1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወባን በባህላዊ መድኃኒት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17 2010

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ,ም በመላው ዓለም 212 ሚሊየን ሕዝብ በወባ በሽታ ተይዞ ነበር። 429 ሺህ ሕዝብ ደግሞ ወባ ምክንያት ሞቷል። እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለውን የወባ በሽታ ፈፅሞ ለማጥፋት ሁሉም ቢስማማም፤ እንዴት ተግባራዊ ይሁን የሚለው ግን የሕክምናውን ዓለም እንደከፋፈለው ይነገራል።

https://p.dw.com/p/321cu
Malaria Senegal
ምስል DW/E. Landais

ወባን በባህላዊ መድኃኒት

የታሸገ ሻይ ማዘጋጃ ማሽን ነው፤ እያንዳንዷን እሽግ የሻይ ቅጠል የወረቀት ከረጢት እየቆረጠ ሲያሽግ ያለውን ድምጽ ነው የሰማችሁት። አረንጓዴ የቅጠል ዱቄት የሞላበት እሽግ የሻይ ቅጠል ከስሩ ተደርድሯል። ደርቆ በሻይ መልክ የተዘጋጀው ቅጠል መገኛ ቻይና ናት። እያንዳንዱ የሻይ ቅጠል ከረጢት የሚይዘው መጠን ተስተካክል ወደ ማሽኑ ውስጥ ይከተታል፤ ማሽኑም እያሸገ በመቁረጥ ለተጠቃሚ ዝግጁ እያደረሀ ያወጣዋል። አንዷ እሽግ ለአንድ ብርጭቆ ሻይ በቂ ናት። እያንዳንዱ እሽግ የሻይ ከረጢት 1,7 ግራም አርቴሚሳ አኑዋ ይዟል። አርቴሚሳ አኑዋ የአረንጓዴው ሻይ ቅጠል ሳይንሳዊ ስም ነው። ይህ ተክል ወባን ለማዳን ጥቅም ላይ ውሏል።

«ከወባ በሽታ ለመዳን አንድ ሰው ሦስት ስኒ ሻይ በቀን ጠጣ ማለት 5,1 ግራም አርቴሚሳ አኑዋ ወሰደ ማለት ነው። ከ5 ግራም በላይ ማለት ነው። እናም በቂ ያልሆነ መጠን ከመውሰድ የሚወሰደው መጠን እጅግ ቢበዛ ይመረጣል።»

የሚሉት የቤልጅግ ዜጋ የሆኑት የግብርና ኢንጂኒየር ፒየር ፋን ዳመ። የሻይ ቅጠል ማሸጊያ ማሽኑን የሚያንቀሳቅሱት እሳቸው ናቸው። መንግሥታዊ ባልሆነው የፈረንሳይ ድርጅት ሃውስ ኦፍ አርቴሚዛ በተባለው የሕክምና ባለሙያዎች ለተሰባሰቡበት ድርጅት ነው የሚሠሩት። ይህ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ በ31 የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ይንቀሳቀሳል። የዚህ ድርጅት ዋና ሥራ ይህ ወባን ያጠፋል የተባለውን ተክል ሰዎች በቀላሉ በሻይ ቅጠል  ወይም በኪኒን መልክ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ነው።

«አርቴሚሳን የወሰደ የወባ ታማሚ፤ በሁለት ቀናት ውስጥ ትኩሳቱ ይወርዳል፤ ከአራት ቀናት በኋላም ምንም አይነት የወባ ምልክት አይገኝበትም። ከሰባት ቀናት በኋላ ደግሞ በጉበት ውስጥ የተጠራቀመም ሆነ የተከፋፈለ የበሽታው ተሐዋሲ ፈፅሞ ይጠፋል።»

አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት እጅግ ብዙ ዓመታት ምርመራ እና  የወባ ህክምና ቢካሄድም በስህነት ያልሆነ ህክምናዎች ብዙውን ጊዜ ያጋጥማል። ይህ እንዲህ ነው፤  አንድ ሰው የወባ ህመም ሊያስከትል የሚችለው አይነት የህመም ምልክት ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ ትኩሳት። በዚህ ጊዜ ይህ ሰው የወባ በሽተኛ ሳይሆን የወባ መድኃኒት እንዲወስድ ይደረጋል። ለበርካታ ዓመታት ደግሞ አፍሪቃ ለወባ ሕክምና የምታቀርበው የተለመዱት እንደ ክሎሮኪን እና ሰልፋዶክሲን እንዲሁም ኩዊኒን ያሉትን ቅምም መድኃኒቶች ነው።

Malaria Senegal
ምስል DW/E. Landais

እነዚህን መድኃኒቶች ከመጠን በላይ በመጠቀም ምክንያት ደግሞ በሽታው መድኃኒት የመቋቋም አዝማሚያ እያሳየ ነው። በዚህ ምክንያትም ወባን ለማሸነፍ አዲስ መድኃኒት ያስፈልጋል የሚለው ሁሉንም አግባብቷል።

አሁን በግንባር ቀደምትነት ለዚህ ሕክምና የሚመከረው አርሬሚሳን ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር አደባልቆ መጠቀም ነው። በርካታ ሳይንቲስቶች፣ የጤና ባለሙያዎች እና እንደ ፒየር ያሉ ተመራማሪዎች ከተጠቀሰው ተክል የሚቀመም መድኃኒት ሳይሆን ራሱን ቅጠሉን መጠቀሙ ወባን ፈፅሞ ለማጥፋት ይጠቅማል የሚል እምነት አላቸው።

«እኛ እንዳለ ተክሉን መጠቀምን ነው የምንመክረው፤ ምክንያቱም ይህ ተክል በውህደት የሚሰሩ 200 ጠንካራ ንጥረነገሮችን የያዘ ነው፤ እነዚህ ንጥረነገሮች ደግሞ በደም ውስጥ የሚገኘውን ጥገኛ ተሐዋሲ የሚዋጉ ናቸው፤ ለወባም ቢሆን እንዲሁ ነው።»

የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች አርተሚስን በመጠቀም ለዓመታት ፀረ ወባ መድኃኒቶችን ሲያመርቱ ኖረዋል። በጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ,ም በቻይና የመድኃኒት ፋብሪካ ውስጥ የሚገኝ አንድ የስነቅመማ ባለሙያ የዚህን ተክል ዘርፈ ብዙ የመድኃኒትነት ጥቅም ዳግም አግኝቶ ይፋ በማድረጉ የኖቤል ሽልማት አግኝቷል። የተጠቀሰው ተክል በቻይና ባህላዊ መድኃኒት ዘርፍ ለምዕተ ዓመታት የዘለቀ ጥቅም በመስጠቱ ይታወቃል።

እንዲያም ሆኖ የዓለም የጤና ድርጅት ይህን ተክል እንደተገኘ በመድኃኒትነት መጠቀምን ይቃወማል። ከዚህ ይልቅ በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ ACT ማለትም የአርትሜሲን ድብልቅ መድኃኒትን ይመክራል።

ድርጅቱ እንደሚለው በመላው ዓመት ከዛሬ 18 ዓመታት ወዲህ በወባ ምክንያት የሞመተው ሰው ቁጥር 60 በመቶ ቀንሷል።  ለምሳሌ ሴኔጋል ውስጥ የዛሬ 10 ዓመት 700 ሺህ ይደርስ የነበረው በወባ በሽታ የተያዘው ሰው ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ከ300 ሺህ ያንሳል። የሴኔጋል ብሔራዊ የወባ መቆጣጠሪያ መርሃግብር ባልደረባ ዶክተር አሊዮኔ ጉዬ እንደሚሉት ይህ ለውጥ የመጣው በሀገሪቱ ነፃ የወባ ህክምና  መሰጠቱ እና የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ስርጭት ምክንያት ነው።

Malaria Senegal
ምስል DW/E. Landais

«አሁን ሴኔጋል በሽታውን ለማጥፋት ከመቃረብ የደረሰችው ላለፉት 15 እና 20 ዓመታት በተጠቀምንበት ዘዴ አማካኝነት ነው። ይህ አሁንም ውጤታማ ሆኖ ቀጥሏል።»

አርተሚስ የተሰኘውን ተክል ለወባ ማጥፊያነት መጠቀም የሚለው የተደባለቀ ስሜት ነው የፈጠረባቸው፤ ይህ ተክል ለመድኃኒትነት መዋሉን ባይጠራጠሩም ተጨማሪ ምርምሮች መደረግ አለባቸው ነው የሚሉት።   

«ይህ ተክል አዎንታዊ ጎኖች ያሉት መሆኑ ግልፅ ነው፤ ሆኖም ግን እኛ ደግሞ የሕዝብ ጤና የሚመለከተን አካላት ነን፤ ሴኔጋል ውስጥም 41 ሚሊየን ሕዝብ እናገለግናለን። እጅግ ብዙ ሕዝብ ነው፤ የምንወስዳቸው ርምጃዎች ወሳኝ ናቸው እናም በሀገር ደረጃ ከማከፋፈላችን በፊት የእነዚህ ምርቶችን ደህንነት እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል።»

አርቴሚሲያ አኑዋ አፍሪቃ ውስጥ በተፈጥሮ የሚበቅል ተክል አይደለም። አፍሪቃ ውስጥ የሚገኘው አርቴሚሲያ አፍራ ነው፤ ተዛማጅ ዝርያ መሆኑ ነው። ግን ደግሞ ይህ አፍሪቃ ውስጥ የሚገኘው ተክል ከአርቴሚሲያ አኑዋ የሚለይ ንጥረነገር በተፈጥሮ አለው። ቀደም ሲል እንደተጠቆመው ይህ ተክል በውስጡ 200 የተለያዩ ንጥረነገሮችን የያዘ ሲሆን አፍሪቃ ውስጥ የሚበቅለውን እና ከሌላ የሚመጣውን አርቴሚሲያ በመደባለቅ ነው በሻይ መልክ ታሽጎ እንዲቀርብ የተደረገው።

በስተሰሜን ዳካር ላይ ሁለቱም ተክሎች እንዲበቅሉ ተደርጎ ሁለቱም አድገዋል። 

ካሪም ሳንካራ በስፍራው የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እና ሌሎች ሁለት ባልደረቦቻቸው ናቸው በ4 ሄክታር መሬት ላይ ለተተከሉት 8,000 የሚሆኑ የመድኃኒት ዛፎች ክትትል ያደርጋሉ።

«ለመድኃኒት የሚሆነው የዛፎቹ ቅጠል ነው፤ ፍሬው ይሰበሰብና በቀጣዩ ወራት እንዲዘራ ይቀመጣል። በዋናነት ቅጠሉን ነው የምናመርተው፤ ብዙ ቅጠል ለመሰብሰብ ስንልም ትልልቆቹን ተክሎች ነው የምንመርጠው።»

እሳቸው እንደሚሉት እነዚህ ተክሎች ቶሎ ነው የሚያደጉት። ቁመታቸው 1 ሜትር ከ20 ገደማ ሲደርስ ቅጠላቸው ለመለቀም ደረሰ ማለት ነው።

የደረቀው የዚህ ተክል ቅጠል ኮንጎ እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በወባ በሽታ የተያዙ ሰዎችን እንዳዳነ የሚያመለክት ጥናት ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ተካሂዷል። በወባ ክፉኛ የታመሙ 18 ሰዎች ለወትሮዉ የሚወስዱትን የወባ መድኃኒት መውሰደው ለመዳን አልቻሉም። በኋላ ግን ከዚህ ቅጠል የተዘጋጀውን ሻይ ጠጥተው ከበሽታቸው መዳናቸውን ጥናቱ ያመለክታል። ብራዛቪል የሚገኘው የዓለም የጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤትም ከዚህ ጊዜ አንስቶ ይህ ተክል ሊኖረው የምችለውን ጥቅም ለማጥናት ወሰነ። 

ሲስተር ሜሪ ኤሚሊ ዲዮፍ ከዳካር ወጣ ብላ በምትገኘው ፖፔንጉዊኒ መንደር በሚገኘው የካቶሊክ የጤና ማዕከል የልምድ አዋላጅ ናቸው። ከጓዳ ተጥዶ ከሚንተከተከው ወርቃማ ድብልቅ ፈሳሽ በስኒያቸው ቀዱ እና ወደ አፍንጫቸው አስጠጉት።

Malaria Senegal
ምስል DW/E. Landais

«ከእሬቱ ቀድቼ ነበር፤ አሁን ቅጠሎቹ ናቸው የቀሩት፤ የተለያዩ ናቸው፤ ባህር ዛፍ አለ፤ የማንጎ ቅጠል አለው እንዲሁም አርቲሜሲንም አለበት።»  

ከሦስት ዓመት በፊት አንድ የእፅዋት ህክምና አውደ ጥናት ላይ ከተካፈሉ ወዲህ፤ የወባ በሽታ በተስፋፋት ዲርብል ከተማ ለሚኖሩ ወባ ታማሚዎች አርቲሜሲን እንዲጠቀሙ ይመክሩ ነበር። በእሳቸው እምነት ድብልቁን የአርቲሜስን መድኃኒት ከመጠቀም ይልቅ ቅጠሉን መጠቀሙ የተሻለ ውጤት ያስገኛል።

«በህክምና ከረዳኋቸው ታማሚዎቼ የተረዳሁት፤ ኩዊኒንም ሆነ ሶሉተር ወይም ድብልቁን አርቲሜሲን መድኃኒት መጠቀሙ አይረባም። እኔ ተጠቅሜባቸው አላውቅም። አርቲሜሲያን ብቻ ነው የምሰጣቸው፤ ከዚያ በኋላ ጉሉኮስ መስጠት እንኳ አያስፈልግኝም።»

የእነዚያን መዳን ያስተዋሉ ሌሎች የወባ ታማሚዎች ወደእሳቸው ይመጡ ጀመር። ቅምም መድኃኒቶቹ በመጋዘን ውስጥ ቢከማቹም ታማሚዎቹ የሚመርጡት ይህንን ሆነ። ኅብረተሰቡ ለባህላዊ ህክምና ወይም ለቅጠሉ ያሳየውን ዝንባሌ ያስተዋሉት ዶክተር ኦሊዩስ ጉዌይ የተሻለ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ብሔራዊ የወባ መቆጣጠሪያ መርሃግብሩ ለባህላዊ መድኃኒት አዋቂዎች ምክሩን እንደሚለግስ ይናገራሉ። ሴኔጋል በጎርጎሪዮሳዊው 2030ዓ,ም ወባን ፈጽማ ለማጥፋት እየሰራች ነው። ለዚህም በቂ የገንዘብ ድጋፍ አላት። ምንም እንኳን የመድኃኒቱ አቅርቦት ችግር ባይኖርበትም ፀረ ወባ ነው የተባለውን ተክል በየቦታው ተክሎ የመጠቀሙ ዝንባሌም ጎልቶ እየታየ ነው።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለመቃኘት ወደ ጤና ጥበቃ የወባ ጉዳይ ወደሚመለከታቸዉ ኃላፊ ወሮ ሕይወት ጋር ተደጋጋሚ ስልክ ብደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ለዛሬ አልተሳካም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ