1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፦ የኢትዮጵያ መንግስት ሕግ እና ሥርዓት ማስከበር ለምን ተሳነው?

እሑድ፣ ኅዳር 2 2011

ዶ/ር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒሥትርነቱን ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በየአካባቢው የሚደረጉ በአብዛኛው ብሔርን ምክንያት ያደረጉ ግጭቶች እየተባባሱ መጥተዋል። ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ጎላ ብለው መታየት ያልቻሉ ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት የብዙዎችን ሕይወት የሚያጠፉ፣ በርካታ ሀብት እና ንብረት የሚያወድሙ ግጭቶችን እያስከተሉ ነው።  

https://p.dw.com/p/3846f
Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

የኢትዮጵያ መንግስት ሕግ እና ሥርዓት የማስከበር ለምን ተሳነው?

ከኢትዮጵያ ሶማሌ -ኦሮሚያ አዋሳኝ ቦታዎች ጀምሮ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና አልፎ ተርፎም ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባና አካባቢዋ ድረስ በየጊዜው በተነሳው ግጭት በርካታ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። ከግጭቱ በተጨማሪ በየአካባቢው የመንግስት መዋቅሮች በመላላታቸው ወይም ጠንካራ የጸጥታ፣ የደህንነት እና የፍትህ ስርዓት ባለመኖሩ ኢትዮጵያውያን በሰላም ወጥተው መግባታቸውን መጠራጠር ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

የፌደራሉም ሆነ የክልል መንግስታት ህግና ስርዓትን ለማስከበር እንደሚጥሩ በየጊዜው ቃል ቢገቡም ችግሩ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ አይደለም ሲሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች ይናገራሉ። የስርዓተ አልበኝነት መልክ እና ባህሪ የተላበሰው ይህ አሳሳቢ ችግር በዚሁ ከቀጠለ አዲስ የተያዘው ለውጥም ሆነ አጠቃላይ የሀገሪቱ ደህንነት ለከፋ አደጋ ያጋልጣል ብለውም ይሰጋሉ። 

Äthiopien ethnische Minderheit der Gedio
ምስል DW/Shewngizaw Wegayehu Aramdie

ለዚህ የጸጥታ መታጣት ችግር የተለያየ ምክንያት ሲቀርብ ይደመጣል። ከውጭ የተመለሱ የፖለቲካ ኃይሎች እና የስራ አጥ ወጣት ቁጥር መበራከት እና በለውጡ ከሚገባው በላይ መጠበቅ ለችግሩ ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው። ብዙዎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት በስርዓት አልበኝነት እና የሀገሪቱን ጸጥታ በሚያደፈርሱ ኃይሎች ላይ ፈጣን እና ግልጽ እርምጃ አለመውሰዱ ግጭቶቹን የሚያባብሱ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ ለመምጣታቸው ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

የግጭቶቹ ምክንያቶች፣ የመንግስት ዳተኝነት እና ያስከተለው ስጋት የዚህ ሳምንት ውይይታችን የሚቃኛቸው ጉዳዮች ናቸው። በዕለቱ ውይይት ላይ የሚሳተፉት የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን እና አሁን የአፍሪካ የስልታዊ እና የጸጥታ ጉዳዮች አጥኚ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ የምስራቅ አፍሪቃ የጸጥታ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ሃሌሉያ ሉሌ እና በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ሙሳ አደም ናቸው።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ልደት አበበ