1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የግጭት ግድያዉ መንስኤ እና መዘዙ

ነጋሽ መሐመድ
እሑድ፣ መስከረም 13 2011

የአዲስ አበባ እና ያካባቢዋ ግድያ የደረሰዉ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የቀድሞዎቹ አማፂ ቡድናት፤ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ደጋፊዎች አዲስ አበባ ዉስጥ በባንዲራ እና አርማ ሰበብ ሲነታረኩ ከሰነበቱ በኋላ ነዉ።

https://p.dw.com/p/35Jft
Äthiopien Proteste in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/AA/M.W. Hailu

ዉይይት፤ ፍካት እና ፅልመት

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተከታታይ አመታት ትግል፤ ተቃዉሞ፤ ደም አፋሳሽ ግጭትና ጥፋት በኋላ አዲስ በፈነጠቀዉ የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ፤የሠላም እና የአብሮነት ጮራ በሚደሰት፤ለለዉጡ ፅናት በሚታትርበት መሐል በመቶ የሚቆጠሩ የዋሕ ወገኖቹ እየተገደሉ፤ ሺሕዎች እየተፈናቀሉ፤ ሐብት ንብረቱ እየተመዘበረ ነዉ።የሰብአዊ መብት ጉባኤ እንዳስታወቀዉ ካለፈዉ ኃምሌ እስከ መስከረም በተቆጠረዉ ጊዜ ብቻ ሶማሌ፤ደቡብ ኢትዮጵያ፤ ኦሮሚያ እና ትግራይ መስተዳድሮች ጎሳን በተላበሱ ግጭቶ በትንሹ 200 ሰዎች ተገድለዋል።

ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ግጭት፤ ግድያ ዘረፋዉ ርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባ እና አካባቢዋን እየናጣት ነዉ።አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች አጥኚዎች እንደዘገቡት ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ በቡራዩ፤ በአሸዋሜዳ እና በአካባቢያቸዉ ነዋሪዎች ላይ የዘመቱ ወጣቶች ሲያስ 58 ሲበዛ 65 ሰላማዊ ሰዉ ገድለዋል።ከ12 ሺሕ በላይ አፈናቅለዋል።ግምቱ በዉል ያልታወቀ ሐብት ንብረት ዘርፈዋል፤ አቃጥለዋልም።

የቡራዩ እና ያካባቢዉን ጥቃት ለመቃወም ባለፈዉ ሰኞ አዲስ አበባ ዉስጥ በተደረገ ሠልፍ መሐል ፖሊስ «አደጋ ለመጣል የሞከሩ» ያላቸዉን አምት ሰዎች ገድሏል። ሰኞዉኑ ለተመመሳይ ተቃዉሞ ደቡብ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ከተማ ሰልፍ የወጣዉ ሕዝብም ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር  ተጋጭቶ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

የአዲስ አበባ እና ያካባቢዋ ግድያ የደረሰዉ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የቀድሞዎቹ አማፂ ቡድናት፤ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ደጋፊዎች አዲስ አበባ ዉስጥ በባንዲራ እና አርማ ሰበብ ሲነታረኩ ከሰነበቱ በኋላ ነዉ።

Äthiopien Bevölkerung begrüßen OLF-Führungskräfte
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች ወይም ደጋፊ የሚመስሉ ወገኖች አሁንም በመገናኛ ዘዴ በተለይም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መወቃቀስ፤ መወጋገዛቸዉ እንደቀጠለ ነዉ።

የኦሮሚያ እና የፌደራል መንግስት ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሰዎችን ያጋጩ፤ ያስገደሉ እና አሁንም ግጭቱ እንዲቀጥል የሚሞክሩት አስቀድመዉ የተደራጁ ኃይላት ናቸዉ።ከነዚሕ ኃይላት የተወሰኑት ከታጠቁት መሳሪያ፤ ከገንዘብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ጋር መያዛቸዉንም መንግሥት አስታዉቋል።ይሁንና የመንግሥት ዉግዘት እና መግለጫ «አስቀድሞ እርምጃ ለምን አልወሰደም» የሚል ጥያቄ አስነስቷል።ግጭት ግድያዉ የኢትዮጵያን የወደፊት ጉዞ፤ በተለይ ብዙ ሕዝብ የተቀበለዉን ለዉጥ ሒደትን አጠያያቂ፤ አስጊም አድርጎታል።የግጭቱ መንስኤ፤ የጥፋቱ መጠን እና ያስከተለዉ ጥያቄ እና ሥጋት የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ