1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቶችን ከ«ሞራል ዝቅጠት» ማዳን

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ኅዳር 7 2011

ወጣቶች በተደጋጋሚ ካነሷቸዉ ጥያቄዎች አንዱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አድርሰዋል፤ የህዝብ ሐብት መዝብረዋል የተባሉት የመንግስት ባለስልጣናትና ተባባሪዎቻቸዉ ለፍርድ ይቅረቡ የሚለዉ እንደነበረ የቅርብ ግዜ ትዉስታ ነዉ።

https://p.dw.com/p/38OCv
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Demonstration mit Anhängern
ምስል Reuters

ሰሞኑን መንግሥት በሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በሙስና የተጠረጠሩ ከተራ ግለሰብ እስከ ጄኔራል ድረስ በቁጥጥር ስር እያዋላቸዉ ይገኛል። ወጣቶቹ ያቀረቡት ጥያቄ መልስ እያገኝ ይሆን?

ወጣቱ «መንግስት ይቅርታ ለማያዉቁት ይቅርታ አበዛ፣ ለምን አይዝዋቸዉም?» ብሎ ሲጮህ እንደነበረ የባቲ ነዋሪ ሌሊሳ ባጫ ተናግሮአል። መንግስት ሰሞኑን እየወሰደ ያለዉ ርምጃ ግን «ህልም» እንደሆነበት በግርምት ያስረዳል። 

ሌሊሳ እንደሚለዉ መንግስት ጊዜ ወስዶ በምርጫ ቦርድ አካባቢ «መቶ በመቶ ኢሕአዴግ አሸንፈዋል» እያሉ የሕዝብን ድምፅ ሲዘርፉ» የነበሩ፣ በመገናኛ ብዙኃን ዉስጥ «የውሸት ትረካ» ሲያሰራጩ የነበሩ፣ በኢንቨስትመንትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ዉስጥ ወንጀል የሠሩ ሁሉ ለፍትህ መቅረብ አለባቸዉ።

ወጣቶች ከቀበሌ እስከ አገር አቀፍ ድረስ የታዘቡት፤ ከሰፈር ወሬ እስከ ዓለማቀፍ ዘገባዎች ሲሰሙ የነበሩት፤ የመንግሥት ባለስልጣናት ሲዘርፉ፣ ሲገድሉና ሲያስገድሉ፣ ሲያስሩና ሲያሳስሩ እንዲሁም ሲያሳድዱ ነዉ። ይህ በወጣቶች ሥነ-ልቦና ላይ ያደረሰዉ ምን ይሁን? መፍቴዉስ? በባህርዳር ዩኒቬርስቲ የሥነ-ልቦና ባለሙያ አቶ ታምሩ ደለለኝ መልስ አላቸዉ።

በአፍላ እድሜ ላይ ያለዉ ወጣት በትዕግስት ነገሮችን ማሳለፍ ቢከብደዉም ከዶክተር ዐብይ ትግስት መማር አለባቸዉ ሲል የባቲ ነዋሪዉ ሌሊሳ ባጫ ይናገራል። «ሳዋ አባን ጋንፋ ጨብሴ ሆርም ኢጃ ጃምሳ»፣ የአማርኛ ትርጓሜዉ «ባለቤቱ ራሱ የበሬዉን ቀንድ ከሰበረዉ፣ ባዳዉ ደግሞ ዓይኑን ያጠዋፏል» የሚል የአፋን ኦሮሞ አባባል፣ ለወጣቱ የትግስት ትምህርት እንደሚሰጥና የመንግሥትን እርምጃ መደገፍ እንዳለበት ያስገነዝባል ሲል ሌሊሳ አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በትምህርታቸዉ፣ በሥነ-ጥበብና በመልካም ምግባራቸዉ ያከናወኑት ለወጣቶቹ አረአያ ነዉ ሲሉ አቶ ታምሩ አክለዋል። ላለፉት አስርተ ዓመታት የነበረዉ የግለሰቦችም ሆነ የቡድኖች የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ፍላጎት ወጣቱ እንዲራራቅ አድርገዋል የሚሉት የሥነ-ልቦና ባለሙያዉ፣ አሁን ዶክተር ዐብይ ግን ሌላ አቀራረብ ይዘዉ መጥተዋል ባይ ናቸዉ።

«ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ይቆጨዋል» የሚል አስተሳሰብ በወጣቱ መስረፅ የለበትም ይላሉ አቶ ታምሩ። ስለዚህ መንግሥት የሚመጣዉን ትዉልድ ለማዳን ካቀደ፤  ወጣቱ እሴቱን ከፍ እንድያደርግ ከተፈለገ በግብረገብ ትምህርት ላይ ማተኮር አለበት በማለት ባለሙያዉ ሃሳባቸዉን ለግሰዋል።

ኢትዮጵያ ወጣቶቿ ላይ «መዋእለ ኑዋይ ካላፈሰሰች፣ መልካም ትምህርትና ፍቅር ካልሰጠች፣ አደገኛ ቦዜኔ አድርጋ ካየች» ተመልሳ ግጭት ዉስጥ ትገባለች ሲሉም ተናግረዋል። ወጣት ሌሊሳም የእድሜ እኩዮቹ ካለፉት ድርጊቶች መማር እንዳለባቸዉ ይመክራል። 

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ