ሰለባ ማንነት የዓይን ምስክሮች እና የዳኛው ስም ሰፍሯል። እንደ ህጉ ለፍትህ ስርዓቱ አገልጋዮች ለተጠርጣሪዎችም ሆነ ምስክሮች ጥበቃ ሲባል ማንነታቸው ይፋ መሆን አልነበረበትም። 
በጀርመን ፓርላማ አብዛኛውን የተቃዋሚዎች መቀመጫ የያዘው ፀረ-የውጭ ዜጎች አቋም የሚራምደው «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ፓርቲ እና ፀረ እስልምና አቋም ያለው ፔጊዳ የተባለው ንቅናቄ  በዚያው በኬምኒትስ ሊያካሂዱ ያቀዱት 6 ሺህ ደጋፊዎቻቸውን የሚያሳትፍ የተቃውሞ ሰልፍ ፖሊስ አስቁሟል። ሰሞኑን ቀኝ ጽንፈኞች እና ተቃዋሚዎቻቸው ግራዎቹ ተፋጠው በቆዩባት ኬምኒትስ ቀኝ ጽንፈኞች በውጭ ዜጎች እና በፖሊሶች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ያወገዘ የሙዚቃ ድግስም ተካሂዷል። የጀርመን ታዋቂ ድምጻውያን በተሳተፉበት በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የተገኙት ድምጻውያን ሙያቸውን ተጠቅመው ችግሩን ለመከላከል መምጣታቸውን ተናግረዋል። ከመካከላቸው አንዱ ሞንቺ የተባለው ታዋቂ ዘፋኝ ነው። 
«በኬምኒትስ የሆነው በሌሎች የጀርመን ግዛቶችም ሊደርስ ይችል ነበር፤ እና በምንገኝበት ፌደራዊ ግዛትም ቢሆን። እናም ለዚህ በጎ ዓላማ በተዘጋጀው የሙዚቃ ትርዒት ላይ በመሳተፍ ግድያን መሣሪያ አድርጎ የሚፈፀመን ዘረኛ የደቦ ጥቃትን ሰዎችን በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ማጥቃት እና መጨቆንን ለመቃወም ተጠይቀናል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ እኛ ብዙ ሰዎችን መድረስ የመቻል አቅማችንን እና ተሰሚነታችንን የመጠቀም ግዴታ አለብን። በዚህ ዓይነቱ ድግስ ሳልሳተፍ ብቀር አፍራለሁ። የባንዱ አባላት በሙሉ ተመሳሳይ ስሜት ነው ያላቸው።»
በኬምኒትሱ ፀረ ዘረኞች እና በውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥላቻ በመቃወም በተካሄደው የሙዚቃ ድግስ ላይ 50 ሺህ ሰዎች ተገኝተዋል። «ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ» የሚሉት ቀኝ ጽንፈኞች በኬምኒትስ የፈጸሙትን የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀይኮ ማስ  ከአሳሳቢነትም የባሰ ነው ሲሉ  ነው የገለጹት። በየሄዱበት አገር ሁሉ ጀርመን ምን እየሆነ ነው የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡላቸው የተናገሩት ማስ አስደሳቹ ነገር አብዛኛው ህዝብ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተቃዋሚ መሆኑ ነው ብለዋል።
«ኬምኒትስ የሆነው ከአሳሳቢም በላይ ነው። አንድ ሰው በአደባባይ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በአውላላ መንገድ ላይ ተገድሏል። ከዚያ በኋላም ሰዎችን በከተማዋ መሀል ያሳድዱ ነበር። ሰዎች በየጎዳናው ሲያልፉ እንደ ሂትለር ሰላምታ ይሰጡ ነበር። ይህን ያደረጉት ጥቂቶች አልነበሩም። ጀርመን ምን እየሆነ ነው ? እያሉ ስለዚህ ጉዳይ ውጭ ያሉ የሥራ ባልደረባዎቼም ይጠይቁኛል። ስለዚህ አሁን የኬምኒትስን እውነተኛ ገጽታ የሚያሳዩ በርካታ ዴሞክራቶች ብቅ ብቅ በማለታቸው ደስተኛ ነኝ። አብዛኛው ጀርመናዊ በነጻ እና የተለያየ ሃሳብ እና እምነትን ማስተናገድ በምትችል ሀገር ነው መኖር የሚፈልገው። ከዚህ ያፈነገጡት ደግሞ አኛ ከምንፈልገው በላይ ይጮሀሉ። ሆኖም የሰለጠነ ህዝብ ድምጽ ደግሞ ከቀድሞው ከፍ ማለት አለበት።»    
ከዚሁ ጋር ለህብረተሰቡ መረጃዎችን በፍጥነት ማቅረቡ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባውም የጀርመን ባለሥልጣናት ያምናሉ። ከ10 ቀን በፊት ተገን ጠያቂዎች በኬምኒትስ ፈጸሙ በተባለው ጥቃት ማንነቱ ያልተገለጸ የ35 ዓመት ጀርመናዊ በስለት ተወግቶ ከመገደሉ ሌላ ሁለት ሰዎችም በጽኑ ቆስለዋል። በግድያው የተጠረጠሩት ሶሪያዊ እና ኢራቃዊ ስደተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል።  ሦስተኛ ተጠርጣሪ ደግሞ እየተፈለገ ነው ብሏል ፖሊስ። ፖሊስ እስካሁን ይካሄዳል ስለተባለው ምርመራ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም። በበኩሉ ግን ህብረተሰቡ እንዲረጋጋ እና ህዝቡም ሆነ ጋዜጠኞች ስለ ወንጀሉ አፈጻጸም በይሆናል ከመናገር እንዲቆጠቡ ተማጽኗል።ያም ሆኖ በመገናና ብዙሀን መላ ምቱ እየተሰራጨ ነው። ቀኝ ጽንፈኛ ቡድኖችም ሆነ ብለው የተሳሳቱ መረጃዎችን በማቅረብ ተጨማሪ ሰልፈኞችን ለመሳብ ቅስቀሳ ያደርጋሉ። ይህን ለመከላከልም ፖሊስ በትዊተር ጭምር ከሚወጡት መረጃዎች መካከል ሀሰት የሆኑትን ማጋለጥ ይዟል። ሆኖም የቀኝ ጽንፈኞቹ መረጃ የማቀበል ፍጥነት  የኬምኒትስ የምትገኝበት የዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ፖሊስ እና ፌደራል መንግሥቱን ሳይቀር አስገርሟል።
«የሀሰት ዜና የበላይ እንዳይሆን ማድረጉ ሊሳካልን ይገባል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ስለተፈጸመው ጉዳይ ሁሉም እንዲያውቅ ተጨባጭ መረጃዎችን ማቅረብ አለብን። ይህ አብሮ የመኖር የመከባበር የስርዓት እና የደህንነት እንዲሁም የዴሞክራሲ እና የህግ የበላይነት ጉዳይ ነው። »
የዛክሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሻኤል ክሬትሽሜር የዛክሰን ባለሥልጣናት የጀርመናዊው ግድያ ጉዳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ እና ተጠያቂዎቹንም ለፍርድ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል። ይሁን እና ክሬትሽሜር ለዓመታት በበፌደራል ክፍለ ግዛታቸው በቀኝ ጽንፈኞች ላይ ወሳን የሆነ እርምጃ ባለመውሰድ ይወቀሳሉ። ወቀሳውን የቀኝ ጽንፈኞች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት ስቲቭን ዛይፈርትም ይጋራሉ።
«ሁኔታው ምንድን ነው ዛክሰን ያሉት አፍቃሪ ናዚዎች ለረዥም ጊዜ ሳይከሰሱ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በዚህም ርዕዮተ ዓለማቸውን ወደ የአብዛኛው አስተሳሰብ ማድረግ ችለዋል።ይህ ዘረኝነታቸውንም ይጨምራል። ይህ እንደ ተለመደ ጉዳይ ሆኖ ሲታይ ማንኛውም ተቃዋሚ የአንድን ሰው ማንነት አደጋ ላይ ሊጥል እና ሁኔታዎችም በጣም በፈጣኑ የሚባባሱበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደርጋል።»
በዛይፈርት አባባል በዛክሰን ከጀርመን ውህደት በኋላ በ1990ዎቹ የተካሄደው ተቃውሞ ነው አሁን የተደገመው። ያኔ የውጭ ዜጎች ጥላቻ የተባባሰው ስራ አጥነት በመስፋቱ እና ኤኮኖሚውን በመንገዳደገዱ ነበር። አሁን ግን ሁኔታው በጣም ተለውጧል። በዛክሰን ስራ ከመቼም ጊዜ በላይ ይገኛል። ቱሪዝምን ጨምሮ ኤኮኖሚው አድጓል። አሁን ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው ጥቂቶች ይህን በጎ ውጤት አደጋ ላይ መጣላቸው ነው ስጋቱ። 

Chemnitz - Konzert gegen Rassismus
ምስል Reuters/H. Hanschke
Teilnehmer der Demonstration der AFD in Chemnitz greifen Journalisten und Polizei an
ምስል Reuters/H. Hanschke
Deutschland AfD-Kundgebung und Gegenproteste in Chemnitz ziehen tausende Demonstranten an
ምስል Getty Images/S. Gallup
Deutschland | Rechte Demo in Chemnitz
ምስል picture-alliance/dpa/R. Hirschberger

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ