1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮፊ አናን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12 2010

የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ ጋናዊው ኮፊ አናን በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ጋና የአንድ ሳምንት የሀዘን ጊዜ አውጃለች። 

https://p.dw.com/p/33MQF
UN Generalsekretär Kofi Annan beim National Forum
ምስል Reuters/Maxwells

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በዋና ጸሀፊነት በመምራት የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የሆኑትን እና ለስራቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት የተበረከተላቸው አናን ያረፉት በሚኖሩበት ስዊዘርላንድ እንደሆነ በስማቸው የሚጠራው ፋውንዴሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አናን ለአጭር ጊዜ ታመው እንደነበር የጠቀሰው የድርጅታቸው መግለጫ በመጨረሻ ቀናቶቻቸው ባለቤታቸው እና ሶስት ልጆቻቸው ከጎናቸው እንደነበሩ ጠቁሟል። እንደ ስዊዘርላንድ ዜና አገልግሎት ዘገባ አናን የሞቱት ጀርመንኛ ተናጋሪ በሆነው የሀገሪቱ ክፍል ባለ ሆስፒታል ውስጥ ነው። 
የአናንን ሞት ከተሰማ አንስቶ የዓለም መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሀዘናቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወቅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጎተሬዝ አናን “ለመልካም ነገር መሪ ኃይል” ነበሩ ሲሉ ገልጸዋቸዋል። “በብዙ መልኩ ኮፊ አናን ማለት የተባበሩት መንግስታት ነበሩ። የተለያዩ የኃላፊነት እርከኖችን ተሻግረው ድርጅቱን በአዲሱ ሚሊኒየም አቻ በሌለው ክብር እና ቁርጠኝነት እስከ መምራት ደርሰዋል” ሲሉ ሀዘን ባጠላበት ድምጽ ተናግረዋል። 
የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኮፉ አዶ በበኩላቸው አናን “ለሀገራቸው ከፍ ያለ ክብር ያመጡ ናቸው” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል። መንግስታቸው እና የሀገሬው ህዝብ “ታላላቅ ከሆኑት የሀገራቸው ልጆች አንዱ በሆኑት” በአናን ሞት ማዘኑን ገልጸዋል። “ጋናውያን በየራሳቸው መንገድ ወደ ዕድገት እና ብልጽግና የማምራት አቅም እንዳለቸው ጥልቅ እምነት ነው ነበራቸው” ሲሉ አናን ለሀገራቸው የነበራቸውን አመለካከት አስታውሰዋል። ፕሬዝዳንት አኮፎ አዶ የጋና ባንዲራ በመላው ሀገሪቱ እና በውጭ ሀገር ባሉ የሀገሪቱ ኤምባሲዎች ለአንድ ሳምንት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። 
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ አናንን “ታላቅ መሪ እና የተባበሩት መንግስታት ለውጥ አምጪ ነበሩ” ብለዋቸዋል። “ጥለውት የሄዱት ዓለም እርሳቸው ከተወለዱበት የተሻለ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሯ አናንን አሞግሰዋቸዋል።  የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ “ዛሬ ለሰዎች የቆመ ታላቅ ሰው አጥተናል” ሲሉ ሀዘናቸውን ገልጸዋል። እንደ ኮፊ አናን ሁሉ የኖቤል የሰላም ሽልማትን የተቀዳጁት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ሊቀ-ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ አናንን ስለሰጠን “ ለእግዚአብሔር ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን” ብለዋል። “አህጉራችንን እና ዓለምን በታላቅ ሞገስ፣ በሀቀኝነት እና በሊቅነት የወከሉ ነበሩ” ሲሉ ዴዝሞንድ ቱቱ አናንን አድንቀዋቸዋል።  
በጎርጎሮሳዊው 1938 በጋና የአሻንቲ ክልል መቀመጫ በሆነችው በኩማሲ ከተማ የተወለዱት አናን ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአሜሪካ ነው። ቦስተን በሚገኘው ዕውቁ የማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት አፍ ቴክኖሎጂ (MIT) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት አናን የተባበሩት መንግስታትን የተቀላቀሉት በጎርጎሮሳዊው 1962 ነበር። 
ጄኔቫ በሚገኘው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት በአስተዳደር እና በጀት መኮንነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስራቸውን የጀመሩት አናን ከ35 ዓመታት ግልጋሎት በኋላ በድርጅቱ ከፍተኛ የሆነው የዋና ጸሀፊነት ኃላፊነት ተቆናጥጠዋል። ከጎርጎሮሳዊው 1997 ጀምሮ ለሁለት የስልጣን ዘመን ድርጅቱን የመሩት አናን የኖቤል የሰላም ሽልማትን በጎርጎሮሳዊው 2001 ከድርጅቱ በጋራ አሸንፈዋል። የዲፕሎማሲ ስራቸውን ኃላፊነታቸው ከለቀቁም በኋላ የቀጠሉት አናን በኬንያ እና ሶሪያ ሰላም ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ይጠቀስላቸዋል። በመልካም አስተዳደር እና ሰላም ላይ የሚሰራ የራሳቸውን ድርጅት የመሰረቱት አናን እስከ ቅርብ ወራት ድረስ በማይናማር ራካሂን ግዛት በሚገኙ የሮሄንጂያ ሙስሊሞችን ቀውስ በሚመለከተው የአማካሪ ኮሚሽን ውስጥ ሲሰሩ ቆይተዋል።        

USA UNHCR Antonio Guterres und Un Generalsekretär Kofi Annan 2005
ምስል Getty Images/AFP/T. A. Clary
Kofi Annan nimmt Friedensnobelpreis entgegen
ምስል picture-alliance/dpa/H. Junge

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ